1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለእሑድ ኅዳር 30 የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ተራዘመ

ዓርብ፣ ኅዳር 28 2016

የፊታችን እሑድ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ሊካሄድ የታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ ለሌላ ጊዜ መራዘሙን አስተባባሪ ኮሚቴው አስታውቋል። ኮሚቴው ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰልፉ ለሌላ ጊዜ የተላለፈው መንግስት አራት የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴን ማሰሩን ጨምሮ «አሉታዊ» የተባሉ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ነው ብሏል፡፡

አዲስ አበባ የታቀደ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ
ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን ተብሎ የታቀደዉን ሰላማዊ ሰልፍ ያስተባበሩ ኮሚቴዎች መግለጫ ምስል Seyoum Getu/DW

በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና ሌሎችም አከባቢዎች በተደረጉ ጦርነቶች ሞት፣ አካል መጉደል እና የንብረት ውድመት ተከስቷል

This browser does not support the audio element.


የፊታችን እሑድ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ሊካሄድ የታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ ለሌላ ጊዜ መራዘሙን አስተባባሪ ኮሚቴው አስታወቀ፡፡ ኮሚቴው ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ጋዘጠኞችን ጠርቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰልፉ ለሌላ ጊዜ የተላለፈው መንግሥት አራት የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴን ማሰሩን ጨምሮ “አሉታዊ” የተባሉ እርምጃዎች በመወሰዳቸው ነው ብሏል፡፡ የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ግን “በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ ከሸፈ” ሲል አስታውቋል።

ኮሚቴው በዛሬ ከሰዓቱ ጋዜጣዊ መግለጫው ከ2011 ዓ.ም. ጀመሮ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና ሌሎችም አከባቢዎች በተደረጉ ጦርነቶች ሞት፣ አካል መጉደል እና የንብረት ውድመት መከሰቱን አስታውሷል፡፡ በጦርነት ሂደቱም አስገድዶ መደፈር ጨምሮ የተለያዩ በደሎች በተዋጊዎች በማህበረሰቡ ላይ መድረሱን በሰብዓዊ መብት ተቋማት ጭምር መረጋገጡንም እንዲሁ፡፡
ግጭቶቹ “ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሃገርን ለዘርፈ ብዙ ምስቅልቅል ከመዳረግ አልፎ ለውል አልባ የማፍረስ አደጋ ሊዳርግ የሚችል” ያለው የሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴው ሰልፉ የተጠራው “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላም እንዲፈቱ በማለም ነበር ብሏልም፡፡ ኮሚቴው ይህንኑን ሰልፍ ለማካሄድ የሚመለከተውን የመንግስት አካል ባሳውቅም መንግስት ሰልፉን የማክሸፍ ስራ ሰርቷል ነው ያለው፡፡ በጋራ የተዘጋጀውን መግለጫ ለጋዜጠኞች ያነበቡት ከአስተባባሪዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ዘለሌ ፀጋስላሴ ናቸው፡፡
በተነበበውም መግለጫ “መንግስት ሰላማዊ ሰልፉን የተለያዩ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ያዘጋጁት እንደሆነ በማስመሰል የሰልፉ ቀን የጸጥታ ሃይሎችን የማሰማራት ፍላጎት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ሰላማዊ ሰልፉን አቅጣጫ በማሳት አደናቅፏል” ተብሏል፡፡
በመሆኑም ኮሚቴው የሰልፉን ቀን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ መገደዱን አስረድተዋል፡፡ “የሰልፉ ዓላማ ግልጽ ነው፡፡ በአገራችን ጦርነት እንዲቆም በማድረግ የሚደርሰውን እልቂትና ውድመት ማስቀረት ነው፡፡ ሆኖም መንግስት የህዳር 30ውን አገር አዳኝ ሰልፍ ከመደገፍ ይልቅ ሰልፉን ከታለመለት ዓላማ ውጪ በመግፋቱ አስተባባሪ ኮሚቴው ለተወሰኑ ቀናት በመግፋት ሰልፉን በተሻለና በውጤታማ መንገድ ለማካሄድ መደምደሚያ ላይ ደርሷል” ነው የተባለው፡፡

ዶቼ ቬለ ስለጉዳዩ ከመንግስት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ብደውልም ምላሻቸውን ማግኘት ባለመቻሉ ጥረቱ አልሰመረም፡፡

የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ትናንት ማምሻውን ባወጣውና ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ ግን “በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ ከሸፈ” ሲል አስታውቋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

የጸጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል በመግለጫው “በውጪ ኃይሎች የሚደገፉ ፅንፈኛ ኃይሎች እና የሽብር ቡድኖች” ያሏቸው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በትጥቅ የታገዘ ግፍና ግድያ በመፈፀም የጸጥታ ችግር በመፍጠር ኅብረተሰቡን እያወኩ ነው ብሏል፡፡ ቡድኖቹ ግጭትና አለመረጋጋቱን ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ ለማስፋፋት ይንቀሳቀሳሉ በማለትም ከሷል፡፡

ዛሬ የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላቱ መግለለጫ ሲሰጡ የትናንት ምሽቱ የጸጥታና የደህንነት ግብረ-ሃይል መግለጫ በቀጥታ ይመለከታችኋልን በሚል ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ ከአስተባባሪ ኮሚቴ አባላቱ አንዱ ፖለቲከኛ የሺዋስ አሰፋ ሲመልሱም፤ “ማመልከቻ አስገብቶ እንዴት አሸባሪ ይባላል፡፡ ከኛ መካከል እንደዛ አይነት የለም፡፡ በህግ እናምናለን፡፡ መግለጫው ግን በእጅጉ ያሳዘነን መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን፡፡ እኛ ያልነው በእርሰበርስ ጦርነት የትም አንደርስምና ጦርነት ይቁም ነው፡፡ በመሆኑም መግለጫው ከኛ ጋራ ግንኙነት የለውም ብለን እናምናለን፡፡ ሰልፉንም አሁን ያራዘምነው የጭቅጭቅ መንስኤ እንዳይሆን ነው” ብለዋል፡፡

አስተባባሪ ኮሚቴው አራት የኮሚቴው አባላት በመንግስት መታሰራቸውንም በዛሬው መግለጫ ገልጧል፡፡በትናንት ምሽቱ የደህንነትና ፀጥታ ግብረ-ኃይል መግለጫም “ወደ ከተማዋ የታጠቁ ኃይሎችንና ቡድኖችን አስርጎ የማስገባት ሙከራ ያደረጉ” ያሏቸው 97 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል፡፡ዛሬ መግለጫ ለሰጠው የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ ታሰሩ የተባሉት አራት አባላቱ መንግስት ቁጥጥር ስር አዋልኩ ካለው ከነዚህ 97 ውስጥ የሚጠቀስ ነው ወይ የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ለጥያቄውም “የእኛ አስተባባሪዎች በዚያ ውስጥ ይካተቱ አይካተቱ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ምክኒያቱም ዝርዝሩ አልደረሰንም፡፡ የታሰሩብን መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ ናትናኤል መኮንን፣ ገዲና መድህን እና ካላዩ መሃሪ ናቸው፡፡ የታሰሩት ሰዎች ባጠቃላይ ግን ከ97ም እንደሚበልጥ ነው የምንገምተው” የሚል ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የትናንት ምሽቱ የፀጥታና ደህንነት ግብረ ሃይል መግለጫ መንግስት የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ለመወጣት “የማያዳግም” እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁሟልም፡፡ አክሎም በአዲስ አበባ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ግለሰቦች ማንነት ሲያብራራ፤ “የአማራ ክልል ጽንፈኛ ኃይሎች እና የሸኔ የሽብር ቡድን ታጣቂዎች” ካሏቸው ጋር የሚሰሩ ናቸው  ብሏል፡፡ ተሰውረዋል ያሏቸውንም በማደን ላይ መሆኑን በመጠቆም፤ “ሰርጎ ወደ ከተማ ገብተዋል” ካሏቸው በርካታ የጦር መሣሪያዎች፣ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች፣ ቦንቦችና የሬዲዮ መገናኛዎችም መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW