በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋለው የአማራ ክልል የእጣንና ሙጫ ሐብት
ዓርብ፣ ጥር 2 2017ተደጋጋሚ ጦርነትና ግጭት በሚደረግበት በአማራ ክልል እጣንና ሙጫ በተገቢዉ መንገድ ማምረት እንዳልቻሉ የማሕበራት አባላትና ባለሥልጣናት አስታወቁ።በአማራ ክልል የዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከፍተኛ እጣንና ሙጫ ከሚመረትባቸዉ አካባቢዎች አንዱ ነዉ።የማሕበራት አባላትና ባለሥልጣናት እንደሚሉት ቀድም ሲል የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል የሚደረገዉ ግጭት ሐብቱ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ አደናቅፈዉታል።የሰቆጣ ዝናብ አጥር ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ ሀብቱ ትኩረት አልተሰጠውም ይላል።
“በዋግኽምራ 10 ቀበሌዎች የእጣንና ሙጫ ሀብት ይገኛል” የሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል
በአማራ ክልል እጣንና ሙጫከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዱ ነው። ሀብቱ በዋናነት በአበርገሌ፣ በዝቋላና በዳህና ወረዳዎች ቆላማ አካባቢዎች እንደሚገኝ በሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርመር ማዕከል የደን ተመራማሪ አቶ ግርማ ንጉሤ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። እምቅ ሀብት በሦስቱም ወረዳዎች ቢኖርም ግን ህብረተሰቡ ለህብቱ ያለው ግንዛቤ ያነሰ በመሆኑና ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገው ጥረትም ትኩረት እንደሚያንሰው ገልጠዋል።
የእጣንና ሙጫ ዛፎች ለማገዶ እየዋሉ ነው
ህብረተሰቡ ሀብቱን አልምቶ ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ የጣን ዛፎችን ለአጥር፣ ለማገዶ፣ ለባህላዊ መድኃኒትና ለእንሣት ምግብ እያዋለው እንደሆን በጥናት መረጋገጡን አቶ ግርማ ጠቁመው ሀብቱም ትኩርት በማጣት እየተመናመነ ነው ብለዋል፡፡
ተከዜ ዋልዋ በተባለ እጣንና ሙጫ ማህበር ውስጥ እንደነበሩ የተናገሩ አንድ የማህበሩ አባል፣ በበኩላቸው በአካባቢው ያለው የፀጥታ እጦት ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰሩ እንዳደረገባቸው አስረድተዋል።
“... የሚመረተው እታች ተከዜ ወንዝ አፋፉ ነው፣ በአሁኑ ሰዓት ምኑ ይመረታል፣ ቤት ዘግቶ እግዚኦ ማህረን ክርስቶስ ነው እንጂ፣ ፋኖውም መከላከያውም በትይዩ ነው ያሉት፣ እዛ ሄዶ ማን ይሰራል?፣ ተዳክሟል፣ ብዙ ዛፍ ነበረ ለጣን፣ ለሙጫ ይሆናል እየተባል፣ አሁን የለም” ብለዋል፡፡
የፀጥታው ሁኔታ ሀብቱን እንዳንጠቀም እንቅፋት ሆኖብናል” የወርዳ ኃላፊዎች
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዳህና ወረዳ አካባቢና ደን ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት መንግስቴ በበኩላቸው አሁን ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ምክንያት ሀብቱ ካለባቸው 5 ቀበሌዎች መካክል ከሚገኙ ማህበራት ውስጥ ድጋፍና ክትትል ማድረግ የተቻለው በ2ቱ ብቻ መሆኑን ገልጠዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የፀጥታ ችግር እንደሆነ አብራርተዋል።
የዝቋላ ወረዳ የእጣንና ሙጫ ማህበራት ኃላፊ ወ/ሮ ዘውድ ዘለላው ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በወረዳው እጣንና ሙጫ የማምረቱ እንቅስቃሴ ተዳክሞና ሀብቱም ሲጎዳ መቆየቱን ጠቁመው እሁን ማህበራቱን እንደገና የማደራጀት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በጦርነቱ ወቅት የእጣን ዛፎች እየተቆረጡ ለሌላ አገልግሎትም ሲውሉ እንደነበርና አሁን እንዲያገግሙ ህብረተሰቡን የማንቃት ሥራ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ አካባቢና ደን ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ ለማ በዳህናና ዘቋላ ወረዳዎች አንዳንድ አካባቢዎች ገብቶ ለመስራት ቦታዎቹ በታጣቂዎች የተያዙ በመሆናቸው አስቸጋሪ ነው ሲሉ ገልጠዋል።
የእጣንና ሙጫ ልማት በአበርገሌ ወረዳ በቅርቡ ይጀመራል ስለመባሉ
በአበርገሌ ወረዳ ሀብቱ እንዳለ ቢታወቅም እስካሁን ግን ወደሥራ እንዳልተገባ የወረዳው አካባቢና ደን ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅረማሪያም ዓለማየሁ ተናግረዋል።
ይህን በተመለከት የብሔረሰብ አስተዳደሩ አካባቢና ደን ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ ለማ እንዳሉት ሀብቱን በአበርገሌ ወረዳም አልምቶ ለመጠቀም እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አበርገሌ፣ ዳህናና ዝቋላ ወረዳዎች ከሚገኙ 60 ቀበሌዎች ውስጥ በ10 ቀበሌዎች የእጣንና ሙጫ ዛፎች እንደሚገኙ የሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል ያካሄደው ጥናት ያሳያል።
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ