1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካን የምርጫ ውጤት አንድምታ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2011

በዩናይትድ ስቴትስ የአንድ ፕሬዝደንት የሥልጣን ዘመን ሲጋመስ ምርጫ ማካሄድ የተለመደ ነው። በዚህ መሠረትም ትናንት በተደረገው ምርጫ ዴሞክራቶች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን አብላጫ ወንበር ሲይዙ፤ ሪፐብሊካን በሴኔቱ የበላይነታቸውን አስጠብቀዋል።

US Midterms 2018

ቀጣዩ ሁለት ዓመት ለትራምፕ አዳጋች ይመስላል

This browser does not support the audio element.

ምንም እንኳን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ውጤቱን «ከፍተኛ ስኬት» ቢሉትም በቀሪ የአስተዳደር እና የሥልጣን ዘመናቸው ጠንካራ ፈተናዎች ከፊታቸው መደቀኑን እንደሚያመላክት ብዙዎች ይስማማሉ። በትናንቱ ምርጫ ሴቶች እና አፍሪቃ አሜሪካውያን ወደምክር ቤት ለመግባት ተሳክቶላቸዋል። 
ምርጫው ከመካሄዱ ሳምንታት አስቀድሞ ነበር ተሰሚነት ያላቸው የዴሞክራትም ሆነ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት መራጩ ሕዝብ ወጥቶ ድምፁን እንዲሰጣቸው ሲቀሰቅሱ የሰነበቱት። ትናንት ገና በማለዳው በመላው የአሜሪካን ግዛቶች የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ ለመስጠት የወጣው በሚሊየኖች የሚገመተው መራጭ ረጃጅም ሰልፎችም የፖለቲከኞቹ ውትወታ መና አለመቅረቱን የሚያሳይ ነው ተብሎለታል። መራጮቹም ለ435ቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይመጥነናል ላሉት፤ እንዲሁም በሴኔቱ 100 መቀመጫዎች ለ35ቱ መንበሮች ድምፃቸውን ሰጥተዋል። 
ውጤቱ ደግሞ ሪፐብሊካኑ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን «አሜሪካ ትቅደም» አጀንዳ ማጠናከር የሚያስችል አቅም በሴኔቱ ላይ እንዲያገኙ፤ ዴሞክራቶች ደግሞ የትራምፕ አንዳንድ ቀፍዳጅ ዕቅዶች እንደልባቸው ሥራ ላይ እንዳይውሉ መገዳደር የሚያስችል ጉልበት በሚይዘው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ወንበር እንዲቆጣጠሩ አድርጓል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ 218 ሲሆን ዴሞክራቶች 219 ወንበር ይዘዋል፤ ሪፐብሊካኑ ደግሞ 193ቱን አግኝተዋል። በሴኔቱ ደግሞ 51 ድምጽ ያገኘ ባለ አብላጫ ድምፅ ሲሆን ሪፐብሊካኖች ይህ ተሳክቶላቸዋል። ዴሞክራቱ 43 አላቸው። 
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድምፅ ያላቸው ዴሞክራቶች በቀሪው የዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ወሳኝ የሆኑ ኮሚቴዎችን ይመራሉ፤ ፕሬዝዳንቱ የሚያከናውኑትን ማንኛውም የንግድ ስምምነት እና የውስጥ አሠራር የመመርመር ሥልጣን ያገኛሉ፤ ይህ ደግሞ በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከትራምፕ ወገን  ከሩሲያ ጋር የተባበረው ማን መሆኑን መመርመርን ሁሉ ይጨምራል። ከምርጫው በኋላ «በአሜሪካን አዲስ ቀን መጣ» ያሉት ዴሞክራቷ ናንሲ ፔሎሲም የምክር ቤት አፈ ጉባኤነታቸውን መልሰው የማግኘት ህልም አላቸው። በተቃራኒው ሪፐብሊካን ፓርቲያቸው በምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ያጣዉ የዶናልድ ትራምፕ ትኩረታቸውን ሁሉ በሴኔቱ ድል ላይ አድርገዋል። ትራምፕ በውጤቱ የተደሰቱ ይምሰሉ እንጂ የአሶሲየትድ ፕሬሱ ስቲቭ ፒፕልስ እንደሚለው ቀሪውን ሁለት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም። 
«ይህ ትልቅ ነገር ነው። በቀጣይ ሁለት ዓመታት በትራምፕ የፕሬዝደንትነት ዘመን ዋሽንግተን ላይ የኃይል ሚዛኑ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል። ከምንም በላይ ዴሞክራቶች ሕግን ተጠቅመው ለረዥም ዓመታት ይፈልጉት የነበረውን የዶናልድ ትራምፕን የግብር መረጃዎች በትዕዛዝ የመመርመር ሥልጣን ይሰጣቸዋል። ዴሞክራቶች በዋናነት የትራምፕን አጀንዳዎች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ማድረግ ይችላሉ። ትራምፕ ግብር ላይ የጤና መድህን ላይ ምናልባት፤ ስደተኞችን በሚመለከት ማድረግ የሚፈልጉት ነገር አለ። ግንብ መገንባት ፈልገዋል። ሌላው ቀርቶ ሪፐብሊካኖች አብላጫ መቀመጫ ይዘው እንኳን ግንቡን መገንባት አስቸግሯቸዋል። ይህ ደግሞ የባሰ ከዴሞክራቶች ጋር በጣም አዳጋች እንደሚሆንባቸው ግልፅ ነው።»
ምንም እንኳን ውጤቱ ለዴሞክራቶች የተሻለ አጋጣሚ ነበር ቢባልም እንዳሰቡት ግን ሰማያዊው ሰንደቃቸውን በሙላት ከፍ ያደረገ አለመሆኑንም አብሮ ያነሳል የፖለቲካ ተንታኙ።  በሌላ በኩል የትናንቱ የፕሬዝደንት የሥልጣን ዘመን አጋማሽ ምርጫ በርከት ያሉ ሴቶችን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስገባ አጋጣሚ መሆኑም ነው የታየው። ሂጃብ የምትለብስ አንድ የሙስሊም ሴትንም አካትቷል። ስቲቭ ፒፕልስ ታሪካዊ ስብጥር የታየበት ምርጫ ይለዋል።
«በዴሞክራቶቹ ወገን በእርግጥም ታሪካዊ ስብጥር የታየበት ምርጫ ነው። የተደባለቀ ውጤትን ነው ያየነው። ሴቶች፤ ታሪካዊ በሚባል ደረጃ የሴቶች ቁጥር በምክር ቤቱ ያሸነፉ ሴቶች ሪከርድ ሰብሯል። ይህ ደግሞ ለብዙ ሰዎች ትልቅ ነገር ነው።» 
ካሸነፉት ሴቶች መካከል ትውልደ ሶማሊያዊ አሜሪካዊት ኢልሀን ኦማር ሚኒሶታ ላይ ዴሞክራቶችን ወክላ ተሳክቶላታል። ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላም ደጋፊዎቿ ፊት ቆማ እንዲህ አለች፤
«ለምክር ቤት እንደተመረጠች የእናንተ ወኪል ዛሬ ምሽት ፊታችሁ ቆሜያለሁ፤ ከስሜ ጀርባ ብዙ ኃይል አለኝ። በምክር ቤት ግዛታችንን የምትወክል የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት፤ በምክር ቤት እናንተን ወክላ ሂጃብ የምትለብስ የመጀመሪያ ሴት፤ የመጀመሪያዋ ለምክር ቤት የተመረጠች ስደተኛ እንዲሁም ለምክር ቤት ከተመረጡ ሙስሊም ሴቶች አንዷ።»
የ36 ዓመቷ ኢልሀን ኦማር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከተሰደዱ 20 ዓመታት አልፈዋል። በዚህ ምርጫ ሌላ አፍሪቃዊም ከኮሎራዶ ወደ ምክር ቤቱ ዘልቋል። ትውልደ ኤርትራዊው ዮሴፍ ንጉሤ ኮሎራዶ ላይ ሪፐብሊካኑን ጄርድ ፖሊስን ባገኘው 64 በመቶ ድምጽ በልጠው ነው ወደ ምክር ቤት መግባታቸውን ያረጋገጡት። ወላጆቻቸው የዛሬ 35 ዓመት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የገቡት የኮሎራዶ የምክር ቤት አባል አሁን ወደዚያ የተሰደዱ ቢሆን ምን ያህል አስቸጋሪ ሕይወት ይገጥማቸው እንደነበረ በመግለፅ፤ በአሜሪካ ዴሞክራሲን ለመገንባት ከፍተኛ ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል። ሚችጋን ደግሞ በትውልድ ከፍልስጤም የሆነችውን አሜሪካዊቷ ረሺዳ ጣሊብን ለምክር ቤት አብቅቷል። 
የምርጫው ውጤት ከዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ጋር ችግር ውስጥ የገቡ ሃገራት ላይ ተስፋ ያሳደረ መስሏል። የአውሮጳ ኅብረት ዴሞክራቶች ያገኙትን ውጤት አወድሷል። ሩሲያ የምርጫ ውጤቱ ለትራምፕ ቀሪ የሥልጣን ዘመናቸውን አዳጋች እንደሚያደርግባቸው ብትገልፅም በሚኖራት ግንኙነት ደረጃ ግን ለውጥ እንደማይኖር አመልክታለች። ጀርመን በበኩሏ በሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም ባይ ናት። 

ኢልሀን ኦማር ምስል picture-alliance/abaca/Minneapolis Star Tribune/M. Vancleave
ዶናልድ ትራምፕምስል picture-alliance/dpa/AP/E. Vucci
ናንሲ ፔሎሲምስል Reuters/A. Drago

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW