ልዩ ዝግጅት፤ የ2018 ዓ.ም. ኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ በአዲስ አበባ
ቅዳሜ፣ መስከረም 24 2018
ዘንድሮ ለተከታታይ 7ኛ ጊዜ መዲናዋ አዲስ አበባ ውስጥ ተከብሮ የዋለው ኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ ማለዳውን በአባገዳዎች የወንዝ ላይ (መልካ-ኢሬፈና) ስነስርዓት ነው የጀመረው፡፡ ማልደው ኢሬቻ በሚከበርበት መስቀል አደባባይ እና አከባቢውን የሞሉት የበዓሉ ታዳሚያን ደግሞ የኢሬቻ ስርዓቱ ድምቀት ነበሩ፡፡
የበዓሉ አከባበር በአባገዳዎች ሲከፈት ሁሉም እንደየስርዐቱና ማዕረጋቸው መርቀዋል፡፡ የቱለማአባገዳ ጎበና ሆላ በዚሁ ወቅት በምረቃ ስርዓቱ ላይ ባሰሙት መልእክት ስለሰላም አስፈላጊነት አብዝተው ተጣርተዋል፡፡ “ኦሮሞ ሰላም ላንተ ይሁን፤ ሰላም ይደርብህ፤ ያለሰላም ምንም የለምና ሰላምህን አስቀድም” ሲሉ ስለሰላም አጉልተው ተጣርተዋል፡፡
ኢሬቻ እንደ የአንድነት ስሜት መገለጫ
ደጀኔ ነገዎ ከምዕራብ ሸዋ ዞን ጉደር አከባቢ ተነስተው በዘንድሮው የ2018 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ተከብሮ በዋለው ኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ ላይ ለመታደም በዋዜማው ትናንት ዓርብ አዲስ አበባ ደርሰዋል፡፡ ኢሬቻን ለማክበር ከተለያዩ አቅጣጫዎች በቡድንና በተናጠል በርካቶች ወደ መሃል አገር ስተሙ ለደጀኔ እና ለበርካታ የእሬቻ ታዳሚያን አከባበሩ የሚሰጠው ትርጉም ከፍያለ በመሆኑ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ “ኢሬቻ ማለት የኦሮሞ ህዝብ አንድነት መገለጫ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ የአገር አንድነትን ይገልጻል፡፡ ኢሬቻ ማለት መከባበር፣ መዋደድ እና እርቅ ነው፡፡ ከዚህም ስያልፍ ባህላችን ነው፡፡ ዘንድሮ በአዲስ አበባ የተከበረው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ አከባበር ከቦታው መመቻቸት ጀምሮ ደስ ያለን ድባብ አስተውለንበታል፡፡ የምትመለከተው ሁሉ አንድነታችን፣ ፍቅራችን እና ውበታችንን ለዓለም የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ ህዝብ የሚጠበቅብንም ይሄው ነውና ኢሬቻም ይህን ያመጣልናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ኢሬቻን ስያከብሩ ተሰብስበው ከመለያየትም በላይ ትርጉሙ ከፍ እንደሚል በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡
ጠይባ ሀጂ አህመድ ደግሞ ከምስራቅ ሸዋ ዞን ባቱ ከተማ ነው ለኢሬቻ አከባበር አዲስ አበባ የደረሱት፡፡ “ኢሬቻ ደስታን ያመነጫል፡ ወገንን ያገናኛል፡፡ የመጣነውም ፍቅርና መተሳሰብን ሽተን ነው” በማለት በዚህም ደስታና እርካታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
ሰፊ ከሆነው የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች የሚመጡ ታዳሚያን እንደየባህላቸውና ወጋቸው ተሰባስበው ህብር የሆነውን ባህላቸውን አሳይተዋል፡፡ ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ከቡኖበደሌ ዞን የመጡ ታዳሚያን ትኩረትን ከሚስቡ ናቸው፡፡ እንደ ባህልና ወጋቸው ልዩ ትዕይንት በሚያሳይ ባህላዊ የአከባቢው ሙዚቃ በመጫወት የበርካቶችን ትኩረት ስበዋል፡፡
ከባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ በመምጣት ኢሬቻ ላይ የታደሙት መኮ ሀጂ አደም ደግሞ ሀዳ ሲንቄ ናቸው፡፡ “የእርቅ እና መተሳሰብ መገለጫ በዓል በሆነው ኢሬቻ ሁሉም እየተደሰቱ ትመለከታለህ” ሲሉ የበዓሉን ፍጹም ሰላማዊነት አስረድተዋል፡፡
የብሔር ብሔረሰቦች ተሳትፎ
በዘንድሮ የኢሬቻ አከባበር ላይ እንደወትሮው ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ከመጡ በርካታ ታዳሚያን በተጨማሪ ከክልሉ ውጪ ተሳታፊ የሆኑ ኢትዮጵያውን እና የውጪ ጎብኚዎችም ተሳትፈዋል፡፡ ካላ ገዛኸኝ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን በመምጣት ነው በዛሬው ኢሬቻ ላይ የታደሙት፡፡ “በዚህ ያየሁት ውብ ነገር ነው፡፡ ብሔር ብሔረሰቡ ኦሮሞም ሆነ ሌላው በራሳቸው አልባሳት ደምቀው ነው የታዩት፡፡ በኦሮሞ ውስጥ ራሱ እንደየጎሳውና አከባቢው የተለያዩ አልባሳትን ነው የተመለከትኩ፡፡ በዚያ ላይ ጭፈራውም ህብር ያለው ነው” በማለት ኢትዮጵያውያን እንዲህ ባለ መድረክ ላይ ተገኝተው የባህል እና የፍቅር ብሎም የአብሮነት ጊዜ ብኖራቸው ነው ያሉት፡፡ በሚሊየን የሚቆጠር ሰፊ ህዝብ በመጣበት ሁኔታ እንዲህ ባለ ሰላም የሚጠናቀቅ በዓልም አስደናቂ ነው ያሉን የበዓሉ ታዳሚ የኮንሶ የሀገር ሽማግሌው፤ ባህል ልውውጡ እንደ ሀገርም ብሰራበት የሚል መልእክታቸውንም አኑረዋል፡፡
ከዚሁ ከአዲስ አበባ በበዓሉ የታደሙት አቶ አበበ ገላሳም ከበዓሉ ባለቤት ከኦሮሞ ህዝብም በተጨማሪ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሐየረሰቦች የተደረገው ተሳትፎ ቀልባቸውን ስቧል፡፡ “አንድነትን በዚህ መድረክ ተመለከትኩ” የሚሉት አቶ አበበ ሰዎች በዓመትም ይሁን አንድ ሆነው ሲመጡ የሚያድግ የአንድነት መንፈስ አለም ነው ያሉት፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪዋ የዘንድሮ ኢሬቻ ተሳታፊዋ ደራርቱ ቶሎሳም ስለአከባበሩ ካገሩን አስተያየት፤ “ኢሬቻ ሰዎች ያለ ብሔርና ጎሳ ልዩነት የሚሳተፉበት እየሆነ መጥቷል” ባለት ታዳጊዎች የአባቶችን አንድነት እንደ አድዋ ካሉ ታሪክ ብቀስሙ የሚል አስተያየት ነው ያጋሩን፡፡
ዶቺ ዛኮ ደግሞ ኢሬቻን ለመጎብኘት ወደ አከባበሩ ብቅ ያሉ ጃፓናዊ ናቸው፡፡ “ከባለቤቴ ጋር ከጃፓን ነው የመጣነው፡፡ ይህን ኢሬቻ በዓል ነው ለማየት የመጣነው፡፡ እጅግ ያስደነቀን ውብ ነገር ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡ የሚደንቅ ባህል ነው” ብለዋል፡፡
ቂም ይዘን እዚህ አንመጣም
ኢሬቻን ለማክበር ከአምቦ አቅራቢያዋ ጉደር ተጉዘው የመጡት ደጀኔ ነገዎ፤ “ኢሬቻ ለኛ ብዙ ትርጉም ያለው ታሪክ ነው፡፡ መስዋእትነትም ተከፍሎበታል፡፡ ብዙ አዋቂ ያጣንበት የታሪክ ውጣውረድ ውጤትም ነው፡፡ ዛሬ ፈጣሪ ምስጋና ይግባውና የእርቅ እና የአንድነት መገለጫ የሆነውን ኤሬቻን እንዲህ ባለ መልካም ስሜት ስናከብር ሁሉንም ወደኋላ ሳይሆን ወደ ፊት በማየት ስሜት ነው፡፡ ቂም ይዘን እዚህ አንመጣም፡፡ በጸጥታ እና በተለያዩ ጉድለቶቻቸው በዚህ የአንድነታችን በዓል ላይ ለመምጣት አስበው መምጣት ያልቻሉትን በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሁሉ ሞልቶ እንዲመጡ ፈጣሪ ይርዳቸው ነው የምለው” ብለዋል፡፡
አቶ ታምሩ ደገፋ ደግሞ ኢሬቻ ላይ የታደሙት ከሰበታ ነው፡፡ “ዘንድሮ ግድባችን በተጠናቀቀበት ዓመት ያየነው ትልቁ ነገር የአንድነት ዋጋን ነው፡፡ በዚህም በእሬቻ በአንድነት እንዴት እንደምናምር ተመለከትን” በማለት ባህሉ እንዲቀጥል መደገፍም አለበት ብለዋል፡፡
አበበ በሪ ደግሞ ከሚኖሩበት አሜሪካ ሜሪላንድ መጥተው ለመጀመሪያ ጊዜ በታደሙበት ኢሬቻ ስላስደመማቸው ነገር እንዲህ ነው የገለጹት፡፡ “ኦረሞ የራሱን ባህል ትሩፋቱን እያሳበት ስለሆነ ኢሬቻን በጣም ነው የተደሰትኩበት” ብለዋል፡፡ ራሱን ማንነቱን የሚወድ ህዝብ ለአገር ግንባታምይመቻል የሚል አስተያየታቸውን ነው ያጋሩት፡፡
ኢሬቻን የሚያስውበው የኦሮሞ ባህል አልባሳት
ከዝዋይ (ባቱ) ተነስተው የመጡት የኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ ታዳሚዋ ወ/ሮ ጠይባ ሀጂ በርካቶች በህብር የሚደምቁበትን የኦሮሞ ባህል አልባሳት ላይ በሰጡን አስተያየት፤ “የባህል አልባሳትን በያመቱ እናሰፋለን፤ ተስፍቶም የተቀመጠ አለ” በማለት የተለያዩ ውበት ያላቸው የኦሮሞ ባህል አልባሳት በእጅጉ የሚያስደስታቸው እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ምኞታቸውም በዚህ ውቤት ፍቅርና አንድነት ከፍ እንዲል ነው፡፡ ጥሪያቸውም በዚህ አብረን እንመር በሚል በበዓሉ ላይ መታደም ላልቻሉ ጥሪ ማቅረብ ሆነ፡፡
ኢሬቻ በመጣ ቁጥር ከበዓሉ ጋር ተያይዘዞ ከሚነሱ ውዝግቦች አንዱ የበዓሉ ከሃማኖት ጋር መያያዝ አለመያያትን የተመለከተ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኝ እና የሃማኖቱ መሪ መሆናቸውን ገልጸው አስተያየት የሰጡን፤ “አባ ገብርኤል እባላለሁ፤ ኢሬቻ እና ሃማኖት የማይጣሉም የማይጋጩም ናቸው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ሲመጣ እሱ ሰማይም የምድርም ፈጣሪ ሆኖ ሳለ በእስራኤል ሲወለድ የእስራኤላውያንን ባህል አክብሯል፡፡ እናም እኛ ከዚህ የምንማረው የግላችን ሃማኖት ብኖረን ከየትም ሃይማኖት ስንሆን ኢሬቻ የጋራ ባህላችን ብለን እንቀበላለን” ብለዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር