1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአማራ ክልል 88ሺህ ያክል ሠዎች የውጪ የሥራ ስምሪት አግኝተዋል

ዓለምነው መኮንን
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 3 2017

በፌድራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል በተዘረጋ አሠራር ከአማራ ክልል 88 ሺህ የሚሆኑ ሥራ ፈላጊዎች ወደ ውጪ ሀገራት መጓዛቸውን የክልሉ ሥራ እና ስልጠና ቢሮ ገለጸ። በህገወጥ መንገድ ወደ ከአገር ሊወጡ የነበሩ 6 ሺህ ወገኖችን መመለስ መቻሉንም አመልክቷል።

 የአማራ ክልል ሥራና ሰልጠና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ
በፌድራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በኩል በተዘረጋ አሠራር ከአማራ ክልል 88 ሺህ የሚሆኑ ሥራ ፈላጊዎች ወደ ውጪ ሀገራት መጓዛቸውን የአማራ ክልል ሥራና ሰልጠና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ ተናግረዋል። ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል 88ሺህ ያክል ሠዎች የውጪ የሥራ ስምሪት አግኝተዋል

This browser does not support the audio element.

በህገወጥ መንገድ ከአገር ለመውጣት የሚፈልጉ ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት፣ ስቃይና ሞት እየተዳረጉ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜዎች የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፣ የዜጎችን የውጪ አገር የሥራ ስምሪት ህጋዊ ለማድርግ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆኑ የአማራ ክልል ሥራና ሰልጠና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል፡፡

ማንኛውም የውጪ ሥራ ስምሪት ፈላጊ አካል “Ethiopian Labour Management Information System” (ELMIS) በሚል በተንቀሳቃሽ ሞባይል ስልክ ጎግል ላይ ወደ ፌደራሉ ሥራና ስለጠና ሚኒስቴር በመመዝግብ የሥራ ፈላጊ መለያ ቁጥር (ID) እንድሚያገኝና የሥራ ስምሪት እንደሚያገኝ ተናግረዋል። የሕገ-ወጥ ስደት አስከፊ ገጽታ - ከሞት መለስ ያሉ የስቃይ ምዕራፎች

በዚህ መንገድ በበጀተ ዓመቱ  87ሺህ 972 ሥራ ፈላጊዎች በአውሮፓና በአረብ አገራት የሥራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ወደ አንዳንድ አገራት በሥራ ስምሪትና  የሚሄዱ ሠዎች ችግር እንደሚደርስባቸው ቅሬታ ይሰማል፣ ለነኚህ ሠዎች እንዴት መድረስ ይቻላል? ስንል አቶ አንዳርጋቸውን ጠይቅናል፣ ህጋዊ በሆነ መንግድ ለሚወጡ ሥራ ፈላጊዎች ውል የሚይዝላቸው የፌደራሉ ሥራና ስልጠና ሚኒስቴር ሆኖ፣ የት እንደሚሄዱ፣ እስከመቼ እንደሚቆዩ ማን ጋ እንዳሉ ስለሚታወቅና ሠዎቹ ቋሚ አድራሻና ተያዥም ስለሚኖራቸው በቀላሉ መድረስ እንደሚቻል ነው የነገሩን፡፡

“... ክብራቸውን ጥብቀው የውጪ አገር ስምሪት እንዲያገኙ ዋስትና መንግሥት ወስዶላቸው፣ የት አገር፣ እስከመቼ ይቆያሉ ፣ ከማን ጋ እንደሚሰሩ መንግሥት ያውቃል” ብለዋል፡፡
ለአገር ውስጥ የሥራ ስምሪት  ትኩረት ተስጥቶ እየተሰራ ስለምሆኑ የሥራ ስምሪቱ በአገር ውስጥም በስፋት እንድሚተገበር የገለፁት አቶ አንዳርጋቸው፣ በዚህም በርካቶች ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ እድል እንዳገኙ አመልክተዋል፡፡ የብድር አገልግሎቶችም በአገር ወስጥ መመቻቸታቸውን አቶ አንዳርጋቸው አብራርተዋል።


ኢትዮጵያዊያንን ለአደገኛ የፍልሰት ጉዞ የሚዳርጓቸው ገፊ ምክንያቶች ምንድናቸው ?

በአማራ ክልል ከሚገኘው የወሎ አካባቢ ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ሥራ ፍለጋ የመንን በማቋረጥ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት ሲሞክሩ በባሕር ላይ ሕይወታቸውን ያጣሉምስል፦ AFP/Getty Images

ህጋዊ የውጪ የሥራ ስምሪት የሚያመቻቹ ድርጅቶች ቢኖሩም አሁንም በህገወጥ መንገድ ሠዎችን የሚያዘዋውሩ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመት ብቻ 6ሺህ ሠዎች በህገወጥ መንግድ ከአገር ለመውጣት ሲሞክሩ መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡ ተመላሾችም የተሀድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው ከማህበረሰባቸው ጋር መቀላቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንዳቸው ሠራው ለዜጎች ስደት ድህነት ብቸኛው ምክንያት እንዳልሆነና ይልቁንም  ነጋዴዎችና የተማሩ ሠዎችም  ከአገር ሲወጡ ይታያሉ ብለዋል፡፡ ገፊም ሳቢም ምክንያቶች አሉ ያሉት አቶ ወንዳቸው፣ ግጭቶችና ድህነት ገፊ ሊሆኑ ሲችሉ የተሻለ ገቢና የተመቻቸ የውጪ ኑሮ ደግሞ ሳቢ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

“በህገውጥ የሠዎች ዝውውር የተከሰሱ እስከ 21 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል” የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ

የሠዎች ዝውውር ወንጀል ፈፃሚዎችም ከባድ ቅጣት እንደሚያርፍባቸው አቶ ወንዳቸው ተናግረዋል፡ በክልሉም እስከ 21 ዓመት የእሥራትና እስከ 25ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የተቀጡ እንዳሉ ነው ያስረዱት፡፡

የመን፤ የወጣት ኢትዮጵያዉያን የባህር ላይ አሰቃቂ የስደት ጉዞ ማብቂያዉ የት ነዉ?

ባለስልጣናቱ ወጣቱ ከተሳሳተ ግንዛቤ መራቅና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የቅርብ የመረጃ ልውውጥ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ወጣቱ ህጋዊ መንግድን ብቻ ተክትሎ የውጪ የሥራ ስምሪት በማግኘት  ራሱን ከሞት፣ ከአስከፊ የእግር ጉዞና ከእንግልት እንዲያድን፣ ቤተሰቡን ደግሞ ከጭንቀትና ከሐዘን  እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW