1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአውሎንፋስ የተቋረጠው የቢሾፍቱ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥገና

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 8 2017

ቢሾፍቱ ከተማ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በረዶና ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዛሬ ላይ 10 ቀናትን ቢሻገርም በርካታ ስፍራዎች ላይ የሃይል አቅርቦቱ አለመመለሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

የቢሾፍቱ ከተማ በከፊል።ባለፈዉ ሳምንት አዉሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝንብ ከጣለ ወዲሕ የከተማይቱ ከፊል አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠበት ነዉ።
የቢሾፍቱ ከተማ በከፊል።ባለፈዉ ሳምንት አዉሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝንብ ከጣለ ወዲሕ የከተማይቱ ከፊል አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠበት ነዉ።ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በአውሎንፋስ የተቋረጠው የቢሾፍቱ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥገና

This browser does not support the audio element.

 

ባለፈው ሳምንት ቢሾፍቱ ከተማ በርካታ ቀበሌያት ውስጥ በረዶና ንፋስን ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶዎች እና የኤሌክትሪክ ገመዶች ላይ ጉዳት በማድረሱ የከተማይቱ ነዋሪዎች   ከ10 ቀናት በላይ ያለ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማጣታቸዉን አስታዉቀዋል።የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ በአደጋዉ 260 የከፍተኛ እና 460የዝቅተኛ መስመር ማስተለለፊያ ምሰሶዎች መወደቃቸውን ገልጧል።መስሪያ ቤቱ  የተቋረጠውን የኃይል አቅርቦት ለመመለስ እየጣረ መሆኑን አስታዉቋልም።

ከመዲናዋ አዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 50 ኪ.ሜ. ርቃ በምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በረዶና ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዛሬ ላይ 10 ቀናትን ቢሻገርም በርካታ ስፍራዎች ላይ የሃይል አቅርቦቱ አለመመለሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ታይቶ የማይታወቅ እጅግ አደገኛ ያሉት በእለቱ ንፋስን ቀላቅሎ በጣለው ከባድ በረዶአማ ዝናብ በከፊል የከተማዋ ክፍል ጣሪያዎችን ቀነጣጥሎ የኤሌክትሪክ ገመዶችን እንዳልነበሩ አድርጎአቸዋል፡፡ አስተያየት ሰጪ የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ፤ “አዲስ ነገር ነው፤ ይህ ማዕበል እንጂ አውሎንፋስ የሚባልም ብቻ አይደለም፡፡ መጀመሪያ ሰማይ ስጠቁር ነው መብራት የጠፋው፤ እንዳውም እሱ ነው የበጀን፡፡ ንፋሱ እንደመጣ ሁሉም ወደየቤቱ ገባ፤ ከዚያን በረዶ ብቻ እየዘነበ በንፋሱም ቆርቆሮ ከጣሪያው ተገነጣጠለ” ብለዋል፡፡

በከተማዋ 14 ቀበሌ ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታል  እና የእምነት ተቋማት በእለቱ በነበረው ከባድ የተፈጥሮ አደጋ ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸውን የገለጹት የከተማዋ ነዋሪ የአይን እማኝ፤ ዛፎች በተቋማት ላይ መገነዳደሳቸውንም ገልጸዋል፡፡ በርካታ የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ፖሎች በከተማዋ ሰፊ አከባቢ ስወድቁ አስቀድሞ ኃይል እንዲቋረጥ መደረጉ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ችሏል የሚሉት አስተያየት ሰጪ ይሁንና እስካሁንም ድረስ ለ10 ቀናት እሳቸውን ጨምሮ በርካታው የከተማዋ ነዋሪ የአሌሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እንደተቆራረጡ እስከ ዛሬ መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡ “በእለቱ መብራት መጥፋቱ ከአደጋ ታድጎናል እንጂ ከተማቃ ትነድ ነበር፡፡ አሁን አልፎ አልፎ ከመጣባቸው አከባቢዎች በስተቀር አብዛኞቻችን አስረኛ ቀናችን እስካሁን ማብራት እንደተቋረጠብን ነው” ብለዋል፡፡

በኤሌክትሪክ መቋረጥ የደረሰው እንግልት

ሌላኛውም የከተማዋ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት፤ “አውሎ ንፋሱ ከሰርክል ወደ ቀበሌ 03፣ ቀበሌ 08 እና ቀበሌ 09 ባቦጋያ መሄጃ በሙሉ ያላወደመ ነገር የለም፡፡ የኤሌክትሪክ ፖሎች በሙሉ ወዳድቀው መንገድ ሁሉ ማለፍ እጅግ አዳጋች ነበርም” ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ በአደጋዉ 260 የከፍተኛ እና 460 የዝቅተኛ መስመር ማስተለለፊያ ምሰሶዎች መወደቃቸውን ገልጧልምስል፦ DW/B. Jequete

ሌላም ነዋሪ ሃሳባቸውን አከሉ፡፡ “ፖሎች የመብራት ተሸካሚዎች እንዳለ የሉም፡፡ አሌክትሪክ ሃይሎች ሻሻመኔን ጨምሮ ከተለያዩ አከባቢዎች መጥተው እየተረባረቡ ነው ተብሏል ግን እስካሁን እኛጋ አልደረሰም፡፡ አንዳንድ ቦታ ሃይል ብለቀቅም በኛ አከባቢ እስካሁን ፖሎች መትከልና ሽቦ መወጠር ላይ ቢሆኑም ሃይል አልተለቀቀልንም፡፡ ቀበሌ 11፣ 12፣ 13፣ 14 እና ባቦጋያ አከባቢ እስካሁን ሃይል የለም” ሲሉ በሃይል መቋረጥ ምክንያት ያለፉትን 10-11 ቃነት በጨለማ መዋጣቸውን ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሪክ መስመሮች መልሶ ጥገና ጥረት

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የተቋረጠውን የአሌክትሪክ ኃይል ለመመለስ የሚደረገው ጥረት እየቀጠለ ነው ብሏል፡፡ አገልግሎቱ የኃይል አቀርቦቱ የተቋረጠው 10 ትራንስፎርመሮች፣ 260 የከፍተኛ መስመር ምሰሶዎች እና 460 የዝቅተኛ መስመር ምሰሶዎች በመወደቃቸው ምክንያት መሆኑን አመልክቷል፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሰሶች መካከል 25 የኮንክሪት ምሰሶ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ 16 መጋቢ መስመሮች ጋር ንክኪ ያላቸውን ዛፎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የማንሳት ስራ እየተሰራ ነውም ተብሏል፡፡

ኃይል ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ከአዲስ አበባ፣ አዳማ እና ቢሾፍቱ ከተማ በተውጣጣ ግብር ኃይል የተቋረጠውን አገልግሎት ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱንም አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW