1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ግጭት በአሮሚያ እና ሲዳማ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ሐምሌ 30 2017

በነንሰቦ ወረዳ ገመቹ ቀበሌ ነገዎ ዋቃ እና ገዳ ሰንበቶ የሚባሉ በኮኮሳ ወረዳ አራርሶ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዳንጎ በሚባል ስፍራ መገደላቸውን የተናገሩት የየአከባቢው ነዋሪ የግጭቱ መንስኤ መሬት የማስፋፋትና መቀማት ፍላጎት ነው ይላሉ፡፡ “ህዝቡ በሰላም ሲኖር ነበር፤ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ በመሬት ማስፋፋት ፍላጎት ተደጋጋሚ ግጭት እየደረሰ ነው ብለዋል።

የኦሮምያና ሲዳማ ክልል አዋሳኝ አካባቢ
የኦሮምያና ሲዳማ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በአሮሚያ እና ሲዳማ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገደሉ፤ ሰባት ቆሰሉ

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን እና ሲዳማ ክልል ምስራቃዊ ዞን አዋሳኝ ሁለት ወረዳዎች አከባቢ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሞተው ሰባቱ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል፡፡ እንደ የአከባቢው ነዋሪዎች እና ተጎጂዎች አስተያየት የአርሶ አደሮች ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ንብረቶችም ተዘርፈዋል፡፡ ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ አሁን በህክምና ላይ የሚገኙ ወሊዪ ዋቆ የተባሉ የነንሰቦ ወረዳ ገመቹ ቀበሌ ነዋሪ ባለፈው ሳምንት እሮብ እና ሐሙስ በነበረውግጭት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ “መሬታችን እና ንብረታችንን ለመዝረፍ ነው እሮብ ሐምሌ 23 ማልደው ከሲዳማ ክልል የመጡ የታጠቁ አካላት ተኩስ የከፈቱብን፡፡

በዚህ መሃል ነው እኔም በጥይት የተመታሁና በቀኝ እጄ ላይ ጉዳት ያስተናገድኩ፡፡ የሞቱብን ወገኖቻችን አሉ፡፡ የተጎዱም ብዙ ናቸው፡፡ ማህበረሰባችን ምንም አገር ሰላም ነው ብሎ በሚኖርበት ነው መሰል ጥቃት እየደረሰበት ያለው፡፡ በገዛ መሬታችን ነው የሚገፉን፡፡ ማለዳ 11 ሰዓት አከባቢ ለሶላት ሳንነሳ ነው በጥቃት የጀመሩን፡፡ ሁለት ሰዎች አልፈዋል፡፡ ሰባት የምንሆን ደግሞ ቆስለን ሆስፒታል ገብተናል፡ እኔ ቀኝ እጄ ላይ ነው በጥይት የመቱኝ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በነንሰቦ ወረዳ ገመቹ ቀበሌ ነገዎ ዋቃ እና ገዳ ሰንበቶ የሚባሉ በኮኮሳ ወረዳ አራርሶ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዳንጎ በሚባል ስፍራ የተገደሉት መሆናቸውን የገለጹልን ሌላው አስተያየት ሰጪ የየአከባቢው ነዋሪ የዚህ ግጭት ዋናው መንስኤ መሬት የማስፋፋትና መቀማት ፍላጎት ነው ይላሉ፡፡ “ከጥንትም ህዝቡ በሰላም ሲኖር የነበረ ቢሆንም ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ ባለው የመሬት ማስፋፋት ፍላጎት ተደጋጋሚ ግጭት እየተስተዋለ ነው፡፡ አሁንም ህዝቡ ምንም ሳያውቅ አርሶአደር ላይ ተኩስ ከፍተው የሁለት ሰው ህይወት አልፏል፡፡ ሰባት ሰዎች ቆስለዋል።በዚያ አከባቢ ድንበር ላይ ስለሆነ ገበሬ ላይ እየተኮሱ መሬት መቀማት ነው ያለው ፍላጎት” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ግጭቱ ተደጋጋሚና በየዓመቱ የማያባራ እየሆነ ነው ብለዋልም፡፡ “በየዓመቱ አሁን አምናም ብዙ ሰው ተፈናቅለዋል ቤት ተቃጥለዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ኣመታት በዚያ በሰላም አብሮ የሚኖር ህዝብ እረፍት አላገኘም” ብለዋል፡፡

የኦሮምያና ሲዳማ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በግጭቱ ቤተሰባቸውን ያጡ የኮኮሳ ወረዳ አራርሶ ቀበሌ ነዋሪ በፊናቸው፤ “እሮብ ሀምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ጠዋት በመኖሪያችን መጥተው ነው ተኩስ ከፍተውብን ሰው የገደሉብን፤ ንብረታችንም ያቃጠሉት፡፡ ከሁለት ቀናት ግጭትበኋላ ዓርብ የአገር መከላከያ ሰራዊት ገብቶበት ሁኔታውን ቢያረጋጋም ቅዳሜም እለት ሾልከው መጥተው ቤት አቃጥለውብናል” ነው ያሉት፡፡
ግጭቱ ለምን ይሆን እልባት ያላገኘው የተባሉት ተጎጂዎች እና የአከባቢው ነዋሪዎች፤ “እሮብና ሐሙስ ገበሬው ጦር ላይ ከዋለ በኋላ መከላከያ  አርብ ገብቶ ነገሩን አብርዷል፡፡ በየዓመቱ ሰው ይሞታል አምናም እንዲሁ ገመዳ ቶርቢ፣ ጎበና ጃራ እና በሪሶ ሁሴን ተገድለዋል፡፡ ከሁለት ሶስት ቀን በኋላ ሰላም ወርዷል ብለው ይመጣሉ ከዚያን ደግሞ ግጭቱ ዳግም ይነሳል” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡…ሌላም አስተያየት ሰጪ፤ “ሽማግሌ ሲቀመጥ ተሳስተን ነው ሰይጣን ነው ያሳሳተን፤ አይደገምም ይላሉ፡፡ የበደለን ገበሬ ሳይሆን የመንግስት አካል ፖሊስ ነው፡፡ የሰው ድንበር አልገፋን ሞት እቤታችን ድረስ ነው እየመጣብን ያለው” ሲሉ የግጭቱ አለመብረድ ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኦሮምያና ሲዳማ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ግጭቱ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ እስከ ትናንትም ድረስ የአከባቢውን ማህበረሰብ በማወያየት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተሰራ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የምዕራብ አርሲ ዞን ሰላምና ፀጥታ ዘርፍ አስተዳዳሪ አቶ ገነሙ በሪሶ፤ ከሲዳማ ክልል አመራሮችም ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑንአመልክተዋል፡፡ “የችግሩ መነሻ ኅብረተሰቡም እንዳነሳልንና እኛም ከዚህ በፊትም ጉዳዩን እንደምናውቀው፤ የመሬት ማስፋፋት ፍላጎት በሲዳማ ክልል በኩል አለ፡፡ ከሲዳማ መጥተው ኦሮሚያ ውስጥ መሬት በሕገወጥ መንገድ ይዘው የነበሩ ሰዎች በሕግ አግባብር ለቀው ወደ መጡበት እነዲመለሱ ተወስኗል ከዚህ በፊት፡፡

እነዚህ ሰዎች በሕግ አግባብ መከራከር ሲገባቸው ወደ ግጭት ቀይረውት ወደ ሲዳማ እየተመላለሱ ሲፈልጉ ሌሊት እየመጡ ህዝብ ላይ ተኩስ ይከፍታሉ፡፡ ይህ ነገር መቆም እንዳለበት ከሲዳማ ክልል ባለስልጣናት ጋርም ተመክሯል፡፡ መስተካከል እንዳለበትና የሕግ የበላይነት መከበር እንዳለበት እነሱም ያምናሉ፡፡ ግን የመሬት ማስፋት ፍላጎቱ ስላለ ችግሩ ተደጋግሟል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዶይቼቬለ በሲዳማ ክልል ምሥራቃዊ ዞን በኩል የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ግዛቸው ኖኦራ እና የዞኑ ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ታደሰ ቱንሲሳን በስልክ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ግን ለዛሬ አልሰመረም፡፡
በኢትዮጵያ በስፋት ቀዳሚ የሆነው ኦሮሚያ ክልል በአገሪቱ ከበርካታ ክልሎች ጋር ወሰን የሚጋራ ሲሆን በተለያዩ አቅጣጫዎች ከዚህም በፊት ውዝግቦች መነሳታቸው አይዘነጋም፡፡

ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW