በአሜሪካ እና በቻይና የንግድ ጦርነት ማን ያሸንፋል?
ረቡዕ፣ ግንቦት 7 2011ቻይና እና አሜሪካ ከፍሬ አልባ ድርድር እና ከእንካ ሰላንቲያ በኋላ የጀመሩት እሰጥ አገባ አሁን ወደ ሙሉ የንግድ ጦርነት የተሸጋገረ ይመስላል። ቻይና ከመጪው ግንቦት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ 60 ቢሊዮን ዶላር በሚያወጡ የአሜሪካን ሸቀጦች ላይ የምታስከፍለውን ታሪፍ ከፍ ማድረጓን አስታውቃለች። የሁለቱን አገራት ውጥረት ያባባሰው ውሳኔ የተደመጠው ከአራት ቀናት በፊት አሜሪካ 200 ቢሊዮን ዶላር በሚያወጡ የቻይና ሸቀጦች ላይ የምታስከፍለውን ታሪፍ ከፍ ካደረገች በኋላ ነበር።
የሁለቱ ልዕለ ኃያላን ውዝግብ ከድንበሮቻቸው ተሻግሮ በአውሮፓ እና በእስያ የአክሲዮን ገበያዎች ጫና አሳድሯል። የጃፓን እና የጀርመንን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች የአክሲዮን ገበያዎች ከወትሮው በተለየ መዋዠቅ የጀመሩት ከዋሽንግተን ዲሲ እና ከቤጂንግ ከተደመጡት ውሳኔዎች በኋላ ነበር።
የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የአውሮጳ ኅብረትም ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነው ፍጥጫ ሥጋት ላይ ናቸው። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዤን ክላውድ ዩንከር ባለፈው ሳምንት በብራስልስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ሁለቱ ልዕለ-ኃያላን እንደ አዲስ የገቡበት የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትንቅንቅ የመላው ዓለምን የመዋዕለ-ንዋይ ሥራ አደጋ ላይ ጥሏል። "ባለወረቶች ይኸ ውጥረት በቶሎ ይፈታል የሚል ዕምነት የላቸውም" ያሉት ዩንከር ድንበር ተሻጋሪ መዋዕለ-ንዋይ መዳከሙን ተናግረዋል። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክሪስቲን ላጋርድ እንደ ዩንከር ሁሉ የቻይና እና የአሜሪካ እሰጥ አገባ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጌንግ ሹዋንግ ባለፈው ሰኞ በሰጡት ማብራሪያ አገራቸው ወደማትፈልገው ውዝግብ ለመግባት የተገደደችው ከዚህ ቀደም የተደረሰ ስምምነት በመጣሱ ነው ሲሉ ወቅሰዋል። ቃል-አቀባዩ "ባለፈው ግንቦት ወር ቻይና እና አሜሪካ በኤኮኖሚያዊ እና የንግድ ልውውጥ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰው የጋራ የአቋም መግለጫ ይፋ አድርገዋል። ይሁን እና ከጥቂት ቀናት በኋላ ቻይና ከአሜሪካ በምትሸምታቸው ሸቀጦች ላይ የተደረሰውን ስምምነት ጥለው በመውጣት የታሪፍ ጭማሪ ተደርጓል። ስለዚህ ቻይና ከቃል ኪዳኑ አፈንግጣለች ሊባል አይችልም" ሲሉ ተጠያቂነቱን ከአትላንቲክ ባሻገር ወዳለችው አሜሪካ ወርውረዋል።
የቻይና እና የአሜሪካ እሰጥ አገባ እንዲህ በድንገት ከሰማይ የወረደ ዱብ እዳ አይደለም። ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊትም አገራቸው ከቻይና ያላት የንግድ ልውውጥ የተዛባ ነው የሚል የከረረ ትችት በማሰማት ይታወቃሉ። ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ባለፈው አንድ አመት አገራቸው በቻይና ምርቶች ላይ አራት ጊዜ የታሪፍ ጭማሪ አድርጋለች። ጎን ለጎን የሚደረገው ድርድር ባይቋረጥም ቻይናም በአጸፋ እርምጃ ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፋለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደሚሉት ግን በሁለቱ አገሮች መካከል በተቀሰቀሰው እሰጥ አገባ አገራቸው ከዚህ ቀደም ያላገኘችውን ጥቅም አትርፋለች። ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት በስቲያ ከሐንጋሪው ጠቅላይ ምኒስትር ቪክቶር ኦርባን ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ እግረ መንገዳቸውን ባነሱት ርዕሰ-ጉዳይ ሲናገሩ አሜሪካ በቻይና ላይ በጣለችው የታሪፍ ጭማሪ በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ማግኘቷን ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "በአሁኑ ወቅት በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያገኘን ነው። በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ በታሪፍ መልክ እያስከፈልናቸው እንገኛለን። እውነቱን ለመናገር እኔ እስክመረጥ ድረስ ከቻይናም ይሁን ከማንም አስር ሳንቲም እንኳ አስከፍለናቸው አናውቅም። አሁን ግን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያገኘን ነው። ይህ እጅግ አዎንታዊ እርምጃ ነው። የተወሰነ የአጸፋ እርምጃ ሊኖር ይችላል። ግን እጅግ የተወሰነ ነው የሚሆነው። ከምናገኘው በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የተወሰነው ለገበሬዎቻችን ይውላል። ምክንያቱም ቻይና የምትወስደው የበቀል እርምጃ በተወሰነ ደረጃ በገበሬዎቻችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል" ብለው ነበር።
መቀመጫውን በሖንግ ኮንግ ያደረገው እና በመዋዕለ-ንዋይ አማካሪነቱ የሚታወቀው ጂዎ ሴኩሪቲስ (Geo Securities) የተባለ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ፍራንሲስ ሉን ዓለምን ላሰጋው የንግድ ጦርነት ተጠያቂዋ አሜሪካ ናት የሚል አቋም አላቸው። ውዝግቡ ከቀጠለ ጫናው ሊበረታ ይችላል የሚሉት ፍራንሲስ ሉን ኃላፊነቱን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሊወስዱ ይገባል ባይ ናቸው። ሉን "ቻይና የንግድ ጦርነቱን እንደማትሻ በተደጋጋሚ ግልፅ አድርጋለች። ነገር ግን ቻይና የንግድ ጦርነት አትፈራም። መቋቋም የማይቻል ኃይል እና የማይንቀሳቀስ እቃ ከጭንቅላት ሲጋጭ መጨረሻው ለሁለቱም ኪሳራ ይሆናል። በንግድ ጦርነቱ ሁለቱም ይጎዳሉ፤ ማንም አያተርፍም" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት የንግድ ፖሊሲ የማዘጋጀት ኃላፊነት የተሰጠው የንግድ ተወካዮች ቢሮ መረጃ እንደሚጠቁመው በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ.ም. ቻይና እና አሜሪካ 737.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የንግድ እና የአገልግሎት ግብይት ነበራቸው። በአመቱ አሜሪካ 179.3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ለቻይና ሸጣለች። ከቻይና የሸመተቻቸው ሸቀጦች እና ግልጋሎቶች በአንፃሩ 557.9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ናቸው። በዚሁ መረጃ መሰረት በባለፈው አመት የንግድ ልውውጥ አሜሪካ ከቻይና አኳያ የ378.6 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አለባት።
የምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎች አሜሪካ በቻይና ላይ የጣለችውን ታሪፍ የሚከፍሉት መልሰው የአሜሪካ ኩባንያዎች እና ሸማቾች መሆናቸውን ይናገራሉ። ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተፃራሪ የአስተዳደራቸው ባለሥልጣናት ገፋ ያለ ጥያቄ ሲቀርብላቸው በእርግጥ ይኸን አይሸሽጉም። የአሜሪካ ብሔራዊ የኤኮኖሚ ምክር ቤት ዳይሬክተር ላሪ ኩድሎው ያደረጉትም ይንኑ ነው። ኩድሎው በፎክስ ቴሌቭዥን ቀርበው የአሜሪካ ውሳኔ በአሜሪካ ኩባንያዎች እና ሸማቾች ላይ ጫና ቢያሳድርም በቻይና ምጣኔ ሐብት ላይ እንደሚከፋ ተከራክረዋል።
የአሜሪካ-ቻይና የንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጃኮብ ፓርከር ሁለቱ አገሮች አንዱ በሌላው ላይ በተደጋጋሚ የሚያደርጓቸው የታሪፍ ጭማሪዎች የንግድ ልውውጡን እንደሚገዳ አይሸሽጉም። እጅግ ያሳሰባቸው ግን ውሳኔዎቹ ድንገተኛ መሆናቸው ጭምር ነው። ፓርከር "ባለፈው ሳምንት ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአጭር መልዕክት የተደመጠው ውሳኔ አብዛኞቹ አባል ኩባንያዎች መቼ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚደረግ መረጃ እንደማይኖራቸው ማረጋገጫ ሆኗቸዋል። የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ የእኛ ምክር ቤት አባል የሆኑ ኩባንያዎች በቻይና የሚገጥማቸውን ሥጋት ጨምሮታል። ይኸ ደግሞ በደንበኞቻቸው ዘንድ ጭምር ጫና አሳድሯል። በዚህ ምክንያት የእኛ ኩባንያዎች በአውሮፓ፤ በጃፓን እና በቻይና ሥራዎቻቸውን እያጡ ነው። ኩባንያዎቹ በዓለም አቀፍ የአክሲዮን ገበያ ያላቸው ዋጋ አሽቆልቁሏል። ከዚህ ማገገም ደግሞ እጅግ ፈታኝ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።
የሁለቱም አገራት ነጋዴዎች፣ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች እና ጣጣው ያሰጋው የዓለም ማኅበረሰብ ምን ዓልባት ይኸ ፍጥጫ በድርድር ሊፈታ ይችላል የሚል ተስፋ አሳድሯል። የሁለቱ አገሮች ተወካዮች ድርድር ያለ ውጤት የተበተነው ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ ጫን ያለ ታሪፍ መጣሏን ባሳወቀችበት ዕለት ነው። የቻይና ታሪፍ የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች፣ የኤሌክትሪኒክ መሳሪዎች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የምግብ ውጤቶችን ይመለከታል። ሲሲቲቪ የተባለው የቻይና መንግሥት የቴሌቭዥን ጣቢያ ባለፈው ሰኞ ከረር ባለ ድምፀት የፕሬዝዳንት ዢ ዢንፒንግ አገር የንግድ ጦርነት እንደማትፈራ አስታውቋል። የቴሌቭዥን ጣቢያው የመንግሥቱን አቋም በሚያንጸባርቅበት ርዕሰ-አንቀፅ እንዳለው ቻይና ለድርድር በሯ ክፍት ነው። ጥቃት ከተፈጸመባት ግን እስከ ፍፃሜው ትፋለማለች። የቻይና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጌንግ ሹዋንግም ቢሆኑ "ከአሜሪካ ወገን ጉዳዩን በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ቻይና ጥቅሟን ለማስጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ዝቅ አድርገው አይመለከቱም ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ቻይና ከዚህ ቀደምም ወደ የንግድ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላት ብታረጋግጥም የምትፈራው ነገር ግን የለም። ሰዎች በእኛ ቤት ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ መልሰን እንታገላቸዋለን" ሲሉ አገራቸው እንደማታፈገፍግ በአፅንዖት ገልጸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አገራቸው ከቻይና ከገጠማት የአጸፋ ምላሽ በኋላ 300 ቢሊዮን ዶላር በሚያወጡ ሌሎች የቻይና ምርቶች ላይ የሚከፈለውን ታሪፍ ከፍ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችው ታሪፍ እስከ 25 በመቶ እንደሚደርስ በአገሪቱ ምክር ቤት የታሪፍ ፖሊሲ ኮሚሽን አስታውቋል።
የቻይና የታሪፍ ጭማሪ ተግባራዊ ለመሆን ሁለት ሳምንት ገደማ ይጠብቃል። በቀሪዎቹ ቀናት አገሮቹ ልዩነታቸውን በድርድር መፍታት ስለመቻላቸው እስካሁን ማንም እርግጠኛ አይደለም። የምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎች የዓለምን ኤኮኖሚ የተቆጣጠሩት ሁለቱ አገሮች የሚገቡበት የንግድ ጦርነት ዳፋው ለዓለም እንደሚተርፍ በተደጋጋሚ እያስጠነቀቁ ይገኛሉ። በተለይ የንግድ ጦርነቱ ካየለ የዓለም ገበያ የነዳጅ ዘይትን ለመሳሰሉ ሸቀጦች ያለው ፍላጎት ሊቀዛቀዝ ይችላል የሚለው ዋንኛው ነው።
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ