1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአማራ ክልል የነዳጅ ዘይት እጥረት የፈጠረው የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል

ኢሳያስ ገላው
ረቡዕ፣ መጋቢት 9 2018

በመካከለኛው ምስራቅ ካለው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የመጣው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ክፉኛ እየፈተነው ይገኛል። በተለይም የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመጓዝ የወጡ በርካታ መንገደኞች በመናኸሪያዎች ተስተጓጉለዉ እንደሚገኙ ታውቋል።

በአማራ ክልል ሰዎች አውቶቢስ ለመሳፈር ተሰልፈው
የኢድ አል ፈጥር በዓልን ለማክበር ወደ ቤተሰቦቻቸው መጓዝ የሚሹ በትራንስፖርት እጦት ተሰቃይተዋልምስል፦ Esayas Gelaw/DW

በአማራ ክልል የነዳጅ ዘይት እጥረት የፈጠረው የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል

This browser does not support the audio element.

የመካከለኛው ምስራቅ አለመረጋጋት አሁን ላይ ህመሙ ከከፍተኛ የነዳጅ ዘይት እጥረት ጋር በአማራ ክልል መታየት ጀምሯል፡፡ የነዳጅ እጥረቱ በብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችላይ ጫናን እየፈጠረ ነው፡፡ በ ኢትዮጵያ  ነገ አለያም አርብ የሚከበረውን የኢድ አል ፈጥር በዓል ለማክበር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከሌሊት 11፡00 ሰዓት ጀምረው በደሴ መናኸሪያ ቢሰለፉም እስከ ቀኑ እኩሌታመኪና ማግኘት እንዳልቻሉ የሚናገሩት ተጓዥ ፋጡማ አሊ በርካታ መኪኖች ቢኖሩም ለማህበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ 

"ስሁር ላይ መጥተን ይሄው እየጠበቅን ነው፤ በጣም  ነው የተጉላላነው ትራንስፖርት ቢቀርብልን ደስ ይለናል፡፡ መኪኖች ቆመዋል፡፡ ትራስፖርት ግን እየሰጡ አይደለም፤ እኛም ተቀምጠናል፡፡ ብርዱ፣ምኑ፣ምኑ እንደምታየው በቃ ቤተሰብ ጋር ነበር በዓል ለማክበር የምንሄደው ግን ካልሄድን ምን ዋጋ አለው፡፡"

በባህር ዳር ከተማ አሽከርካሪ የሆኑት አስተያየት ሰጭም በነዳጅ ዘይት እጥረት ምክንያት ስራ ፈተው ቤት መዋላቸውን ይናገራሉ፡፡ 

" ተኝተን ነው ያለነው  ቤት ነው ያለን የኔ አባት፤ ቆመናል ከባድ ነው ቤንዚን እያገኘን አይደለም፤ ናፍጣው ግን የተወሰነ ማደያ አለ፤ ግን አይበቃም፡፡" ይላሉ  

መነሻቸውን ወልዲያ ከተማ ያደረጉት አሽከርካሪም ባለፉት አራት ቀናት ነዳጅ ለመቅዳት በማደያ ወረፋ ቢይዙም ማግኘት አለመቻሉን ይገልፃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ነዳጅ ለመቅዳት  እጅ መንሻ እንደሚጠየቅም ነው የሚናገሩት፡፡

በአማራ ክልል የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ከመከሰቱ በፊትም በተለያዩ ምክንያቶች ተከስቶ ነበርምስል፦ Esayas Gelaw/DW

"የነዳጅ እጥረቱ በጣም ችግር ገጥሞታል በስራችን መስራት አልቻልንም ተገልጋዮችም መገልገል አልቻሉም፤ ነዳጅ ለመሰለፍ ሄደን ለመቅዳት ወረፋ ይባላል፡፡ የሚቀዳውም በመሃል ይገባል ገንዘብ እየተሰጠ ነው በዚያ ላይ ለልማት ይውላል ይባላል ለኮሪደር ልማት፤ ህብረተሰቡ እንደምታየው ትራንስፖርት አጥቶ መናኸሪያ ላይ ነው፤ ታክሲውም በእግር ሆኗል ሰው እየሄደ ያለው፤ እንደ እኔአሁን እዚህ ከተሰለፍኩኝ አራት ቀኔ ነው፡፡ በአራት ቀን ውስጥ ራሱ ማግኘት አልቻልኩም ናፍጣ፡፡"

የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት በመጠቀም ነዳጅን በህገወጥ መንገድ የሚሸጡ መኖራቸውን የሚገልፁት አሽክርካሪዎች አንድ ጀሪካን የናፍጣ ዘይት ከ11 – 12 ሺህ ብር እንደሚገዙ ይገልፃሉ፡፡ 

የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ክፉኛ እየፈተነው ይገኛል።ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

"ኮንትሮባንድ በጀሪካ 11 ሺህ፣ 12ሺ ብር ውድ ነው፡፡ 12 ሺ ብርአንድ ጀሪካን ለሊትር 340 ብር ከቆቦ ወደዚያ በጀሪካን በ11ሺ ብር ነው የሚሸጠው በቃ ይሄው በየመንገዱ መኪና የሚባል ነገርየለም፡፡"

 

የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ ትራንስፖርት ሎጂስቲክ መምሪያ ሃላፊአቶ እብራሂም አህመድ በመኪና መናኸሪያው በርካታ ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም በቂ የነዳጅ ዘይት ማግኘት ባለመቻላቸው ተገቢውን ግልጋሎት እየሰጡ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ 

 

"እንደምታየው በጣም በርካታ ህዝብ አለ ያው ተሽከርካሪዎቹ ተሰልፈው ነው የሚቀዱት ብዙ ቦታ ማደያ የለም፤ ከሰሞኑ በተፈጠረ  የነዳጅ እጥረት ምክንያት ብዙ መኪናዎች አይገቡም ብዙ መኪናዎች ነዳጅ አያገኙም፤ ስለማያገኙም ሰው እንደምታየው በርካታ ተጓዥ አለ በዓሉን ምክንያት በማድረግአሁን እኛ ላይ በጣም በርካታ ሰው ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ግን በዚያ ልክ መኪና ማቅረብ አልቻልንም እውነት ለመናገር፡፡"

መጋቢት 9 ቀን 2018 ዓ ም ሰዎች ትራንስፖርት ለማግኘት ተሰልፈውምስል፦ Esayas Gelaw/DW

በተለይም በዞኑ ያሉ የወረዳ  ከተሞች አንዳንዶቹ የነዳጅ ማደያ የሌላቸው በመሆናቸው የነዳጅ እጥረቱ የላቀ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸዋል ይላሉ አቶ ኢብራሂም አህመድ፡፡ 

"ወረዳ ከተሞች ላይ የሚሆነው ምንድን ነው ወረዳ ከተሞች መናኸሪያ ያላቸው አንዳንዶች ማደያ የሌላቸው ስላሉ እነዚያ ላይ አሁን ከዚህ እንደምታየው ተፅዕኖ አለ፡፡"

 

በአማራ ክልል በተፈጠረ የነዳጅ እጥረት ምክንያት በህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ ይነገራል፡፡ በዚህ ዜና ላይ የአማራ ክልል መንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ሃሳብ እንዲሰጡ ስልክ ብንደውልም መልዕክት ብናደርስም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡ 

ኢሳያስ ገላው

ልደት አበበ

ፀሀይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW