በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሁለት ህጻናት ተገደሉ
እሑድ፣ መጋቢት 21 2017
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ትናንት ምሽት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሁለት ህጻናት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የወረዳው የፀጥታ ኃላፊዎች ለዶቼ ቬለ ገለጹ፡፡ ፖሊስ “በቡድን የተደራጁ” ያላቸው አካላት በወረዳው ዘይሴ ወዘቃ ቀበሌ ግድያውን የፈጸሙት ህጻናቱን በቤት ውስጥ አስገብተው በመቆለፍ በእሳት እንዲቃጠሉ በማድረግ ነው ብሏል ፡፡
ሕይወታቸው ያለፈው የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ የአራት እና የሰባት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ህጻናት መሆናቸውን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኮሜ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ በህጻናቱ ላይ የፈጸሙት ጥቃት “ዘግናኝ ፣ ከሰብአዊነት ያፈነገጠ እና አረመኔያዊ ነው” ያሉት አቶ ኮሜ ጥቃት አድራሾቹ በዛው ቀበሌ በአንድ የወረዳ አመራር መኖሪያ ቤት ላይም የተኩስ ሩምታ ከፍተው እንደነበር ገልጸዋል። በጥቃቱ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም “በመኖሪያ ቤቱ ላይ ግን መለስተኛ ውድመት አድርሰዋል” ብለዋል ፡፡
በአሁኑ ወቅት የጋሞ ዞን እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፀጥታ አካላት በአካባቢው ተሠማርተው የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለመያዝ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ለሐዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ነግረዉታል ፡፡ እስከአሁን ከዋንኛ የድርጊቱ ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ የተያዘ ሲሆን ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እየተሠራ መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
ፎቶ፡ ከአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የተወሰደ
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ