በአቪዬሽን ደኅንነት ረቂቅ አዋጅ የተካተቱ ድንጋጌዎች የሚና መደበላለቅ እንዳያስከትሉ ተጠየቀ
ማክሰኞ፣ የካቲት 10 2018
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት "የአቪዬሽን ደኅንነት ሥራዎችን በበላይነት ለማስፈፀም" አግባብነት ያለው ተቋም ሆኖ ሥልጣን እንዲሰጠው የቀረበው ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ፣ የተቋማትን የሚና መደበላለቅ እንዳያስከትል ጥያቄ ቀረበበት።ጥያቄው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች እንዲሁም የከተማ መሰረት ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ዛሬ በጋራ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የቀረበው ነው።
በውይይቱ የፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን ወክለው የተገኙ ተሳታፊዎች ይህንን ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ማሻሻያውን ያቀረበው ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የቀረቡ የማሻሻያ ድንጋጌዎች ከ ሀገሪቱ "ብሔራዊ ደኅንነት አንጻር" የሚታዩ መሆናቸውን ጠቅሷል።የማሻሻያ ድንጋጌው አስተማማኝ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የአቪየሽን አገልግሎትን የሚያበረታቱ እንጂ የተቋማቱን ሚና ለመተካት የተዘጋጀ እንዳልሆነ የተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል
ማሻሻያ ረቂቁ ተላላፊ መንገደኞች ላይ ያለውን ተደጋጋሚ ፍተሻ ያስቀራል
ለ20 ዓመታት ያገለገለውን የአቪየሽን ደኅንነት አዋጅ ለማሻሻል በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት መርሐ ግብሮችን፣ የአየር መንገድ ኦፕሬተሮችን፣ የአየር እንቅስቃሴ አገልግሎት ሰጪዎችን እና ሌሎች የሚያወጧቸውን የደኅንነት መርሐ ግብሮችና መመሪያዎችን የመገምገም፣ የማፅደቅ እና ተገቢውን የጥራትና የቁጥጥር ተግባራትን የማከናወን ሥልጣን በበላይነት እንዲመራ የሚያደርግ ነው።
የማሻሻያው ገፊ ከተባሉ ምክንያቶች የሳይበርእና የሰው አልባ በራሪ አካላት ወይም ድሮኖች ጥቃትን፣ ከትከሻ የሚተኮስ መሣሪያን አደጋ፣ ከውስጥ የሚነሱ አሻጥሮችን፣ የአውሮፕላን ጠለፋን እና ፍንዳታዎች ለመከላከል እና የዘርፉን "ደኅንነት የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ" ሌሎች ተጨማሪ ባለድርሻ አካላት የተካተቱ በመሆናቸው አባልነታቸውን በሕግ መደንገግ በማስፈለጉ" የሚሉት ይጠቀሳሉ።በሥራ ላይ ያለው አዋጁ ሲፀድቅ እና አሁን ያለው ተጨባጭ የአቪየሽ ሥጋት ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ማሻሻያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚያጓጉዛቸው ማንገደኞች ውስጥ 80 በመቶ ይሆናሉ የሚባሉት ተላላፊ መንገደኞች ላይ ያለውን ተደጋጋሚ ፍተሻ በማስቀረት የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ተብሏል። የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የሕግ ክፍል ዳይሬክተር አቶ አማረ ኢቲቻ ይህንኑ ገልፀዋል።
"በኢትዮጵያ በኩል የሚጓዙ ተላላፊ መንገደኞች ከመነሻ ሀገር የሚደረግላቸው የደኅንነት ርምጃ አስተማማኝ መሆኑ ከተረጋገጠ መንገደኞች እና የዕቃ ጉዞዎቻቸው ከፍተሻ ነጻ የሚሆኑበት አግባብ ነው።"
ከፌዴራል ፖሊስ እና ከኢሚግሬሽን የተነሱ ጥያቄዎች
"የአቪየሽን ፖሊስ ከሌለ የአቪየሽን ደኅንነት የለም" ያሉ አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል የውይይቱ ተሳታፊ፣ በሀገሪቱ 24 ኤርፖርቶችን እየጠበቀ ያለው ፖሊስ ከተሰጠው ኃላፊነት አንፃር "የሚና መደበላለቅ እንዳይኖር" ሥጋት መኖሩን ጠቅሰዋል።በማሻሻያው ላይ ሌላው የጎላ ጥያቄ የቀረበው ከኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሲሆን፣ ለተቋሙ በአዋጅ የተሰጡት ሥልጣኖች በዚህኛው ማሻሻያ ሥር እንዳይሆኑ ጥያቄ አስነስቷል።"ተጓዦችን በሚያስተናግድበት ጊዜ ኢሚግሬሽን፣ ተጓዦች ከሀገር እንዳይወጡ ዕገዳ የተጣለባቸው ስለመሆኑ፣ ነጻ ስለመሆናቸው የማረጋገጥ ተፈጥሯዊ ሥልጣን ነው ያለው። ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ይህንን በምን አይነት መንገድ ለማስተግበር እዚህ ድንጋጌው ላይ እንደተቀመጠ ግልጽ" አይደለም።
ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎትበኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከተጓዥ ቲኬት ላይ የሚሰበስበው "የሴክዩሪቲ አገልግሎት ክፍያ" የአሰራር ችግር እንዳይፈጥር በሚል ዛሬ በሰፊው ያወያየ አንዱ ጉዳይ ነበር። በውይይቱ ማሻሻያው የኃላፊነት መጣረስ እና መገፋፋት እንዳያከትል በሚል ለቀረበው ሥጋት ምላሽ የሰጡት የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ቶላ፣ ጉዳዩ "ከብሔራዊ ደኅንነት አንፃር" የሚታይ እንደሆነና የፖሊስን፣ የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎትን፣ የኤርፖርቶች ድርጅትን እና የሌሎችንም ሚና የመተካት ፍላጎት የለም ብለዋል።
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጄላ በበኩላቸው በተለይ ከኢሚግሬሽን የተነሳው ጥያቄ የብሔራዊ ደኅንነት ተልዕኮን ካለመረዳት የተነሳ ካልሆነ በቀር የአዋጁ ማሻሻያ አሁን ያለውን አሠራር የሚቀይር ሳይሆን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
"ከፓስፖርት፣ ከቪዛ ጋርና ሌሎች ከድንበር ጋር አይገናኝም። የሚጣረስ አይደለም። ይበልጥ የሚመጋገብ ነው።"
በረቂቅ ማሻሻያው መሠረት ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት“የመንገደኞችን ምዝገባ እና ቅድመ-በረራ መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት ትግበራን ይመራል፤ ያስተባብራል። በሀገር ውስጥ ከሚያከናውናቸው የመረጃና ደህንነት ተግባራት በተጨማሪ ከሌሎች አቻ ተቋማት በመተባበር አለም አቀፍ የወንጀል ሪከርድ ያላቸውን ተጠርጣሪዎችን የሚመለከት መረጃ በመለዋወጥ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ሽብርተኝነትና የተደራጁ ወንጀሎች በመከላከል ረገድ እንደ ሀገር ያለበትን ኃላፊነት መወጣት ያለበት በመሆኑ" ይህ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ