በአዲስ አበባ ጉዳት ያደረሰው ጎርፍና መንስኤዉ
ሰኞ፣ መስከረም 12 2018
በአዲስ አበባ ጉዳት ያደረሰው ጎርፍና መንስኤዉ
በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ወራት በተደጋጋሚ የደረሰዉ ድንገተኛዉ የጎርፍ አደጋ በሰዉ ህይወት እና የንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። በከተማዋ ውስጥ በግንባታ ላይ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በተፈጥሮም የዘንድሮ ዝናብ ጠንክሮ መታየቶ ተነግሯል። ለመሆኑ በከተማዋ እየተስተዋለ ላለው የጎርፍ አደጋ መበራከት የኪነህንጻ ባለሙያዎች ምን ይላሉ? የከተማዋ ባለስልጣን ግምገማ እና የመፍትሄ አቅጣጫስ ምንን ያመለክታል?
አዲስ አበባ ውስጥ ዘንድሮ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተለይም ባለፉት ሁለት ወራት ማለትም በወርሃ ነሐሴ እና መስከረም የተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች በንብረት ላይ የጎላ ጥፋት ስያስከትሉ ታይተዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን ከአንድ ሳምንት በፊት የከተማዋ ተራራማ ስፍራዎች ላይ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በሰው ቤት ውስጥ በብዛት ሰርጎ የገባው ከባድ ጎርፍ በርካቶችን አስደንግጧል፡፡
የአዲስ አበባው የጎርፍ መንስኤ በባለሙያዎች አስተያየት
በከተማዋ ከወትሮ በተለይ ዘንድሮ የተባባሰው የጎርፍ አደጋ መንስኤዎቹ የተለያዩ ናቸው የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ህንጻ መምህር የሆኑት አርክቴክት ዮሓንስ መኮንን፤ መንስኤውን ይዘረዝራሉ፡፡ “በከተማዋ ጎርፍ የበዛበት አንደኛው ምክንያት በከተማዋ ውስጥ ውኃ ስያሰርጉ የነበሩ ቦታዎች በብዛት በከተማዋ የመንገዶች ግራና ቀኝ ወደ አለታማ ኮንክሪት ተቀይረዋልና ውኃን የማሰረግ እድላቸው እየጠበበ መጥቷል” የሚሉት አርክቴክት ዮሓንስ፤ በከተማዋ በግንባታ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ በተለይም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ውኃን ከትሮ ለመያዝ ካለው ፍላጎት ጋር ተያይዞ አነስ ያሉ ግድቦች ስገደቡ ጎርፍ ከፍ ብሎ ስመጣ ማስተንፈሻ ባለመዘጋጀቱ ካለው የዲዛይን ስህተት ጋር ተያይዞ ጎርፍ ከተፈጥሯዊ ተዳፋት በመውጣት አደጋ ስፈጥሩ ተስተውሏል ነው የሚሉት፡፡ በመንገዶችም ዳር የውሃ መቀበዳያ ማፋሰሻዎች በበቂ ሁኔታ ውኃን ተቀብለው እንዲያሳልፉ ተደርገው ባለመሰራታቸው ምክንያት ብሎም ባለው አነስተኛ የክትትል ስራ የተነሳ አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ቦታዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ተስተውሏል ሲሉም አስተያየታውን አጋርተዋል፡፡
ስለጎርፍ ክስተቱ የከተማ አስተዳደሩ ግምገማ
በመዲናዋ በስፋት ለተስተዋለውየጎርፍ አደጋ በክረምቱ ከተጠበቀ በላይ ዝናብ መጣሉ እንደ አንዱ መንስኤ እንደሚወሰድ የሚያነሳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፊናው፤ አደጋውን ለመቀነስ ግን የተሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ይጠቁሟል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የከተማ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስከያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤ “በተለይም ከነሃሴ አጋማሽ በኋላ ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንደሚመጣ የሜትሮሎጂ መረጃ ስያሳይ ስለነበር እኛ ከክሬምቱ መግባት በፊት ነው የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችን ስንሰራ የነበረው” ብለዋል፡፡ “ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ላይ የማቅለያ ስራ መስራትና መከታተል” ከተማ አስተዳደሩ ከሰራባቸው የጎርፍ አደጋን ለማቅለል የተሰራ ስራ መሆኑን የገለቱት ኢንጂነር ወንድሙ፤ “በቅርብ ጊዜ የጎርፍ አደጋ የተከሰተባቸው ቦታዎች አስቀድሞ የቅድሜ ጥንቃቄ ስራ ያልተወሰዱባቸው ናቸው” ሲሉም ክፍተቱን ስለፈጠረው ጉዳይ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡
ቅስበታዊው የኮተቤ-ወሰን አከባቢ ጎርፍ
ኢንጂነር ወንድሙ የክረምቱ ዝናብ በራሱ ይዞት የሚመጣው ተረፈ ምርቶች በርካቶች እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፤ በአንዳንድ አከባቢዎች የጎርፍ ማፋሰሻ ቱቦዎች መዘጋታቸው ጎርፉ ተፈጥሯዊ ተዳፋቱን ለቆ በመውጣት አደጋ እንዲያደርስ መንስኤ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ “አስቀድመን የማቅለያ ስራ የወሰድንባቸው አከባቢዎች ላይ እንደዚህ አደጋዎች ሳይከሰቱ አልፈዋልም” ያሉት ባለሙያው፤ በቅርቡ መስከረም ወር ውስጥ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ስላደረሱ የጎርፍ አደጋዎች ስያሽረዱም “በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወሰን ግሮሰሪ ተብሎ የሚጠራ ሰፈር አከባቢ በትልቅ ግንድ ወንዝ ውስጥ መኖር ምክንያት ማፋሰሻውን ሰብሮ በመውጣት የሰው ቤት ውስጥ የገባው ጎርፍ አንድ ቤት ውስጥ ገብቶ በዚያ ውስጥ የነበሩትን ስድስት ሰዎች ላይ የህይወት አደጋ ያደረሰው ነው” በማለትም በመዲናዋ ውስጥ የተፈጠሩትን በጎርፍ የደረሱ የንብረት ጉዳትንም ጭምር በቀጣይ እንዳይከሰቱ አፋጣጭ መፍትሄም ለመስጠት እንደሚሰራ ነው ማብራሪያው ያመለከተው፡፡
አዜብ ታደሰ
ታምራት ነገራ
ሥዩም ጌቱ