በመካነ ሰላም በመንግሥትና በፋኖ ኃይሎች መካከል ትላንት ሰኞ ከባድ ውጊያ መደረጉ ተገለጸ
ማክሰኞ፣ መስከረም 26 2019
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ ዙሪያ ትናንትና ከማለዳው 12 ሰዓት ተኩል በኋላ በመንግሥት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል ከባድ ጦርነት መካሄዱን የከተማው ነዋሪዎች ለዶቼቨለ ተናገሩ። ትናንት ከእኩለ ቀን በኋላ ጦርነቱ ተቀዛቅዟል ያሉት የመካነ ሰላም ከተማ ነዋሪም ዛሬ በከፊል ማኅበረሰቡ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሷል ይላሉ።
«ዛሬ ደህና ነው። እንግዲህ ትናንትና ነበር ትንሽ ከባድ ነገር የነበረው። ዛሬ ሰላም ነው። ምናልባት ማታ ትንሽ ከባድ መሣሪያ ተኩሶች አንድ አልፎ አልፎ ሰምተን ነበር። እስከ ሰባት ሰዓት ድረስ ትናንትና ግን ከባድ ነበር። ከቤት አልወጣንም እኛም። ያው ተኩሱም ከባድ መሣሪያ ነበር የሚባለው። አንዳንድ የሚሰማው ልክ እንደ ክላሽ የማያቋርጥ ከባድ መሣሪያ ይሰማል። ግን ሰላም ነው፤ አሁን በከተማው ውስጥ ሰላም ነው። ምናልባት ያን ያህል የተኩሶ ጉዳቱ ሲታሰብ ተመስገን ያስብላል።»
በአካባቢው ከዚህ ቀደም በርካታ የተኩስ ልውውጥ ማየታቸውን የነገሩን መምህርም ትናንት የነበረው ጦርነት ከዚህ በፊት አጋጥሞ የሚያውቅ በማለት ይናገራሉ። ዛሬም በትምህርት ቤት ለተገኙ ተማሪዎቻቸው ትምህርት ለማስተማር አለመቻላቸውን ይገልጻሉ።
«ትናንት አሁን እንደዚህ አይነት... ማለት ብዙ ጊዜ እንደዚህ ተበጥብጠን እናዉቃለን ፤ ግን እንደዚህ አይነት ሜካናይዝድ መሳሪያዎችን ከባድ ነበረ በቃ... ሮኬቶች፣ ምንም፣ ምንም... በቃ የመሳሪያ አይነት የተለየ ነገር ነበረው እና በጣም ከባድ አይነት ነገር ነው። አሁን የትኛው ገጠር ላይ ምን ተጎዳ፣ ምን አለ፣ ምናምን... ለጊዜው ምንም አላወቅንም፤ ወጥተህ ከሰው ጋርም እስካልተቀላቀልክ ድረስ ማለት ነው። ከቤታችን ውጪ እንቅስቃሴው ከባድ ነበር። ዛሬ ራሱ በስጋት ነው የገባነው ። ግን ተማሪዎችን ማስተማር አልቻልንም፤ ምክንያቱም ተማሪዎችጥሩ አልነበሩም። መከላከያዎቹም ሲታኮሱ አይተዋል፣ ፈርተዋል።»
ዛሬ መደበኛው የማኅበረሰብ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የቀጠለበት መካነ ሰላም ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን የነገሩን አስተያየት ሰጭም ጦርነቱ በበርካታ የከተማው አቅጣጫ መካሄዱን ይጠቅሳሉ።
«አሁን መከላከያ ነዉ ያለዉ ምናልባት ገባ ብሎ ወጥቷል። አይ ረጅም ሰዓት አልቆዮም መሰለኝ ። በአንድ በኩል ያለው፣ በዚህ በተዋ በኩል ያለው፣ በዚያ በደብረ ማርያም አካባቢ ሁለት ሦስት ቦታ ነበረ። ማለፋ አልቻሉ ም ። በወዲህ በኩል፣ ቦጎሎ ብሎ የሚባል አለ። ቀጠና በዚህ በሰሜኑ በኩል፣ በዚያ አካባቢ ያለው ነው ገባ ብሎ የወጣው። ስለዚህ ከባድ መሳሪያው በጣም ከባድ ስለነበረ ውጊያው በቃ በከባድ መሳሪያ ነበረ»
ትናንት በመካነ ሰላም ከተማ ዙሪያ በነበረው ጦርነት የአንድ ታዳጊ ህፃን ህይወት ማለፉን እና ቤተሰቦቿ ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማው ነዋሪ ተናግረዋል።
«ሆይሄ አካባቢ ንፁሐን ተጎድተዋል። ህፃን ልጅ ሞታለች። እንደገና ደግሞ እናትና አባቷ ደግሞ በከባድ ቁስለት ሆስፒታል ገብተዋል። አሁን እዚያ አካባቢ ራሱ አሁን ያለው መከላከያ ነው። አሁን ፀጥ ብሏል አሁን። ምንም ነገር የለም አሁን። ከጠዋት ጀምሮ፤ ተማሪውም አልፎ አልፎ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ነው። ሰራተኛዉምወደ ቢሮ ገባ ገባ እያለ ነው። የትናንትናው በጣም አስፈሪ ነበረ።»
«ንፁሃኑ እንግዲህ ወደ ቀበሌ 03 ጎየ በሚባል ቦታ ላይ ቤትና አንድ ህፃን ሞታለች። ቤት ላይ ያረፈው ነገር ከማንኛዉ ኃይል የተወረወረ እንደሆነ ያንን መረጃ የለኝም፤ ግን በጠዋት ጀምሮ አየሩ ሰላም ነው። ህዝቡ እንቅስቃሴውን አሁን በሚገባ እንቅስቃሴውን እያደረገ ነው። ትምህርት ቤቶችም ዛሬ የተከፈቱ አይመስለኝም ። ያው ትንሽ ስጋት እንደሚያድርባቸው ሆኖ እንጂ፤ ዙሮ ዙሮ በከተማው ውስጥ ያለው አየር ጥሩ ነው፣ ሰላም ነው አሁን።»
በመካነ ሰላም ከተማ ትናንት በነበረው ጦርነት የደረሰውን ጉዳት ከከተማው የስራ ኃላፊዎች ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ኢሳያስ ገላው
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ