በአሜሪካ የሚደገፈው የጋዛ የሰላም እቅድ እና አንድምታው
ማክሰኞ፣ መስከረም 20 2018
በአሜሪካ የሚደገፈው የጋዛ የሰላም እቅድ
በአሜሪካ የሚደገፈውና ጋዛ ውስጥ ሰላም ለማስፈን ያለመው ባለ 20 ነጥብ የሰላም ሀሳብ ከሁለቱም ወገኖች ጥንቃቄ የተሞላበት ምላሽን ነው ያስተናገደው። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እቅዱን የተቀበሉት ቅድመ ሁኔታወችን አስቀምጠው ነው። እነዚሁ ቅድመ ሁኔታወች ደግሞ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በጋዛ ጠንካራ የደህንነትና የጸጥታ ማስከበር ተልዕኮውን የሚቀጥል መሆኑና ለፍልስጤም አስተዳደር የሉዓላዊ ሃገረ መንግስትነት እውቅና የሚሰጥ ማንኛውንም ቅድመ ሁኔታም ሆነ አንቀጽ የስምምነቱ አካል መሆን አለመቻሉ ነው።
ሃማስ ሃሳቡን ይቀበለው ይኾን?
ሃማስ በበኩሉ እቅዱን በግብፅ እና በኳታር አሸማጋይነት እየገመገመው እንደሆነ ተገልጿል። ያም ሆኖ የአመራር አባላቱ ትጥቅ መፍታትን እና ከፍልስጤም አስተዳደርአካልነት መውጣታቸውን አጥብቀው የሚቃወሙ መሆናቸው ይታወቃል። እነዚህ ሁለት ቅድመ ሁኔታወች ደግሞ የስምምነቱ ዋና መስፈርቶች ናቸው። የሰላም እቅዱ ታጋቾችን መልቀቅ፣ መጠነ ሰፊ የእስረኞች ልውውጥን ማድረግ፣ እስራኤል ደረጃ በደረጃ ጋዛን እየለቀቀች የምትወጣበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ተግባራዊ ለማድረግ የ72 ሰአታትን ገደብ አስቀምጧል።
ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጠው ትርጉም
ይሄው የሰላም ሃሳብ ውጤታማ መሆን አለመሆኑን ጥርጥር ውስጥ የሚጨምረው ደግሞ በጋዛው ጦርነት እና ሁለቱም ወገኖች የተናገሩትን በመፈጸም ረገድ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ መታመን አለመቻላቸው እና ሶስተኛ ገለልተኛ ተቋም የቀረቡትን የሰላም መስፈርቶች አግባባዊ ተፈጻሚነት ማረጋገጥ የሚችልበት ሁኔት ኣለመመቻቸቱ እንደሆነ ተገልጿል። ሌላው ቁልፍ ድክመት ደግሞ ጠንካራ የትግበራ የጊዜ ሰሌዳ አለመኖር ነው። አካባቢውን ለቆ ለመውጣት፣ ትጥቅ ለማስፈታት ወይም ለአስተዳደር ርክክብ ግልጽ የሆነ ቀነ-ገደብ ከሌለ የሰላም ሃሳቡ ያለፉትን የተኩስ አቁም ሙከራዎችን ባዳከሙ ወጥመዶች ውስጥ ዳግም የመውደቅ እድል አለው።
ዘላቂ መፍትሔ ያመጣ ይኾን?
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላም እቅዱ የተሰጠው ምላሽ ተስፋና ጥርጣሬን የያዘ ነው። የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጦርነቱን የሚያቆም ማንኛውንም ተነሳሽነት በደስታ ይቀበላሉ። ነገር ግን ያለ ፍልስጤማውያን ፈቃድ በላያቸው ላይ የሚጫን ማንኛውንም የአስተዳደር መዋቅር ይቃወማሉ። ሌላው መሰረታዊ ስጋት ይሄው ሃሳብ እስከዛሬ ሲቀነቀን የኖረውን የሁለት ሃገራት መፍትሄ ተፈጻሚ አድርጎ፣ ፍልስጤም እንደ ሃገር የምትቆምበትን ህሳብ ሙሉ በሙሉ ያላካተተ መሆኑ የአካባቢውን ችግር በዘላቂነት የመፍታት ተስፋውን አጥብቦታል።
አበበ ፈለቀ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ