1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

በአክሱም ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ላይ የተጣለዉን እገዳ የመቀሌ ነዋሪዎች በሰልፍ ተቃወሙት

ማክሰኞ፣ ጥር 13 2017

ፍርድቤቱ፥ ይህ አስተዳደራዊ መመርያ በተማሪዎች ላይ 'የማይመለስ የመብት ጥሰት' ሊያስከትል ስለሚችል ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑም ገልጿ ነበር። ይሁንና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሁን የትግራይ ትምህርት ቢሮ የስራ መመርያ እስካሁን ተፈፃሚ አልሆኑም።

በሰልፉ ላይ የተካፈሉ በ10 ሺሕ የሚቆጠሩ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ የእስልምናና የክርስትና ዕምነት ተከታዮች፣ የመብት ተሟጋቾች ክልከላዉን አዉግዘዋል።
የአክሱም ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰዉ እንዳይማሩ የተጣለባቸዉን  ክልከላ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በመቐለ ተካሄደምስል፦ Million Hailesilassie/DW

በአክሱም ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ላይ የተጣለዉን እገዳ የመቀሌ ነዋሪዎች በሰልፍ ተቃወሙት

This browser does not support the audio element.

የአክሱም ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰዉ እንዳይማሩ የተጣለባቸዉን  ክልከላ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ በመቐለ ተካሄደ። ሰልፉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች፣ የተማሪዎች ወላጆች፣ ሌሎች የእስልምና እና ክርስትና እምነት ተከታዮች እንዲሁም የሴቶች መብት ተማጓቾች የተገኙበት ነው።

ይህ ዛሬ ጠዋት መነሻው በመቐለ የሚገኘው የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ዋና ፅሕፈት ቤት አድርጎ እስከ ሮማናት አደባባይ በዘለቀው ሰልፍ፥ ሒጃብ በመልበሳቸው ምክንያት በአክሱም የሚገኙ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መታገዳቸው የመብት ጥሰት ነው ሲሉ ሰልፈኞቹ አውግዘዋል። ሒጃቧ ትለብሳለች ትምህርቷም ትማራለች፣ ሒጃብ የማንነታችን መገለጫ ነው፣ ሒጃብ መልበስ መብት እንጂ ልዩ ጥቅም አይደለም፣ መብታችን ይከበር ነፃነታችን ይጠበቅ የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮች በሰልፉ ተስተጋብተዋል።

 

ከሰልፉ በኃላ የሙስሊሙ ማሕበረሰብ ጥያቄ ይዘው የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት አመራሮች ወደ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት መስርያ ቤት ያመሩ ሲሆን፥ ከክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋርም ተወያይተዋል። ፕሬዝደንት ጌታቸው ለሙስሊሙ ማሕበረሰብ ተወካዮች በሰጡት ማብራሪያ፥ የተፈጠረው ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑ አንስተዋል።

ሰልፈኛዉ ከትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ዋና ፅሕፈት ቤት ተነስቶ እስከ ሮማናት አደባባይ በዘለቀው ጎዞዉ ሒጃብ በመልበሳቸው ምክንያት ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መታገዳቸው የመብት ጥሰት ነው በማለት አዉግዞታል።ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

 

አቶ ጌታቸው "ከውጭ የሚመጣ ተሟጋች አያስፈልገንም። ጉዳዩ በራሳችን ነው የምንጨርሰው። ያለን አንድነት እና መፈቃቀር ሊነካ አይገባም። የአክሱም ህዝብም በዚህች ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዳለው ነው የማውቀው። እንዳንድ በክፋት የተሰማራ ካልሆነ፥ እያያችሁት እንዳለ ይህ ጉዳይ ያላሳዘነው፣ መፍትሔ መበጀት አለበት ያላለ የለም። ችግሩ እንደሚፈታ ነው የማምነው፣ ያለን ግንኙነትም የሚያሳየው ይህ ነው። በመዘግየቱ ግን ለሙስሊሙ ማሕበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ልጆቹ ወደትምህርት ቤት መላክ የሚፈልግ የትግራይ ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለብን ብዬ ነው የማምነው" ብለዋል።

 ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ወደ የአክሱም ከተማ ትምህርት ፅሕፈት ቤትደብዳቤ ፅፎ የነበረው የትግራይ ትምህርት ቢሮ፥ ችግሮች በመምርያ እና አሰራር መፈታት ስለሚገባቸው ትምህርት ቢሮ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እየሰራ መሆኑ የሚያነሳ ሲሆን፥ እስከዛ ድረስ ግን ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው የቆዩ ተማሪዎች ከክልከላው በፊት ይጠቀሙት የነበረ አለባበስ ተጠቅመው ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ሲል መመርያ አስተላልፎ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድቤት አምስት የከተማዋ ትምህርት ቤቶች በሴት ሙስሊም ተማሪዎች ላይ የጣሉት ክልከላ ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑ ይታወሳል።

ከሰልፉ በኃላ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት አመራሮች ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ከአቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ተወያይተዋልምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ትምህርት ቤቶቹ ባስተላለፉት የአስተዳደር መመርያ መሰረት ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ከከሳሽ የትግራይ እስልምና ጉዳዮይ ጠቅላይ ምክርቤት መረዳቱ የገለፀው ፍርድቤቱ፥ ይህ አስተዳደራዊ መመርያ በተማሪዎች ላይ 'የማይመለስ የመብት ጥሰት' ሊያስከትል ስለሚችል ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑም ገልጿ ነበር። ይሁንና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሁን የትግራይ ትምህርት ቢሮ የስራ መመርያ እስካሁን ተፈፃሚ አልሆኑም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW