1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአዲሱ በሽታ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ገለፀ

ዓርብ፣ ኅዳር 5 2018

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ ውስጥ ተከሰተ በተባለው «ቫይራል ሄመሬጂክ ፊቨር» የተባለ በሽታ ላይ ከኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ገለፀ።የበሽታው ምልክት ያለባቸው ሰዎች በአፋጣኝ ወደ ጤና ጣቢያ እንዲሄዱም ድርጅቱ አሳስቧል።አንድ የአካባቢው ነዋሪ ግን ስለበሽታው ግንዛቤ የለም ይላሉ።

World Health Organization Logo
ምስል፦ Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

በአዲሱ በሽታ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ገለፀ

This browser does not support the audio element.

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ ውስጥ በተከሰተው «ቫይራል ሄመሬጂክ ፊቨር» የተባለ በሽታን  ከኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ  መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት በእንግሊዥኛው ምህፃሩ (WHO) ገለፀ።የበሽታው ምልክት ያለባቸው ሰዎች በአፋጣኝ ወደ ጤና ጣቢያ እንዲሄዱም ድርጅቱ አሳስቧል።ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማውስጥ «ቫይራል ሄመሬጂክ ፊቨር» የተባለ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ ከኢትዮጵያ የጤና ባለስልጣናት ጋር ተጨማሪ ምርመራዎችን እያደረገ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት በእንግሊዥኛው ምህፃሩ (WHO) ገለፀ።
እንደ ድርጅቱ በበሽታው ክስተት እና ባደረሰው ጉዳት ላይ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከክልላዊ ጤና ባለስልጣናት ጋር በቅርበት እየሰራ  ነው።
በዚህም፤ የበሽታውን መንስኤ ለማወቅ እና ተጨማሪ ስርጭት እንዳይኖር ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የመጀመሪያ ደረጃ ምላሽ ሰጪ ቡድን በማሰማራት የህክምና ቁሳቁሶችን እያቀረበ መሆኑን አመልክቷል።
እስካሁን ድረስ ስምንት በበሽታው ተይዘዋል ተብሎ የተጠረጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል፤።ያለው የድርጅቱ መግለጫ፤ መንስኤውን በትክክል ለማወቅ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቤተሙከራ  ምርመራ እየተካሄደ ነው ብሏል።

ኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን ለመደገፍም የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት በ«ቫይራል ሄመረጂክ ትኩሳት» ወረርሽኝ ምላሽ የመስጠት ልምድ ያላቸውን11 ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን ማሰማራቱንም አመልክቷል።
 የዓለም ጤና ድርጅት ለጤና ሰራተኞች የግል መከላከያ መሳሪያዎችን እና የበሽታ መከላከያ አቅርቦቶችን እንዲሁም የህሙማን እንክብካቤን እና የአስተዳደር አቅምን ለማጎልበት የሚያስችሉ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን  እያቀረበ መሆኑንም አመልክቷል። ሀገሪቱ ለገጠማት ለአዲስ የጤና እክል  አፋጣኝ ድጋፍ ለመስጠትም 300 000 የአሜሪካ ዶላር ከአደጋ ጊዜ በጀት መልቀቁን ገልጿል።
ድርጅቱ አያይዞም ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ድካም፣ማዞር፣ እና የጡንቻ ህመም፣ የመጀመሪያ ምልክቶች ናቸው ብሏል። ስለሆነም እነዚህ የበሽታው ምልክቶች ሲታዩ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ማሳወቅ እንደሚገባም ድርጅቱ አሳስቧል። ያም ሆኖ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የጂንካ ከተማ ነዋሪ በበሽታው ላይ የአካባቢው ነዋሪ ግንዛቤ እንደሌለው ያስረዳሉ።

ምስል፦ Mesay Tekelu/DW

የአካባቢው ነዋሪ የዕለተዕለት እንቅስቃሴ ለማድረግ ስጋት ውስጥ መሆኑን ነዋሪው ያስረዳሉ። ባለፈው ኅዳር 3 ቀን 2018 ዓ.ም. የፌደራል ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ በደቡብ ኢትዮጵያ«ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ያለየሔሞራጂክ ፊቨር» በሽታ መከሰቱን አስታውቀዋል።የጂንካ ከተማ ነዋሪው ግን  ስለበሽታው  ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥ  ይጠይቃሉ።
ይህንን ጥያቄ ይዘን የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር  ምንስቴር ድኤታ  ዶክተር ደረጄ ድጉማ እና የሚንስቴሩን የህዝብ ግንኙነት እና ኮምኒኬሽን ስራ አፅፈፃሚን ዶክተር ተገኔ ረጋሳ  ለማነጋገር በእጅ ስላኮቻቸው ብንደውልም ባለመነሳቱ ሃሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።
ተከሰተ የተባለውን በሽታ ምንነት እና ያደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። 
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ጂንካ ከተማ ውስጥ በተከሰተው በዚህ በሽታ የተያዙ ስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዶቼቬለ  በአካባቢው ከሚገኙ  የሕክምና ተቋማት እና ባለሙያዎች ያገኘው መረጃ ያሳያል።

ሙሉ ዝግጅጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW