1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ ይፈጸማሉ የተባሉ የወንጀሎች መበራከት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2016

የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋ “በእግርና የተለያዩ ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም ቅሚያዎች ይፈጸማሉ፡፡ ወንጀሎቹ ደግሞ የሚቀነባበሩባቸው የተለያዩ ሺሻ ቤቶችና ቁማር ቤቶች ናቸው፡፡ ” ብለዋል፡

ፌደራል ፖሊስ አርማ
በአዲስ አበባ ይፈጸማሉ የተባሉ የወንጀሎች መበራከታቸውን የፖሊስ መግለጫ ያመለክታል። ምስል Seyoum Getu/DW

የአዲስ አበባ ፖሊስ አካሄድኩ ያለው ልዩ ዘመቻ

This browser does not support the audio element.


የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆኑ አከናወንኩ ባለው ልዩ ኦፕሬሽን በርካታ ተጠርጣሪዎችን ከነኤግዚቢቶቹ በቁጥጥር ስር ማዋሉንም አሳውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሚመራው የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ያሉትና ከታህሳስ 6 ጀምሮ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተካሄዱ በተባሉ የኦፕሬሽን ሥራዎች በርካታ ተጠርጣሪዎች ከልዩ ልዩ ኤግዚቢቶች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተነግሯል።


የተበራከቱ የወንጀል አይነቶች
 የሁለቱን ተቋማት ስራ መገምገማቸውን ገልጸው በዛሬው እለት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችበመዲናዋ መነሻቸውና ድርጊታቸው ልዩ ልዩ ነው የተባሉት በርካታ የወንጀል ተግባራ እንደሚፈጸሙ አብራርተዋል፡፡  በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋ  “በእግርና የተለያዩ ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም ቅሚያዎች ይፈጸማሉ፡፡ ወንጀሎቹ ደግሞ የሚቀነባበሩባቸው የተለያዩ ሺሻ ቤቶችና ቁማር ቤቶች ናቸው፡፡ ጭካኔ የተሞላባቸው ወንጀሎች ደግሞ መነሻቸው እንደነዚህ ያሉ ቦታዎች እንደመሆናቸው በተለየ ትኩረት ይሰራበታል” ብለዋል፡፡

በመግለጫው በአዲስ አበባ ከተማ መነሻ እና ድርጊታቸው ልዩ ልዩ ነው የተባሉ በርካታ የወንጀል ተግባራት እንደሚፈጸሙም ተገልጿል። ምስል Seyoum Getu/DW

   
መሰል ወንጀሎችን ለመከላከል 1 ሺህ 400 የቁማር ማጫወቻ ቤቶች እና 176 ሺሻ ቤቶች ላይ እንደ ከተማ አስተዳደሩ እርምጃ መወሰዱ ነው የተነገረው፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ለአብነትም 73 ኪ.ግ. የሚመዝን ሃሺሽ ፖሊስ ባደረገው የምርመራ ዘመቻ በቁጥጥር ስር መዋሉ በአብነት ቀርቧል፡፡ ፖሊስ እንዳመለከተው አዳጊ ህጻናት ጭምር ሰብስበው በሱስ ገንዘብ የሚሰበስቡ አሉ ነው የተባለው፡፡ ለአብነትም በቦሌ ክፍለ ከተማ 164 ታዳጊ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጥለው በአንድ ቤት ተሰባስበው አላስፈላጊ የተባለው ሱስ ውስጥ ተዘፍቀው መያዛቸው በማሳያነት ቀርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራር አባላት መግለጫ ሲሰጡምስል Seyoum Getu/DW

 

“በመዲናው ወንጀልን ለማጽዳት ስለተባለው ስምሪት”
አዲስ አበባን ከወንጀለኛ ለማጽዳት ይሰራል በተባለው በዚሁ ኦፕሬሽን (ዘመቻ) እንደ አዲስ አበባ ከተማ በሁሉም አይነት ወንጀሎች መጠነ ሰፊ የተባለ ዘመቻ መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ ባዕድ ነገር ቀላቅለው ለተመጋቢ የሚያቀርቡትን ጨምሮ በአንድ ቤት ውስጥ አንድ ጊቢ ተከራይተው በ190 ሲም ካርድ የኦንላይ ማጭበርበር ላይ የተሰማሩት መያዛቸውም ነው የተገለጸው፡፡ የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊው ረ/ኮሚሽነር ዓለማየሁ አያልቄ በመግለጫው እንዳብራሩትም በተለይ በዚህ ክፍለ ከተማ በእጅ ስልክ ንጥቂያ ላይ የተለየ ያሉት ትኩረት ተሰጥቶ ወንጀለኞችን የማደን ስራ ተሰርቷል፡፡ “በተለይ መገናኛ አከባቢ ሞባይል ተቀማሁ የሚሉ በርካቶች እንደመሆናቸው በዚህ ላይ በተለየ ትኩረት ሰርተን በልዩ ኦፕሬሽኑ ከ190 በላይ ስልኮችን ከሚቀሙትና ተረካቢዎች ጋር በቁጥጥር ስር አውለናል” ነው ያሉት፡፡
ልዩ በተባለው በዚህ ኦፕሬሽን የተለያዩ የውጭ አገራት የገንዝብ ኖቶች በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ ከነበሩበት ተይዟል ያሉት ደግሞ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረ/ኮሚሽነር ዳመና ተስፋዬ ናቸው፡፡ “የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ ሀሰተኛ ገንዘቦች፣ ስርቆት ላይ የተሰማሩ ተሸከርካሪዎች እና የጦር መሳሪያዎች ተይዘዋል” ብለዋል፡፡
ከተሸከርካሪዎች በተጨማሪም በመኪና እቃ ስርቆትና ተቀባይነት ላይ የተሰማሩም መያዛቸው ተነግሯል፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደሩ ከ1 ሺህ 700 በላይ የተሰረቁ የእጅ ስልኮች ልዩ በተባለው በዚህ ኦፕሬሽን መያዛቸውም ተነግሯል፡፡
በዚሁ ተደርጓል በተባለው ኦፕሬሽን ከ5 ሺህ 500 በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉም እንዲሁ ተነግሯል፡፡
ስዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW