1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሞሮኮዋ ናዶር የሚገኙ ስደተኞች ይዞታ

ሰኞ፣ ሰኔ 19 2015

ከሜሊላው አሳዛኝ አደጋ አንድ ዓመት በኋላ ከዚህ ቀደም ወደ ከተማይቱ ለመሻገር የሚፈልጉ ስደተኞች ይኖሩበት የነበረው ጫካ አሁን ሰው የለበትም ።ባለፈው ዓመት ስደተኞች የኤሌክትሪክ ንዝረት ያለው እሾሀማ የድንበር የሽቦ አጥር ዘለው በአውሮጳ ኅብረትዋ ሜሊላ ለመግባት ሲሞክሩ ከፖሊሶች ጋር በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 23 ስደተኞች ተገድለዋል።

Spanien | Migranten in der spanischen Nordafrika-Exklave Melilla
ምስል Javier Bernardo/AP/dpa/picture alliance

በሞሮኮዋ ናዶር የሚገኙ ስደተኞች ይዞታ

This browser does not support the audio element.

 
ከአንድ ዓመት በፊት ሰሜን አፍሪቃ ሜዴትራንያን ባህር አጠገብ የምትገኘዋን የስፓኝዋን የሜሊላን ከተማ የድንበር አጥር ዘለው ለመግባት በሞከሩ ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ስደተኞችና በድንበር ጠባቂ ፖሊሶች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ጉዳት የደረሰባቸውም ነበሩ። በርካቶች ደግሞ እስከዛሬ በእስር ላይ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ በአካባቢው በሚገኝ ደን ውስጥ እየኖሩ እጣ ፈንታቸውን ሲጠባበቁ ነበር የዶቼቬለዋ ዱንያ ሳዲቅ እንደዘገበችው ግን ከአንድ ዓመት ወዲህ በአካባቢው ብዙ ለውጦች አሉ። 

ለአብዛኛዎቹ ስደተኞች ድኅነት ረሀብ እና ተስፋ ማጣት መራር እውነታዎች ናቸው። የስፓኞቹ ሴኡታና ሜሊላ በሞሮኮ የተከበበቡ ብቸኞቹ አፍሪቃን ከአውሮጳ ጋር በየብስ የሚያገናኙ የአውሮጳ ድንበሮች ናቸው። የእነዚህ ከተሞች ድንበሮች በአውሮጳ ኅብረትና በሞሮኮ የጋራ ድንበር ጥበቃ በሚደረግላቸው ብዙ ሜትሮች ከፍታ ባላቸው እሾሀማ የድንበር የሽቦ አጥሮች የተከለሉ ናቸው። አምና በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የሜሊላውን የድንበር አጥር ዘለው ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ  ከሞትና ከአካል ጉዳት ተርፈው ሌላ እድል እናገኝ ይሆናል በሚል ተስፋ በአካባቢው በሚገኝ ደን ውስጥ የሚኖሩም ነበሩ ።የዶቼቬለዋ ዱንያ ሳዲቅ በዓመቱ ጎብኝታቸው ነበር።  
የስፓኝዋን የሜሊላ ከተማን የድንበር አጥር ዘለው ወደ ከተማዋ ለመሻገር በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሞሮኮዋ በናዶር ከተማ ሆነው ይጠባበቃሉ። ከሜሊላው አሳዛኝ አደጋ አንድ ዓመት በኋላ ከዚህ ቀደም ወደ ከተማይቱ ለመሻገር የሚፈልጉ ስደተኞች ይኖሩበት የነበረው ጫካ አሁን ሰው የለበትም ። በውስጡ ያረጁ ፍራሾች ልብሶች የውሐ ማያዣዎች ሌሎች እቃዎች አሁንም እዚያው ይገኛሉ።ባለፈው ዓመት ስደተኞች  የኤሌክትሪክ ንዝረት ያለው እሾሀማ የድንበር የሽቦ አጥር ዘለው በአውሮፓ ኅብረትዋ ሜሊላ ለመግባት ሲሞክሩ ከፖሊሶች ጋር በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 23 ስደተኞች ተገድለዋል።  የሞሮኮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በምህጻሩ AMDH የድንበር ጠባቂ ባለሥልጣናት ላይ ከባድ ክሶችን አቅርቧል
ከዓመት በኋላ አሁን ሜሊላን የምታዋስነው የሞሮኮዋ ከተማ ናዶር ጸጥ ብላለች። ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት እንደነበረው በከተማይቱም ይሁን በድንበሩ አቅራቢያ በሚገኝ ደን ውስጥ ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት የመጡ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች አይታዩም ይላል ከጊኒ ተሰዶ ናዶር የሚገኘው ተገን ጠያቂ ሙሳ። የ30 ዓመቱ ሙሳ በአንድ በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ሳህን እና ሌሎች የምግቤቱን ቁሳቁሶች ማጠብ ነው ስራው። ምንም እንኳን እዚያ መቆየት የሚያስችለው ወረቀት ቢኖረውም ኑሮ በዚያ ቀላል አይደለም ይላል። 
«ሁሉ ነገር የተገደበ ነው። በፈለጉ ጊዜ ከቤት ወጥቶ መሄድአይቻልም። ያን ማድረግ የሚቻለው ከመሸነው። እስከ ምሽቱ 2 ሰዓትና ሦስት ሰዓት መጠበቅ አለብህ. እንኳን ፖሊስ እንዳያየን ተሸሽገን ግሮሰሪ ሄደን እቃ የምንገዛው።ያለበለዚያ ግን ወይ ያስሩናል አለያምወደ ሌላ ቦታ ይወስዱናል።» 

ምስል AMDH

ሙሳ ባለቤትና አንድ ሴት ልጅ አለው።ልጁ ከወራት በኋላ ሦስት ዓመት ይሆናታል። ሰሜን ሞሮኮ ለጥቁር አፍሪቃውያን በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ  ወደ ስፓኝ ልኳቸዋል። ወደዚያ እንዲሄዱም 4500 ዩሮና ፈጣን ጀልባ ነው የሚያስፈልገው ይላል። ስፓኝ የሚገኙ ባለቤቱና ልጁ በአንድ የእርዳታ ድርጅት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።ሙሳ አሁን ምን እንደሚያደርግ ግራ ገብቶታል። እርሱ ለሁለት ዓመት ጫማ ውስጥ ኖሯል።የሰዎች አሻጋሪ ገንዘቡን ወስዶበታል። እርሱ ራሱ የተገን ጠያቂ ወረቀት እያለው  ታስሮ ነበር። እናም ናዶር የመቆየት ሀሳብ የለውም  
«ገበያ ሄደህ እቃ መግዛት ስትፈልግ የእቃው ዋጋ አንድ ድርሃም ሆኖ ለኛ የሚሸጡልን ግን በሁለት ድርሃም ነው። ጥቁር ከሆንኩ ብዙ መክፈል አለብህ»
ኦስማኔ ባ ከአስር ዓመት በላይ ሞሮኮ የኖረ ሴንጋላዊ ተገን ጠያቂ ነው። ጉሩጉ በሚባለው ደን ውስጥ ለ11 ዓመታት ኖሯል። አስር ጊዜ ያህል ወደ አውሮፓ ለመምጣት ሞክሮ አንዴም አልተሳካለትም።ያኔ ይበላው የነበረ ምግብ ከቆሻሻ መጣያ የሚገኝ፣ የሚጠጣውም ውኃ እንዲሁ በሽንት የተበከለ እንደነበርና ይህም በሽተኛ እንዳደረገው ይናገራል። ሁለት ልጆች ያሉት ኦስማኔ ባ ዛሬ ግንየመኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ የራሱ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አለው። ድርጅቱም በሞሮኮ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት የመጡ ስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከት ነው።በዓለም ዙሪያ የስደተኞችን ጉዳይ በሚመለከቱ ጉባኤዎችም ላይ ይሳተፋል። 
«የአውሮጳ ኅብረት በናዶር ስራው በደንብ ተሰርቷል ይላል። አሁን ጫካ ውስጥ ምንም ስደተኛ የለም ።ይህ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ትልቅ ጥፋት ነው።ጥቂቶች እዚያ የቆዩት ለ,ተለያዩ ችግሮች ተጋልጠዋል። በቱቦዎችና በደኑ ውስጥ ሙሉ ቀን ለመደበቅ ይገደዱ ነበር። እንደቀድሞው በታክሲ እንኳን እንደልብ መንቀሳቀስ አይቻልም። ከዚህ ቀደም አሳ ወይም ውኃ ይሸጡላቸው የነበሩት ሞሮኳውያንም ሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ወደ ደኖቹ መሄድ አይችሉም።ያሁሉ አሁንም የለም። »
የአምናው የሜሊላ አሳዛኝ አደጋ ያስገኘው፣ ጥብቅ የፖሊስ ቁጥጥር ይበልጥ ማዋከብ እስር እና የረዥም ጊዜ የእስራት ፍርድ ነው።እናም አሁን በናዶር ደኖች ውስጥ አንድም ጥቁር ስደተኛ የለም ማለት ይቻላል። ኦስማኔ ባ እንደሚለው በተለይ ለበርካታ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ሰብዓዊው ቀውስ ግን አልተቀየረም። 

ምስል Kawe Vakil/DW

ዱንያ ሳዲ

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW