1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ በኢትዮጵያ ምን አሉ?

ቅዳሜ፣ መስከረም 10 2018

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን ቀጠና “ሰላም ለማጠናከር ባላት ቁርጠኝነት” እንደተበረታቱ በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ ተናገሩ። ቡሎስ ይኸን ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ወደብ ሊኖራት ይገባል በሚል የሚያራምደው አቋም ውጥረት በፈጠረበት ወቅት ነው።

በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ  ማሳድ ቡሎስ እና ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ
የዶናልድ ትራምፕ አማች የሆኑት ቢሊየነሩ ማሳድ ቡሎስ በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ሆነው የተሾሙት ባለፈው መጋቢት 2017 መገባደጃ ላይ ነበር።ምስል፦ Julia Demaree Nikhinson/AP Photo/picture alliance

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን ቀጠና “ሰላም ለማጠናከር ባላት ቁርጠኝነት” እንደተበረታቱ በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ ተናገሩ። ቡሎስ ይኸን ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል ወደብ ሊኖራት ይገባል በሚል የሚያራምደው አቋም በቀጠናው ውጥረት በፈጠረበት ወቅት ነው። 

ቡሎስ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኩል በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በአፍሪካ ቀንድ “ጸጥታ እና መረጋጋትን ማጠናከር” ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ስቴትስ “ቅድሚያ የሚሰጡት” ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።  

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የኢትዮጵያ እና የጎረቤቶቿ “ሰላማዊ ግንኙነት” የሚኖረው “ጠቀሜታ” ላይ መነጋገራቸውን ማሳድ ቡሎስ ገልጸዋል። 

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የአረብ እና መካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ጭምር የሆኑት ቡሎስ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተጨማሪ ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማሕሙድ አሊ ይሱፍ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰውን አግኝተዋል። 

ከ2013 እስከ 2015 የተካሔደው ጦርነት “በወቅቱ በዓለም ትልቁ ግጭት” እንደነበር ያስታወሱት ሞሊ ፊ በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትርነታቸው ሲሰናበቱ “የትግራይን ጦርነት ለማስቆም በሠራንው ሥራ በጣም እኮራለሁ” ብለው ነበር። ምስል፦ piemags/IMAGO

ቡሎስ በከፍተኛ አማካሪነት የሚያገለግሉት በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ እና በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 የተካሔደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት እንዲገታ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

በድርድሩ ወቅት በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት ሞሊ ፊ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ ሲመለሱ ከኃላፊነታቸው ተሰናብተዋል። በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሥር የሚገኘው የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮን የሚመሩት ጆናታን ፕራት ናቸው። 

የዶናልድ ትራምፕ አማች የሆኑት ቢሊየነሩ ማሳድ ቡሎስ በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ሆነው የተሾሙት ባለፈው መጋቢት 2017 መገባደጃ ላይ ነበር። ባለፉት ወራት በከፍተኛ አማካሪነታቸው ወደ ኮንጎ፣ ርዋንዳ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳን የመሳሰሉ ሀገራት ተጉዘዋል። ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዙ ግን የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው። 

አርታዒ ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW