1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል በዓል (2024)

ሐሙስ፣ ነሐሴ 2 2016

ባለፈው ሳምንት ከሐምሌ 23 እስከ 27 ቀ ን ለአራት ቀናት በቤልጀየም ጌንት አካባባቢ በምትገኘው ሮንሰ ከተማ ሁለገብ የስፓርት ማዘውተሪያ ስፍራ የተክሄደው በአውሮጳ ኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፊሲቲቫል በሰላምና በስኬት ተጠናቋል።

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን በዓል
በአውሮጳ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውናን እና ትውልደ ኢትዮጵያ የተሰባሰቡበት ደማቅ በዓል በቤልጅየም ተካሂዷል። ምስል Gebeyaw Nigussie/DW

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል በዓል (2024፟)

This browser does not support the audio element.

 

ባለፈው ሳምንት ከሐምሌ 23 እስከ 27 ቀ ን ለአራት ቀናት በቤልጀየም ጌንት አካባባቢ በምትገኘው ሮንሰ ከተማ ሁለገብ የስፓርት ማዘውተሪያ ስፍራ የተክሄደው በአውሮጳ ኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፊሲቲቫል በሰላምና በስኬት ተጠናቋል። በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌዴርሺን ይህን መሰል በዓል ሲያዘጋጅ የዘንድሮው 19ኛው ነው። በበዓሉ የተለያዩ ደረጃዎች የእግር ኳስና ሌሎች ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ተካሂደዋል። ባህላዊ ጭፈራዎችና ሙዚቃዎች ታይተዋል ፤ ተደምጠዋል። የሙዚቃ ኮንሰርቶችም ቀርበዋል።

የእግር ኳስ ውድድሩ አሸናፊዎች

በበልጅየም ጌንት ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው የሮንሰ ከተማ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ የተከሄደው የስፖትና ባህል ፈስቲቫል በእግር ኳስ በኩል በአውሮጳ የአንደኛና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡድኖች በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች ያሉ የሕጻናት ቡድኖች በየደረጃቸውና በጠቅላላው 37 የእግር ኳስ ቡድኖች በስፖርታዊ ጨዋነት ከፍተኛ ውድድ አድርገው በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የተስየመውን የአንደኛ ዲቪዝዮኑን ዋንጫ ኢትዮ ሎንዶን ቡድን ኢትዮ ስዊዝን በማሸነፍ ሲወስድ፤ በወጣት አበበ ገብረመድኅን የተሰየመውን የሁለተኛ ዲቪዝዮን ዋንጫ ኢትዮ አዲስ ቤልጀየም ቡድን ኢትዮ በርሊንን አሸንፎ አሰቀርቷል።

 ወጣት አበበ ገ/መድኅን የኢትዮ ቤልጀምን ቡድን ከመሰረትት አንዱና በባህልና ሌሎች የቤልጀየም ኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችም ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው ሲሆን፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በድንገተኛ የሥራ ላይ አደጋ ሕይወቱ በማለፉ በቤልጀየም የስፖርት ማኅበረሰብ ጥያቄ የዘንድሮው የሁለተኛ ዲቪዚዮን ዋንጫ በሱ ስም እንዲሰየም የተወሰነ መሆኑን  የፊዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አሳየኸኝ ጥላሁን አስታውቀዋል።  

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል በውጭ ሀገር ለተወለዱት ሕጻናት ልዩ ስለ ኢትዮጵያ የሚያውቁበት ልዩ የመማሪያ እና የመገናኛ መድረክ ነው።ምስል Gebeyaw Nigussie/DW

 በቤልጀየም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብና ቤተሰቦቹ ፌዴርሽኑ ይህንን ውስኔ በማስለፉ ምሥጋና ያቀረቡ ሲሆን በሱ ስም የተሰየመውን ዋናጫ ያስቀረው የኢትዮዮ አዲስ ቤልጅየም የወጣቶች ብድን አሰልጣኝ ያፌትም ይህን በአበበ ገብረመድኅን የተሰየመውን ዋንጫ በማስቀረታቸው ልዩ ክብርና ስሜት የሚሰማቸው መሆኑን ገልጿል።

የስፖርትና ባህል ፌዴሬሽኑ ዓይነተኛ ተግባሮች

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አሳየኸኝ ጥላሁን የፌዴሬሽኑ ተግባር  ከስፖርትዊ ውድድሮች በተጨማሪ በዋናነት ኢትዮጵያውያንን ማገናኝትና ባህልና ወጋቸውንም ለሌሎች ማኅብረሰቦች ማስተዋወቅ ብሎም ኢትዮጵዊነትን ማክበር መሆኑን በተለይ ለDW ተናግረዋል።

እንደተባለውም ከኳስ ጨዋታው ውድድሮች ባሻገር፤ ዋናዋ የዝግጅቱ ማዕከል የሮንስ ከተማ ብቻ ሳትሆን በአካባቢው የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ጭምር የኢትዮጵያውያን የባህል ጭፈራዎች የሚታዩባቸውና የሚሰሙባቸው፤ ኢትዮጵውያን በልዩ ልዩ የባህል አልባሳት ተውበው የደመቁባቸው፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን  ሕጻናት የቧረቁባቸው ሆነው ከርመዋል። በትልቁ የዝግጅቱ ስፍራ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቀውና አምረው ንግድ ሲካሄድባቸው፤ የባህል ዕቃዎች ሲታዩብቸውና ሲሸጡባቸው፤ ሙዚቃዎች ሲንቆረቆሩባቸው የክረሙት ድንኳኖች የአዲስ አበባውን የጥምቀት ጃን ሜዳ የሚያስጋውሱ ሆነዋል።

በቤልጂየም የተካሄደው የባህል እና የስፖርት በዓልበተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ ወገኖችን በአንድ መድረክ ያገናኘ ነበር። ምስል Gebeyaw Nigussie/DW

የፊዴሬሽኑ ይዞታ

 የፈዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት እንደገለጹትና እኛም እንድታዘብነው ፊዴሬሽኑ ከየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ፤ ሃይማኖት ወይም ብሔር ያልወገነ ግን የሁሉም ኢትዮጵያውያን የሆነና ኢትዮጵያዊነት የደመቀበት ነበር። የነበረው ድባብና ስሜት ማንኛውም ዓይነት ከፋፋይና የሚለያይ አስተሳሰብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ቦታ ሊኖረው እንደማይችልም ኢትዮጵያውያኑ ይህን የመስለውን ሙዚቃ በጋራ በማቀንቀንና በመጨፈር ስሜት መልእክታቸውን ሲያስተላልፉ ተስተውለዋል።

በዓሉ በተለይ ለቤተብና ልጆች የሚፈጥረው ስሜትፋይዳው

 የአውሮጳ የስፖርትና ባህል ፊስቲቫል ከሁሉም በላይ ግን የቤተስብና የልጆች በዓል እንድሆነ ነው የሚነገርውና መታዘብም የተቻለው። በሺህ ከሚቆጠሩት ከበርካታ የአውሮጳ ሃገራት ብዙዎቹ ለበዓሉ ከልጆቻቸውና ሌሎች ቤተሰቦቻቸው ጋር የመጡ ናቸው። በውጭ የተወለዱ ሕጻናት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚተዋወቁበት ዓይነተኛ መድረክ በመሆን የሚያግለግል ሲሆን፤ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን እንደሚናገሩት ወደ በዓሉ ሲመጡ ወደ ኢትዮጵያ የሄዱ ያህል ይሰማቸዋል፤ ልጆቻቸውም የበዓሉን ድባብና ስሜት ይወዱታል በየዓመቱም ከዝግጅቱ መቅረት አይፈልጉም። በዝግጅቱም የተለያዩ የሕጻናት ውድድሮች ብቻ ሳይሆን ከመድረክም የሕጻናት ሙዚቃዎችና መዝሙሮች ሲስተጋቡ ተሰምተዋል።

የዘንድሮው የአውሮጳ የስፖርትና ባህል በዓል የክብር እንግዳ አቶ ስሎሞን መኮንን ለዶቼ ቬለ እንደገለጹትም በአሜሪካም ይሁን በአውሮጳ የስፖርት በዓላት ትልቁ ነገር የሕጻናት በብዛት በበዓሉ መገኘትና መሳተፍ ነው። ከተለያዩ የአውሮጳ አገሮች ከነቤተሰባቸው የመጡ ወላጆችና ታዳሚዎችም ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ።

ዘንድሮው በዓል ከቀድሞዎቹ በዓላት የተለየበት

የዘንድሮው በዓል በተለይ በርካታ ሕጻናትና ወጣቶች የታዩበትና ከኢትዮጵያ ውጭ በአውሮጳ የተለያዩ አገሮች ያደጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በክለብ ተደራጅተው የተሳተፉበት መሆኑን፤ የፌደሬሽኑ ፕሬዝድንት የስፔኑን የኢትዮ ባርሴሎናን ቡድን በመጥቀስ አስረድተዋል። በአውሮጳ አሳዳጊ ወላጆች ያደጉ በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አገሮች የሚገኙ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ አንዳንድ ቦታ ለምሳሌ ቤልጅየም የትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ሕጻናት ወላጆች እራሳቸው በማኅበር ተደራጀተውና በግል በእንደዚህ ዓይነት ቦታዎች በመገኘት ለልጆቻቸው የትውልድ አገራቸውን ባህልና ታሪክ ሲያሳዩና ሲያስተምሩ ይስተዋላሉ። በቀጣይም ልክ እንደ ኢትዮ ባርሴሎኖቹ ቡዱን ከሌሎች አገሮችም በስፖርት ክለብ የተድራጁ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ቡድኖች ፌዴሬሺኑን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ነው የሚገመተው። ይሕም ፌዴሬሽኑ ከሀገራቸው ለራቁትና ስለሀገራቸው ለማወቅ ለሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያውንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ዓይነተኛ መድረክ በመሆን እያገለገለ ስለመሆኑ የሚይሳይ ሁኗል።

በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል በዓል ኢትዮጵያን የማስተዋወቂያ መድረክም ነው። ምስል Gebeyaw Nigussie/DW

የበአሉ ማጠቃለያና ሰላማዊነቱ

 በጥሩ ስሜትና ፈንጠዝያ፤ ስፖርታዊ ውድድርና የእርስ በእርስ ትውውቅ ያለፈው የዘንድሮው የስፖርት በዓል በመጨርሻ ያሸናፊዎቹን ቡድኖች የዋናጫ ሽልማት የክብር እንግዳው አቶ ስሎሞን መኮንና የወጣት አበበ ገብረመድኅን ቤተሰቦች ሰጥተው በአዓ በሰላም ተጠናቋል።

 ይህ በሁሉም የዝግጁት ቀናት በዋናው የበዓሉ ሜዳና የኮንሰርት ቦታዎች ከአስር ሺህ ህዝብ በላይ ሳይሳተፍበት አልቀረም የተባለለት የዘንድሮው የአውሮጳ የስፖርትን ባህል ዝግጅት ሰላማዊና የጎላ ችግር ያልታየበት፤ ይልቁንም ታዳሚዎች የተደሰቱበት እንደሆነ በብዙዎች ተነግሯል። የፊዴርሺኑ ፕሬዝደንት አቶ አሳየኸኝም ይህንኑ ሀሳብ በማጠናከር በዓሉ በታቀደው ልክ የተካሄደና የተሳክ እንደነበር ነው የተናገሩት። የተነሱ ችግሮችና የነበሩ ድክመቶች

የዝግጅቱ ቦታ ምንም እንኳ ለስፖርታዊ ውድድሮች የተሟላ ሜዳ ያለውና ለእንዲህ ዓይነት በርካታ ታዳሚዎች ለሚገኙበት በዓል አመቺ ቢሆንም ወደ ቦታው ለመድረስ የነበረውን የመጓጓዣ ችግር ግን ብዙዎች በምሬት በማንሳት ለወድፊት ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ማሳሰቢያ ሲሰጡ ተሰምተውል።

በተለያዩ ቀናት ምሽት ሙዚቃዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ፌዴሬሽኑ አስቴር አወቀን፣ ጸሐየ ዮሐንስን፣ አብዱ ኪያርንና ዳኘ ዋለን የጋበዘ ቢሆንም፤ በበዓሉ የመጨረሻ ቀን ምሽት ሊቀርብ ፕሮግራም የተያዘለት የታዋቂዋ አስቴር አወቀ ዝግጅት ግን ዘግይቶ መሰረዙ ተገልጿል። ይህም ብዙዎችን አጉላልቷል አስቆጥቷልም። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አሳየኸኝ ጥላሁን ለዚህ ያልተጠበቀ ላሉት ጉድለት ታዳሚዎቹንና አንጋፋዋን አርቲስት አስቴር አወቀን በፌዴሬሽኑ ስም ይቅርታ መጠየቃቸው ታውቋል።

በዓሉ አሳድሮት ያለፈው ተዝታ

19ኛው የአውሮጳ የስፖርትና ባህል ፊስቲቫል ብዙዎችን አገናኝቶና አስተዋውቆ የኢትዮጵያን ባህል፣ ምግብና ሌሎች የምርት ውጤቶችንም አስተዋውቆና አገባይቶ፣ ከሁሉም በላይ ኢትዮያዊነትን አጉልቶና አክብሮ የማይረሳ ትዝታ አሳድሮ አልፏል። የሚቀጥለው ዓመት ዝግጅት በፍራክፈርት ጀርመን እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ዝግጅት የታዩ ጉድለቶችና ስህተቶች ታርመውና ተስተካክለው እንደሚቀርቡ በመተማመን ብዙዎች ከርሞ ፍራንክፈርት ለመገናኛት ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW