1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአቢዬ ግዛት የኢትዮጵያ ሔሊኮፕተር ተከስክሶ 3 ሰዎች ሞቱ

ቅዳሜ፣ የካቲት 2 2011

ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን በሚወዛገቡባት አቢዬ ግዛት የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሔሊኮፕተር ተከስክሶ ሶስት ሰዎች ሞቱ። በአደጋው የሞቱት ሶስት ሰዎች የሔሊኮፕተሩ የበረራ ሰራተኞች ናቸው። ከቆሰሉ ስምንት ተሳፋሪዎች ሶስቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ተብሏል።

Screenshot | Facebook Post United Nations Interim Security Force for Abyei
ምስል UNISFA

የምዝገባ ቁጥሩ UNO 379P የሆነው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሔሊኮፕተር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቢዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል (UNISFA) ቅጥር ግቢ ውስጥ በተከሰከሰበት ቅፅበት 23 መንገደኞች ጭኖ ነበር። የአቢዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል እንዳስታወቀው ኤምአይ ስምንት (MI-8) የተባለው ሔሊኮፕተር በተከሰከሰበት ቅፅበት ካዱግሊ ከተባለ ቦታ ወደ አቢዬ በመቀየር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች አሳፍሮ ነበር። 

በአደጋው ስምንት መንገደኞች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ሶስቱ በአስጊ ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት የአቢዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል ተልዕኮ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በአስጊ ኹኔታ ውስጥ የሚገኙት ተሳፋሪዎች በካዱግሊ በኩል ወደ አዲስ አበባ መወሰዳቸውንም አክሎ ገልጿል። በመግለጫው መሠረት ቀሪዎቹ አምስት መንገደኞች በአቢዬ በሚገኝ ሆስፒታል እገዛ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ሔሊኮፕተሩን ለመከስከስ ያበቃው ምክንያት እስካሁን አልታወቀም። በተባበሩት መንግሥታት የአቢዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ገብሬ አድሐና ጉዳዩ እየተመረመረ መሆኑን ተናግረዋል። "ዛሬ ከሰዓት በኋላ በተፈጠረው ክስተት እጅግ አዝነናል። በአደጋው ለሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እንገልፃለን" ብለዋል ሜጀር ጄኔራል ገብሬ። 

የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሔሊኮፕተር የተከሰከሰው መደበኛ የወታደሮች ዝውውር መርኃ-ግብር ተሰማርቶ በነበረበት ወቅት መሆኑን የአቢዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል ያወጣው መግለጫ አትቷል። ለተባበሩት መንግሥታት የአቢዬ ጊዜያዊ የጸጥታ ኃይል ወታደሮች በብቸኝነት ያዋጣቸው ኢትዮጵያ 4,500 አባላት ያሉትን ኃይል አሰማርታለች።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW