1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአራት ክልሎች ቀሪ ምርጫ ሊደረግ ነው

ዓርብ፣ የካቲት 22 2016

በተለይ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ፣ የተፈናቀለ ሕዝብ የሚገኝበት ቢሆንም ክልሉ አሁን ድረስ ባልተመረጠ ምክር ቤት የሚተዳደር በመሆኑ ምርጫው ይደረግ የሚለውን ሲጠይቁት የቆዩት ጉዳይ መሆኑን በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጠቅሰዋል።

ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ እንዳሉት በአራቱ ክልልሎች ምርጫ እንዲደረግ የተወሰነዉ የየአካባቢዎቹ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ በመሆኑ ነዉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላት ወርቅ ሐይሉምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

በአራት ክልሎች ቀሪ ምርጫ ሊደረግ ነው

This browser does not support the audio element.

 

ኢትዮጵያ ዉስጥ በ2013 በተደረገዉ 6ኛው ዙር ብሔራዊ  ምርጫ ወቅት በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ምርጫ ባልተካሄደባቸው አራት የምርጫ ክልሎች በመጪዉ ሰኔ 6 ቀን 2016 ምርጫ ለማድረግ ማቀዱን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።ቦርዱ እንዳስታወቀዉ ምርጫዉ የሚደረገዉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ነዉ።በምርጫዉ ዘጠኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 26 የክልል ምክር ቤቶች አባላት ይመረጣሉ።በቦርዱ ዕቅድ መሰረት ሰኔ 6 የሚሰጠዉ ድምፅ አጠቃላይ ዉጤት ሰኔ 16 2016 በይፋ ይገለጣል።

ምርጫው የፀጥታ ችግር በሌለባቸው ቦታዎች ይደረጋል

 

ከሦስት ዓመታት በፊት በተከናወነው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ በፀጥታ መናጋትና በሰላም እጦት ምክንያት ምርጫ ሳይደረግባቸው በቀሩ፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁናቴ ምርጫ ለማስፈፀም የፀጥታ ችግር የሌላለባቸው በተባሉ አራት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ከአራት ወራት በኋላ ምርጫ እንደሚደረግ ነው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን ጊዜያዊ የምርጫ ማስፈፀሚያ መርሐ ግብር ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ድርጅቶች ሲያሳውቅ ዛሬ ይፋ ያደረገው።

ምርጫውን "ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት ወደ ሰኔ ስድስት ለመግፋት ተገደናል" ያሉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ይህንኑ ሥራ ለማስፈፀም የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወናቸውን ገልፀዋል።
ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በተጠቀሱት ክልሎች አሁን ምርጫ ለማድረግ የሰላም ችግር - "በየቦታው ድንገት የሚፈነዱ የፀጥታ ችግሮች" መኖሩ ተጠቅሶ ጥያቄ የቀረበላቸው ሰብሳቢዋ ቦርዱ የፀጥታ ሁኔታዎችን ሳያረጋግጥ ወደዚህ ሥራ አለመግባቱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪዉ ሰኔ ሊደረግ ስለታቀደዉ ምርጫ ያወጣዉ መርሐ-ግብር ምስል Solomon Muchie/DW

ቦርዱ ለሥራው የጠየቀው በጀት እስካሁን አልተለቀቀም

 

የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የሚከናወንባቸው 1112 መደበኛ የምርጫ ጣቢያዎች እና 34 የተፈናቃይ የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙ ቦርዱ አስታውቋል። በተለይ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ፣ የተፈናቀለ ሕዝብ የሚገኝበት ቢሆንም ክልሉ አሁን ድረስ ባልተመረጠ ምክር ቤት የሚተዳደር በመሆኑ ምርጫው ይደረግ የሚለውን ሲጠይቁት የቆዩት ጉዳይ መሆኑን በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጠቅሰዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ሥራ ለማስፈፀም መስከረም ላይ የጠየቀው በጀት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢፀድቅም የገንዘብ ሚኒስቴር ገንዘቡን እስካሁን እንዳልለቀቀላቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገልፀዋል። ፓርቲዎቹም ይህ አሳሳቢ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያልተደረገው ምርጫ አሁንም አይደረግም

 

በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ፤ ምርጫው አሁን ይደረግባቸዋል ከተባሉት አራት ክልሎች በተጨማሪ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችም ምርጫ ያልተደረገባቸው ሥፍራዎች ጥቂት አይዱሉም።የትግራይ ክልልም የራሱ ሌላ መልክ ቢኖረውም ምርጫ አልተደረገበትም። ሰኔ ላይ ይደረጋል ተብሎ በተነገረው ቀሪ እና ድጋሚ ጠቅላላ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዲስ የመራጮች ምዝገባ የሚደረግ ሲሆን በሌሎቹ በስድስተኛው ምርጫ ለመምረጥ የተመዘገቡት ብቻ ድምፅ እንደሚሰጡ ተገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW