1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
መኪና እና መጓጓዣአፍሪቃ

በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ

ዓርብ፣ ጥር 12 2015

በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ ታክሲዎች፣ አውቶቡሶች፣ መካከለኛ ተሽከርካሪዎችና የከተማ ባቡሮች ላይ የአገልግሎት የክፍያ ሒሳብ የታሪፍ ማሻሻያ ተደረገ። ከነገ ጥር 13 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል የተባለው የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ማሻሻያ በአንበሳ እና በሸገር አውቶቡሶች ላይ ሲደረግ ከ4 ዓመታት በኋላ ነው።

Äthiopien Addis Abeba | Straße und Mobilität
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ ታክሲዎች፣ አውቶቡሶች፣ መካከለኛ ተሽከርካሪዎች እና የከተማ ባቡሮች ላይ የአገልግሎት የክፍያ ሒሳብ ወይም የታሪፍ ማሻሻያ ተደረገ። ከነገ ጥር 13 ቀን፣ 2015 ዓ. ም ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል የተባለው የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያ ወይም የታሪፍ ማሻሻያ በአንበሳ እና በሸገር አውቶቡሶች ላይ ሲደረግ ከአራት ዓመታት በኋላ ነው። ከፍተኛ የማሻሻያ ክፍያ ጭማሪው በአውቶቡሶች ላይ የተደረገ ሲሆን፤ እስከ ስድስት ብር ድረስ ጭማሪ ተደርጓል። እስከ 17 ኪሎ ሜትር ድርስ በሚወስድ የባቡር አገልግሎት ላይ ደግሞ ከነበረበት የ 3 ብር ጭማሪ ተደርጎ ሰባት ብር ሆናል።

አብዛኛዎቹ ማለትም 23 የከተማ ባቡሮቹ ከሥራ ውጪ የሆኑበት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ጽ/ቤት አገልግሎት እየሰጠ ያለው በ 18 ቱ ብቻ ሲሆን ይህም ቢሆን መጨናነቅ እና ግፊያ ያልተለየው ነው። ቢሮው በቅርቡ ሰባት ባቡሮች ከቻይና በተገኘ የ 60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ በሂደት ላይ ነኝ ሲል አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም አይነት የተመዘገቡ 9667 ተሽከርካሪዎች የከተማ ውስጥ ሕዝብ የማጓጓዝ አገልግሎት ይሰጣሉ ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ምትኩ አሥማረ በተለይ እስከ ስድስት ብር ድረስ ጭማሪ የተደረገበትን የአውቶቡስ ታሪፍ ማሻሻያ ምክንያት ገልፀዋል። ቢሮው ማሻሻያ ያደረገበት ሌላኛው የትራንስፖርት አማራጭ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ነው። በጭማሪው መሰረት አራት ብር የነበረው የ 17 ኪሎ ሜትር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ታሪፍ ወደ ሰባት ብር ከፍ ብሏል። ያም ሆኖ ግን ተቋሙ ካሉት 41 ባቡሮች ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 18ቱ ብቻ መሆናቸው አማራጮች እንዲጠቡ አድርጎታል።

ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ይታያሉምስል፦ Solomon Muchie/DW

መንግሥት የታሪፍ ማሻሻያውን ዛሬ ይፋ ቢያደርግም ከሳምንታት በፊት ከፍተኛ የሚባል የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ በተለይ አመሻሽ ላይ የታክሲ አሽከርካሪዎች በራሳቸው ፈቃድ ዋጋ ጨምረው ያስከፍላሉ። ባሉን 350 የቁጥጥር ሠራተኞች ብቻ መሰል ችግሮችን መቆጣጠር ያስቸግራል የሚሉት የቢሮ ኃላፊው ሕዝቡ ከዋጋ ተመን በላይ ባለመክፈል መብቱን ሊያስከብር ይገባል ብለዋል። ታክሲዎች በቀን ያ 25 ሊትር የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው ሳላ የተወሰኑት አገልግሎት የማይሰጡ ሆነው መገኘታቸውም ሌላው ችግር ነው።

በሥሩ አራት ተጠሪ ተቋማትን ያቀፈው የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥርን፣ የትራፊክ ማኔጅመንትን፣ የከተማ አውቶቡስ እና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎቶችን ያስተዳድራል። የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እና የሚጓጓዘው ሕዝብ ፍላጎት አለመመጣጠን በአዲስ አበባ መሠረታዊ ሊቃለሉ ካልቻሉ ችግሮች ዋነኛው ነው።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW