1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአዲስ አበባ ገበያ የጤፍ ዋጋ ለምን አሻቀበ?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ መጋቢት 6 2015

በአዲስ አበባ የጤፍ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች፣ ነጋዴዎች እና የወፍጮ ቤት ባለቤቶች ይናገራሉ። አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጤፍ "የትም ቦታ ላይ ጨምሯል ነው እንጂ ቀንሷል የሚባል ነገር የለም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የነዋሪዎችን አቅም ከተፈታተነው የዋጋ ጭማሪ ባሻገር በገበያው የተከሰተው የጤፍ እጥረትም ሌላ ችግር ነው።

Bildergalerie Äthiopien Teff
ምስል DW/J. Jeffrey

በአዲስ አበባ ገበያ የጤፍ ዋጋ ለምን አሻቀበ?

This browser does not support the audio element.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአስራ አንዱ ክፍለ ከተሞች በሰባቱ በሚገኙ ገበያዎች አንድ ኪሎ ጤፍ የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ ገበያው በቅጡ እንዳልተረጋጋ አሳይቷል።  በመረጃው መሠረት የኪሎ ጤፍ ከፍተኛው ዋጋ 75 ብር ነው። በአራዳ ክፍለ ከተማ በሚገኙ ገበያዎች ቀይ ጤፍ በኪሎ 47 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሰራጨው መረጃ ይጠቁማል። የከተማ አስተዳደሩ መረጃ ነጭ ጤፍ፣ ሰርገኛ እና ጥቁር ጤፍ በገበያው ያላቸውን ልዩነት በግልጽ የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ ባሻገር አንድ ኪሎ ጤፍ በአንድ ከተማ የተለያዩ ገበያዎች በከፍተኛ ልዩነት እየተሸጠ እንደሚገኝ የሚጠቁም ነው።

ወይዘሮ ሐረገወይን ግሩም ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጠቀሰው ዋጋ ሰሞኑን አንድ ኪሎ ጤፍ አልሸመቱም። ወይዘሮዋ የቤተሰባቸውን የወር ቀለብ ነጭ ጤፍ የሚሸምቱት ከነጋዴዎች ተቀብለው ፈጭተው ለገበያ ከሚያቀርቡ ወፍጮ ቤቶች ነው።  "የጤፍ ዋጋ በየቀኑ ነው የሚጨምረው" የሚሉት ወይዘሮ ሐረገወይን "ከአንድ ወር በፊት አንድ ኪሎ ጤፍ በ70 ብር እየተሸጠ ነበር። አሁን ስምንት ብር አካባቢ ጨምሮ 78 ብር ሆኗል" ሲሉ ተናግረዋል።

የጤፍ ዋጋ ማሻቀብ በተለይ ለመንግሥት ሠራተኞች እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚቀመስ አልሆነም። በዋና ከተማዋ አንድ እንጀራ እስከ 16 ብር ይሸጣል። ምስል DW/J. Jeffrey

እንደ ወይዘሮ ሐረገወይን ሁሉ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሌሎች ስድስት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላለፉት ሁለት ሣምንታት ገደማ ጤፍ የሸመቱበት ዋጋ የከተማ አስተዳደሩ ካሰራጨው መረጃ ጋር የሚጣጣም አይደለም። ጤፍን ጨምሮ በእህል ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ማሕደር አሰፋ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ "ከ75 ሺሕ ብር ጀምሮ እስከ 85 ሺሕ ብር ድረስ ይሸጣል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በነጭ ጤፍ ላይ ብቻ በአንድ ኪሎ የ20 ብር ጭማሪ በገበያው መታየቱን ለዶይቼ ቬለ ያስረዱት ወይዘሮ ማሕደር "ቀደም ሲል 57 እና 58 ብር የሚሸጠው ጥቁር ጤፍ አሁን 70 ብር በላይ ገባ። በ65 ብር ገደማ ይሸጥ የነበረው ማኛ ጤፍ አሁን 85 ብር ገብቷል" ሲሉ የገበያውን ኹናቴ ያስረዳሉ።

እንደ ወይዘሮ ማሕደር ካሉ ነጋዴዎች ጤፍ ተቀብለው ለሸማቾች ከሚሸጡት አቶ አብርሀም አበበ ናቸው። "ከዛሬ ወር በፊት ከ68 ብር እስከ 70 ብር የምንሸጠው ጤፍ አሁን የ20 እና የ30 ብር ጭማሪ አድርገን የምንሸጠው" ሲሉ ተናግረዋል። ምንጃር የሚመረት ጤፍ በአንጻሩ አንድ ኪሎ 95 ብር እንደሚሸጥ የገለጹት አቶ አብርሀም "ዝቅተኛው ሰርገኛ ጤፍ አንድ ኪሎ እስከ 75 ብር ድረስ ይሸጣል። ጥቁር ጤፍ ደግሞ የምንጃር አንደኛው 80 ብር ይሸጣል። ከዚያ በታች ያለው የጅሩ የሚባል አለ 75 ብር ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ጤፍ ፈጭተው ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡ ነጋዴ አንድ ኪሎ የምንጃር ጤፍ እስከ 95 ብር መግባቱን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ሰርገኛ እና ጥቁር የሚባሉ የጤፍ አይነቶችም ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶባቸዋል። ምስል DW/J. Jeffrey

ገበያውን በቅርብ ከሚያውቁ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ በላይ ቶሌራ በእርግጥም በአዲስ አበባ ካለፉት ወራት አኳያ የጤፍ ዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ ይስማማሉ። የምዕራብ ሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በላይ  "ዋጋው በእርግጥ አምና በዚህ ሰዓት ከምንገዛበት፤ ከሁለት እና ከሶስት ወራት በፊት ከምንገዛበት ዋጋ ላይ ከ600 እስከ 1,000 ብር ጭማሪ አለው" ይበሉ እንጂ የዋጋ ጭማሪው ስንዴ፣ ፓስታ እና መኮረኒን በመሳሰሉ ምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ ጭምር የተፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል። "የዋጋ ንረቱ አልተረጋጋም" የሚሉት አቶ በላይ  "የብር የመግዛት አቅሙ እየወረደ የምርት ዋጋ በጣም ከፍ እያለ የመጣ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባን የጤፍ ሸማች ቅርቃር ውስጥ የከተተው ግን በገበያው የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ብቻ አይደለም። አቶ አብርሀም መጋዘን እና ወፍጮ ቤትን በሚያጣምረው መደብራቸው እንደ ወትሮው የጤፍ ክምችት የላቸውም። ጤፍ "የለም አልቋል ማለት ይቻላል። አሁን ያለን 20 እና 30 ኩንታል ጤፍ ብቻ ነው። በፊት እስከ 300 ኩንታል ጤፍ እንይዝ ነበር" የሚሉት አቶ አብርሀም  "እኛ በምንም በምንም ብለን እያስገባን ነው እንጂ አንዳንድ ቦታ የምናውቃቸው ጓደኞቻችን ጋ ስንደውል ቅዳሜ ለት፤ አርብ ዕለት ጨርሰው የዘጉ አሉ። ባዶ ምንም የሌለበት ቦታ አለ" ሲሉ ተናግረዋል።

የጤፍ የግብይት ሰንሰለት አርሶ አደሮች፣ ሰብሳቢዎች፣ ጅምላ ሻጮች እና ቸርቻሪዎችን ያካትታል። እነዚህ ነጋዴዎች ለአዲስ አበባ የሚቀርበውን ጤፍ የሚሸምቱት በዋናነት ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ነው። ነጋዴዋ ወይዘሮ ማሕደር ግን "እኛ የምናመጣው ከጎጃም ነው። ጎጃም ደግሞ መንገድ ዝግ ነው። እህል እየገባ አይደለም። ከዚያ መስመር አሁን ምንም አይነት እህል ወደ አዲስ አበባ እየገባ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።

ነጋዴዎች ለአዲስ አበባ የሚቀርበውን ጤፍ የሚሸምቱት በዋናነት ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ነው። ምስል Reuters/T. Negeri

ጤፍ ከነጋዴ ተቀብለው ወይም ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አስመጥተው በመፍጨት ለደንበኞቻቸው የሚሸጡት አቶ አብርሀም አበበም "የጎጃም ጤፍ ከቆመ ሁለት ሣምንታት አልፎታል። እየገባ አይደለም። ነጋዴው የሚጠቀመው እሱን ነው። ቀለብተኛውም ቢሆን በስፋት ይጠቀመዋል። አልፎ አልፎ ከሰሜን ሸዋ ነበር የሚገባው። ሰሜን ሸዋ ደግሞ ጥራት ያለው ጤፍ እንጂ ብዛት የለም" ሲሉ አስረድተዋል።

ጤፍ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ ታግዷል የሚለውን መረጃ ዶይቼ ቬለ ከተለያዩ ነጋዴዎች ሰምቷል። ይሁንና ጉዳዩን በገለልተኝነት ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት አልሰመረም። አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ በሚለው የፖለቲካ ትኩሳት ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞች እንግልቶች ይገጥሟቸው የነበረ ቢሆንም በግብርና ምርቶች ላይም ይሁን ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚፈጠር እክል እምብዛም ነበር።

"ሰሞኑን እኛ ከኦሮሚያ ክልል፤ አማራ ክልል ከዚህ በፊት የሚያቀርቡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኒየኖች፣ መሠረታዊ ማኅበራት ላይ እየተነጋገርን ነው። [ጤፍ] ወደ አዲስ አበባ እያመጣን ነው" የሚሉት አቶ በላይ ቶሌራ "አዲስ አበባ መግባት ተከልክሏል የሚባለው መሠረተ ቢስ ነው፤ ምርት ከዚያም ከዚህም እየገባ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ምርቱን እጁ ላይ የማቆየት፤ ወደ ገበያ ያለማውጣት ችግር ነው የነበረው። እሱን እሱን በየደረጃው ያለው አስተዳደር እየተነጋገረ ነው" የሚሉት አቶ በላይ ከኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች ጤፍ ወደ አዲስ አበባ "እያመጣን ነው" ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ በላይ በአዲስ አበባ የተፈጠረው የጤፍ እጥረት በቅርብ ይረጋጋል የሚል ተስፋ አላቸው። ለዚህም እርሳቸው የሚመሩትን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙት አስሩ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚያደርጉትን ጥረት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። እንደ ወይዘሮ ሐረገወይን ያሉ ሸማቾች ግን የአንድ ኪሎ ጤፍን ዋጋ አይቀመስ ያደረገው ጉዳይ ምን እንደሆነ አልገባቸውም። ጤፍ "የትም ቦታ ላይ ጨምሯል ነው እንጂ ቀንሷል የሚባል ነገር የለም" የሚሉት ወይዘሮ ሐረገወይን "አሁን እኮ መኖር አልቻልንም። ለመኖር ተቸግረናል። የመንግሥት ሠራተኛ እና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ሰው በጣም ከብዶታል" ሲሉ ጫናውን ያስረዳሉ።

 

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW