በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን 19 ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 24 2017
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ ሆማ ጋለሳ በተባለ ቦታ በደረሰው ጥቃት አራት ሪጴሎላ ወይም ጸረሽምቅ የተባሉ የመንግስት ጸጥታ ሐይሎችን ጨምሮ 23 የሚደርሱ ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱ የደረሰው ሰብአዊ ጉዳት እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎቹ የተጎዱ ሰዎችን አሁንም እየተፈለጉ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር በበኩሉ ጥቃቱ መድረሱን አረጋግጠው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ የተባሉ ሀይሎች ጉዳት ማድረሳቸውን አመልክተዋል፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ከተማ ዋኩማ የጸጥ ሐይሎች በአሁኑ ወቅት በታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱ 19 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል
በታጣቂዎች ጥቃት በተደጋጋሚ ጉዳት የደረሰባት በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን ውስጥ በምትገኘው አቤዶንጎረ ወረዳ ትናንት በደረሰው ጥቃትም 19 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች መ እና አራት መንግስት ጸጥታ ሐይሎች ገደላቸውን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱ በወረዳው ሆማ ጋለሳ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ መድረሱን የተናገሩት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪው በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ፍለጋ ዛሬም ቀጥሎ መዋሉን አክለዋል፡፡ በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች መካከል አንድ ሴትና የአምስት ዓመት ህጻናን የሚትገኝ ሲሆን ሰባት ሴቶችም ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንደደረባቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹በጥቃቱ አራት ረጵሎላ(ጸረ ሽምቅ) ሀይሎች የተገደሉ ሲሆን የቆሰሉ አምስት ናቸው፡፡ ከነዋሪው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 19 የደረሰ ሲሆን አስራ አንድ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ አንድ ባለሀብት ደግሞ ይዞ ነው የሄዱት፡፡ ከአርብ አጥቢያ 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ አምስት ሰዓት በቦታው ላይ ከፍተኛ ተኩስ ሲሰማ ነበር፡፡››
ሌላው አስተያየቸውን የሰጡን የአካባቢው ነዋሪም ጥቃት አድራሾች በወረዳው ቱሉ ሞቲ እና ሆማ ጋለሳ በሚባል ስፋራ በከባድ መሳሪያ በታገዘ መልኩ ጥቃት እንደሚያደርሱ ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች በተደጋጋሚ በተደራጀ መልኩ በደረሱት ጥቃቶች የበርካታ ሰዎች ህይወት እያለፈ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ ትናንት በደረሰው ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉን የተናገሩ ሲሆን ከአካቢው ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ ብዙ ሰዎች ናቸው የተጎዱት፡፡ ከስድስት ቀን በፊትም በ18/2017 ዓ፣ም በተመሳሳይ ቱሉ ሞቲ ላይ ባደረሱት ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ከ200 በላይ በግ የቁም እንስሳት ነው የወሰዱት፡፡ ከሆማ ጋለሳም የትናንቱን ጥቃት ተከትሎ በርካታ ሰዎች እየሸሹ ይገኛሉ፡፡››
ጥቃቱን ያደረሱት እነማን ናቸው?
ዳዳሪ የሆኑት አቶ ከተማ ዋቁማ በወረዳው ሆማ ጋለሳ በተባለ ስፍራ በደረሰው ጥቃት የሰዎች ህይወት ማፉሉን ያረጋገጡ ሲሆን የጉዳት መጠኑን እያጣሩ እንደሚገኝ ገልተዋል፡፡ በአካባቢው ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ እና ከአጎራባች ክልል ይሻገራሉ የተባሉ (ፍንጣለይህ) ወይም ጽንፈኛ ሐይሎች ያሏቸው ቡድኖች ጥቃቱን ማድረሳቸውን አብራርተዋል፡፡
‹‹ መሰል ጥቃቶችን ለመካከል ቀበሌዎች እየተደራጄ ነው፣ምሊሻም በየቀበሌው እየተደረጀና እየታጠቀ ነው፤በየአካባቢው የመከላከያ ሰራዊትም ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ደን በብዛት በአካቢው መገኘቱን እነዚህ ሀይሎች ለዝርፍና ግድያ ይጠቀሙበታል፡፡ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ ይዘርፋሉ፡፡ ብለዋል፡፡››
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ በተደጋጋሚ የታጣቂዎች ጥቃት የሚደርስባት ወረዳ ናት፡፡ በቅርቡ በደረሱት የተደራጅ ጥቃቶችም የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉም መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ፀሐይ ጫኔ