በአዲስ አበባ የመሬት መንሸራተት ስጋት
ረቡዕ፣ መስከረም 7 2018
የብርጭቆ ፋብሪካ ሚኪሊላንድ ኮንዶሚኒየም (ወረዳ 13) ነዋሪዎች ስጋት
«አስፓልቱ እንደዚህ አልነበረም እኩል ነበር ከላይም ከታችም፤ በዚያ በኩል የእግረኛ መንገድ እንደምታየው ሰምጧል» ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በተለምዶ ብርጭቆ ሰፈር ሚኪሊላንድ ኮንዶሚኒየም ነዋሪ ናቸው።
ሌላው አስተያየት ሰጪ የአካባቢው ነዋሪ ሰሞነኛው በአካባቢው እየሰፋ ነዋሪዎችንም ያሰጋው የመሬት መንሸራተት ምልክት ያሳየው መሰንጠቅ ከዝናብ መጨመር ጋር ተያይዞ ሰሞኑን አስፈሪ እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት። «ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደዚህ የሆነው ቀስ በቀስ ነው። ዝናብ ዘንቦ ጎርፍ ሲመጣ ደግሞ እየባሰበት ይሄዳል» በማለት የአካባቢው የመሬት ናዳ ስጋት ከስንጥቃቱ ጋር የፈጠረውን ፍርሃት ገልጸዋል።
ነዋሪዎችን ከስጋት ቀጣና የማሸሽ ጅማሮ
ይህ የመሬት መንሸራተት ስጋት ያሳደረውና የመሬት መሰንጠቅጎልቶ የተስተዋለበት ስፍራ አካባቢውን ከፍሎ በሚያልፈው ገደላማ ወንዝ ዙሪያ የሚገኙትን ነው። ዶይቼ ቬለ በስፍራው ተገኝቶ እንደተመለከተው በአከባቢው በተለይም የሚኪላንድ ትምህርት ቤት ኋላኛው አጥርና ብሎክ 13 የተባለው በአከባቢው ላይ የሚገኝ የጋራ መኖሪያ ሕንጻ አጥር አከባቢ የመሬት መሰንጠቅና መሸሽምልክት ታይቷል፡፡ በተመለከቱት ነገር ስጋት እንደገባቸው የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎችም ባለሥልጣናት አካባቢውን ከጎበኙ በኋላ ጠንከር ያለ ስጋት ካለባቸው የመኖሪያ ሕንጻ ነዋሪዎች እንዲወጡም መደረጉን አስረድተዋል። «ይሄ ያየኸው በጣም አስቸጋሪ ነው፤ እንደ አካባቢውም ስጋት አለ» ያሉን ለዘመናት በአካባቢው የኖሩ አዛውንት እንዲህ ያለን ነገር ተመልክተው እንደማያውቁ ነው የገለጹት። «ከከተማ አስተዳደሩ የተላኩ የአፈር ናሙናውን የተመለከቱ ባለሙያዎች ከፍተኛ ስጋት ያለበትን አንደኛውን የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ እንዲወጡና የሌላኛውም ሕንጻ ነዋሪዎች በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ መልእክት ተላልፏልም» ያሉት አስተያየት ሰጪው የመሬት መሰንጠቅና የናዳ ስጋቱ የሰፋው ባሳለፍነው ቅዳሜ በጣለው ከባድ ዝናብ ነው፡፡ ሌላም አስተያየት ሰጪ የአካባቢው ነዋሪ ብሎክ 13 የተባለ የአካባቢው የጋራ መኖሪያ ሕንጻ ነዋሪዎች እንዲወጡና ሌላኛውም በአጠገቡ የሚገኝ ሕንጻ ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች በተጠንቀቅ ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።
በወረዳ 14 የደረሰው የመሬት መንሸራተትና ጉዳቱ
በክፍለ ከተማው ወረዳ 14 በተለምዶ አስኮ አዲስ ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሕይወት ምንጭ ኢየሱስ ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን (JSL) ላይ እሑድ ሌሊቱን ለሰኞ አጥቢ በደረሰ የመሬት ናዳ አደጋ የጠፋ የሰው ሕይወት ባይኖርም በቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ይህን ክስተት አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የቤትክርስቲያኑ አገልጋይ ፓስተር ዘነበች ገሰሰ፤ «እሑድ ሌሊት በተለይም ወደ ማለዳው መጀመሪያ መስታወት እና ቤቶች እየተሰነጣጠቁ በሚገርም ፍጥነት ነው ወደታች የሰመጠው» ብለዋል። በዚህም የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች፣ ዕቃ ማስቀመጫ መጋዘን፣ ቢሮዎች እና መጸዳጃ ቤቶች በከፍተኛ አደጋ ተደርምሰው መስጠማቸውን ገልጸዋል።
በናዳው የደረሰው ጉዳትና ቀጣዩ ስጋት
የመሬት ናዳውን ያስከተለው የቤቶቹ መሰንጠቅ የተጀመረው ከመሬት መሰንጠቅ ምልክት ነበር ያሉት ፓስተር ዘነበች፤ ምልክቶቹ አስቀድመው ቢታዩም ቤቶችን ይዞ ወደ አምስት ሜትር ወደታች የሰመጠው መሬት ግን በፍጥነት የተከሰተ እንደሆነም ነው ያስረዱት። «አሁን የቆምንበት እና ቤቶችን ይዞ ወደ አምስት ሜትር ግድም የሰመጠው መሬት እኩል ነበር» ያሉን ፓስተር ዘነበች የመሬት ናዳውና መሰንጠቁ ሚኪሊላንድ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ከተከሰተው ጋር ተመሳሳይ ጊዜ መሾኑንና ተያያዥ ሳይሆን እንዳልቀረም ገልጸውልናል። አሁን በቀጣይነት መሬቱ እየተሰነጠቀ መሆኑ በድጋሚ ተመሳሳይ ናዳ እንዳይከሰት አስጊ ነው በማለትም በእስካሁኑ ጉዳት ብቻ ከስምንት ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ ማጋጠሙን ተናግረዋል።
ዶይቼ ቬለ በአካባቢው ዙሪያ ገቡ ላይ በተለይም ገደላማ የአካባቢው ወንዝ ጋር የተያያዙ ስፍራዎች ላይ መጠነኛ የመሬት መንሸራተትን ተመልክቷል። በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ ከመቆጣጠር አኳያ በከተማ አስተዳደሩ እየተሰሩ የሚገኙትን ሥራዎች ለመረዳት ለአዲስ አበባ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባዮች ብንደውልም ለዛሬ አልተሳካልንም።
ስጋት ላይ የሚገኙት አካባቢው ነዋሪዎች ግን «የከተማ አስተዳደሩ ኢንጂነር መጥተው አይተው ተገቢውን ምላሽ እንሰጣለን፣ በአጭር ጊዜም እናሳውቃለን» ማለታቸውን ነግረውናል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር