በአርሲ የተፈጸመው ግድያ እና የቀረበው አቤቱታ
ረቡዕ፣ ግንቦት 26 2018
በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ሀገረ ስብከት በአስኮ ወረዳ በሺርካ ወረዳና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹእ አቡነ ማትያስ ፦ «የመንግስት የፀጥታ አካላት መዋቅሩ ይህንን የጥቃት ሰንሰለት በማስቆም ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ ይገባል» ሲሉ አሳሰቡ ። በአካባቢው 13 ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያኖች መገደላቸውን ሀገር ስብከቱ ቀደም ሲል አመልክቷል ። ከግድያው ባሻገር በሦስት ቀበሌዎች ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱን የዐይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ግንቦት 23 ቀን 2018 ከንጋቱ የጀመረው የታጣቂዎች ጥቃት የንጹሃን ሰላማዊ ዜጎች መቅጠፉንና በሦስት ቀበሌዎች ከፍተኛ የንብረት ውድመት ማስከተሉን የዐይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱ ሃይማኖታዊ ተቋም ላይም ያነጣጠረ ነው የሚሉት ከእሁዱ ጥቃት የተረፉ የአይን እማኞች ከ100 ዓመት እድሜ በላይ ያስቆጠረው ታሪካዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲየን በእሳት መጋየትን እንደ አንዱ ማሳያ አቅርበውታል፡፡
"እሁድ ከማለዳ እስከ እኩለ ቀን የተኩስ እሩምታ ውስጥ ነው የዋልነው” ተጎጂዎች
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ተማጽነው አስተያየታቸውን ብቻ ያጋሩን የዐይን እማኝ ቢያንስ ለዘጠኝ ንጹሃን ዜጎች መቀጠፍ ምክንያት የሆነው የታጣቂዎች ጥቃት እሁድ ግንቦት 23 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. ከማለዳው 11፡30 ግድም መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ "የመንግስት ታጣቂዎች እና ህዝቡም ስጋት ስለነበር ከተማው ይጠበቅ ነበር” ያሉት የአይን እማኙ እሁድ ማለዳውን በአከባቢው ታጥቀው መንግስትን የሚወጉት ታጣቂዎቹ በከባባድ መሳሪያዎች ጭምር የታገዘ የተኩስ ናዳ አውርደዋል ነው ያሉት፡፡
በዚሁ ታጣቂዎች ከፈቱ በተባለውም ጥቃት ሁለት የመንግስት ጸጥታ አካላት እና ዘጠኝ ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውንም የአይን እማኙ ነዋሪ ገልጸዋል፡፡ "11፡30 ሰዓት ተጀመረው ተኩስ እስከ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ድረስ ከተመዋን የጦር አውድማ አስመስሎትም ነበር” ያሉት የአይን እማኙ፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመትም በእለቱ መከሰቱን ገልጸዋል፡፡ "በዚያ እለት ወደ 150 ከብቶች በታጣቂዎች ተነድቷል” በማለትም ብያንስ ሁለት፣ ሶስት፣ አራትም አምስትም ቢሆን ከብት ያልተዘረፈ አልነበረም በማለትም ጉዳቱ ሁሉንም የማህበረሰብ አባላት ያዳረሰ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በእለቱ የተገኘውን አስከሬን በማንሳትና ልጆቻቸውን በማንሳት ከአከባቢው መሸሽ የአከባቢው ማህበረሰብ እጣ ፈንታ ነበር ነው ያሉት፡፡
የታጣቂዎች ጥቃት ለዓመታት መራዘም ያሳደረው ተጽእኖ
በአከባቢው ንጹሃን ሰላማዊ ዜጎች ላይ አነጣጥሮ በተደጋጋሚ የሚፈጸም የታጣቂዎች ጥቃቱዓመታትን እያስቆረጠ ነው ያሉት በጥቃቱ ልጃቸውን ያጡት ሌላው አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ነዋሪና ተጎጂ እንደሚሉትም፤ "አብዛኛው የአከባቢ ህዝብ ከዛሬ ነገ ሰላም መጣል የሚለውን ተስፋ እያደረገ ከወረዳው ቆላማ አከባቢዎች ወደ ከተማው ከፍ እያለ መሸሽ ከጀመረ አምስት አመት ሆኖታል”፡፡ በእሁድ ጠዋቱ የአሰኮ ወረዳ ብያንስ አስር ንጹሃን ሰዎች መሞታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በሃይማኖት ተቋም እና ንጹሃን ነዋሪዎች ላይ የሚያነጣጥረው ጥቃት
እሁድ ግንቦት 23 የተጀመረው የታጣቂዎች ጥቃት በማግስቱም ግንቦት 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. ቀጥሎ ከ100 አመት በላይ ዕድሜ የነበረው ጠለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን ጨምሮ ወደ 200 የነዋሪዎች ቤቶች በቃጠሎ ማውደሙንም ተጎጂዎቹ በአስተያየታቸው አክለው ተናግረዋል፡፡
"ታጣቂዎቹ ያው እሁድ ማታውን ተመልሰው ገቡበት ሰኞ ለታ በቃ ሙሉ ቃጠሎ ነው የተጀመረው” ያሉት አንደኛው የአይን እማኝ አስተያየት ሰጪ፤ ቤተክርስቲያኑ ላይ ሰኞ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ግድም እሳት ስለቀቅበት መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጠለታ ጨፋ፤ ባቲ እና ካራፈኒሳ ቀበለያት ከ200 በላይ የማህበረሰቡ ቤቶች በእሳት ጋይቷል ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪም፤ በጥቃት አድራሾቹ ታጣቂች ቤተክርስቲን ተሰብሮ ከተዘረፈ በኋላ በእሳት መጋየቱንም ነው ያስታወቁት፡፡ "የሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ እና ሰንበተ ቤቶችም አጠቃላይ በእሳት ጋይተዋል” በማለትም ማህበረሰቡ ልጆቹን ይዘው ከአከባቢው እንደሸሸም ነው የገለጹት፡፡
ጉዳቱን ለማስቀረት የፀጥታ አካላት ጥረት
በእለቱ ለጥበቃ አከባቢው ላይ የነበረው የመንግስት ታጣቂ በቁጥር ውስን ነበሩ ያሉት የአይን እማኝ የአከባቢው ማህበረሰቡ፤ በሸማቂዎቹ በተከፈተባቸው ጥቃት ሕይወታቸውን የሰውም ስለመኖራቸው ተገልጿል፡፡ "በአከባቢው የነበሩ የመንግስት ኃይል ውስን ሲሆን ታጣቂዎቹ ከነጀለው ወደ አራት ሺህ የሚጠጋ ነው” በማለት ታጣቂዎቹ እራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብለው እንደሚጠሩ መስማታቸውንም የአይን እማኙ ገልጸዋል፡፡
በእሁድ ያላበቃው የታጣቂዎቹ ጥቃት ሰኞም ቀጥሎ በቆየበት አሰኮ ወረዳ ጠለታ ጨፋ ቀበሌ አከባቢ ላይ ወድቀው እስካሁን አስከሬናቸው ያልተነሳ መኖሩንም የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ወደ 280 አባወራዎች ተፈናቅለው ወደ ሱልጤ ቅድስት ማሪያም እና ኢሬቻ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ሸሽተው ተጠልለው እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡ በጥቃቱ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠረ የሚመስል ጥቃት ቢኖርም በተለይም ከመንግስት ጋር ስማቸው የሚያያዝ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታዮች በታጣቂዎቹ መጠቃታቸውንም የአይን እማኞቹ ገልጸዋል፡፡
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውና ኃላፊነታቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የአሰኮ ወረዳ የአንድ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ፤ "በኛ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ባሁኑ ዘጠኝ ሰው ነው የሞተው” በማለት 280 አባወራ (1500) ያህል ዜጎች ችግር ላይ ወድቀው እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥሪ
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በምእመናን እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት መቀጠሉ "እስከ መቼ” ነው የሚል ሐዘን እንደፈጠረ የገለጹት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአሰኮ፣ ሽርካ፣ ሆንቆሎ-ዋቤ እና በሙኔሳ ወረዳዎች በተፈጸሙት ጥቃቶች "በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የሰማነው በተሰበረ ልብ ነው” ብለዋል። ፓትሪያርኩ ዛሬ እሮብ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫቸው፤ "መከራው እያበቃ ሳይሆን እየሰፋ በመምጣቱ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅና ሰላምን የማስፈን አደራ የተጣለባችሁ የጸጥታ አካላትና በየመዋቅሩ ይህንን የጥቃት ሰንሰለት በማስቆም ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ ይገባል” በማለትም አሳስበዋል።
ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት በዚህ ዘገባ ለማካተት ለአርሲ ዞን ጸጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ጥላሁን ደውሎላቸው ጉዳዩን ሲያስረዳቸው ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡ ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ከድር ደውለንም ስብሰባ ላይ ነን በማለታቸው፤ ለዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ እና ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊም ደውለን ጥረታችን ለዛሬ አልሰመረም፡፡
መንግስታዊውየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአርሲ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በንጹሃን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት የሚመለከተው የመንግስት አካላት እንዲያስቆሙት ከዚህ በፊት ባወጠው ይፋዊ መግለጫ መጠየቁም አይዘነጋም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ