በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአገራዊ ምክክር ጉባኤ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች
ሰኞ፣ ግንቦት 25 2017
ባሳለፍነው ዓርብ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሮ ትናንት በተጠናቀቀው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ የሃማኖትና ሲቪክ ተቋማት፣ የመንግስት ተወካዮች፣ ሚዲያ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት እንዲሁም ማህበራት እና ታዋቂ ሰዎችን ያካተተው የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ በአጠቃላይ 879 ተወካዮችን በአንድ መድረክ ያገናኘ ነው፡፡ በዚህም እንደ አገር ለገጠሙ ችግሮች መንስኤ ናቸው የተባሉ ጉዳዮች በምክክር ተለይተው ትናንት እሁድ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀርበው ርክክብ ተደርጓልም፡፡
በዚህ የምክክር መድረክ ተሳታፊ ከነበሩት አንዱ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማካሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዑስታዝ ካሚል ሸምሱ ናቸው፡፡ “በተለያየ ደረጃ ሲቀርቡ ከነበሩ አጀንዳዎች አንዱ የዚህን አገር ችግር በመሰረታዊነት ይፈታል ተብሎ የሚታመነው የህገመንግስት እና ከህገመንግስት ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች ናቸው” ያሉት ዑስታዝ ካሚል ሸምሱ የመንግስት ስርዓትና አወቃቀር ምን መምሰል አለበት የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች በመድረኩ ተነስተው ለምክክር በአጀንዳነት መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም የህብረተሰብ ጥያቄ የሆኑ በርካታ ሃሳቦች በመድረኩ መንሸራሸራቸውን ነው ያነሱት፡፡
የኢትዮጵያ እውነተኛ ችግር ምልክቶቹ ሳይሆን መሰረቱ ላይ ነው የሚል አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ ፖለቲከኛ ኢብሳ ነገዎ በምክክር መድረኩ ተነስተው ትኩረት የሳቡ ባሏቸው ሃሳቦች ላይ ይህን ብለዋል፡፡ “የመንግስት አመሰራረት ላይ ችግር ስለነበር ችግሩ እስካሁን ቀጥሏል” ያሉት አቶ ኢብሳ ከአገር ምስረታው በኋላ እንደ አገር ምክክር ተደርጎ አለመታወቁ የቋንቋ፣ የብሔር እና የመሬት ጥያቄን ማስነሳቱን በማንሳት በአስተያየታቸው ጠቃቅሰዋል፡፡ በኃይል ላይ የተመሰረተ የአገር ግንባታ የዴሞክራሲ ጉዳይን ማስነሳቱንም የገለጹት አቶ ኢብሳ ይህ አሁን ለተፈጠሩ ጭቅጭቆችና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ምናልባትም መሰረታዊ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡ በመሆኑም ችግሮቹን ለመፍታት ትልቅ ውይይት እንደሚስፈልግ ገልጸዋል፡፡
አስተያየት ሰጪ ተሳታፊዎቹ አክለውም በመድረኩ የተነሱ አጀንዳዎች አንገብጋቢነትን በማስመልከት በሰጡን አስተያየታቸው፤ “ሂደቱም ሆነ የተነሱ አጀንዳዎች ተቀርጸው ለኮሚሽኑ ርክክብ የተደረገው ተስፋን የሚጭር ነው” ያሉት ዑስታዝ ካሚል በመድረኩ ያልተነሳ አስፈላጊ ጥያቄ የለም ባይ ናቸው፡፡ ከህገመንግስት ማሻሻያ፣ የማንነት ጥያቄ፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ አጠቃቀም፣ ባንዲራ እና የድንበር አከላለል፣ ታሪክና ትርክት ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው በስምንት አበይት ክፍሎች ተሰንደው ለኮሚሽኑ መተላለፋቸውንም አንስተዋል፡፡
የኦሮምኛ ቋንቋን የፌዴራል የስራ ቋንቋ የማድረግ ጥያቄን ከተነሱ ሃሳቦች እንደማሳያ አድረገው አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ኢብሳ ነገዎ በፊናቸው ለሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች የህገመንግስት ማሻሻያን በመሰረታዊ ጥያቄነት መቅረቡን አመልክተዋል፡፡ ለሚነሱ የወሰኖች አከላለልም ሆነ ለሌሎች ጥያቄዎች መሰረታዊ ምክክር እንደሚያስፈልጋቸውም በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡
ትናንት የፌዴራል ባለድርሻ አካላቱን የምክክር አጀንዳ ከተረከቡ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፈሰር መስፍን አርዓያ የቀረቡትን አጀንዳዎች በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበው በመገባደድ ላይ ባለው የአገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት ትግራይ ክልል እና በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ላይ ማተኮር አበይት ቀሪ ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ ከዚሁ ጎን ለጎን እስካሁን በሂደቱ ተሳታፊ ያልሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የታጠቁ አካላትን ተሳታፊ የማድረጉ ጉዳይም እንደሚሰራበት ነው የገለጹት፡፡ በዚህም “እነሱም ወደዚህ አጀንዳቸውን በማምጣት በቀጣይ በሚደረገው የአገራዊ ምክክር ጉባኤ እነሱም ተሳታፊ ሆነው ሁሉም አሸናፊ ሆነው የሚወጣበትን እንደሆን ነው ጥሪ የምናቀርበው” ብለዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ