1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፋር ነዋሪዎችን ያሰጋው ተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 7 2017

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ነዋሪ አሁን አሁን በእየእለቱ በአራት ሰዓት ግድም ልዩነት የመሬት ንዝረቱን ከፍተኛ ስሜት ማስተናገድ እየተለመደ ከመምጣት ይልቅ አደጋዎችን ማስከተል መጀመሩ በእጅጉ አስግታል፡፡ትናንት ለሊት 5፡11 አከባቢ ተከስቷል የተባለው ርዕደ መሬት አስደንጋጭና ከባድ ነበር

የመሬት መንቀጥቀጡ የአካባቢዉን ነዋሪዎች ሥነ ልቡናና እንቅስቃሴ እያወከዉ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ
በተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ ከደረሰባቸዉ የአፋር ክልል አካባቢዎች የአዋሽ 7 ኪሎ ከተማ አንዱ ነዉምስል DW/Y. Geberegzihaber

በአፋር ነዋሪዎችን ያሰጋው ተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ

This browser does not support the audio element.

የአፋር ክልልን የተለያዩ አካባቢዎች ሰሞኑን በተደጋጋሚ የመታዉ የመሬት መንቀትቀጥ የነዋሪዎችን ስነልቦና  እያወከ ነው፡፡አደጋዉ የደረሰባቸዉ አካባቢዎች ነዋሪዎች እንደሚሉት የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በየቀኑ ተደጋግሞ ከመሰማትም አልፎ ጉዳትም እያደረሰ ነዉ።ትናንት ምሽት በድጋሚ በከፍተኛ መጠን የተሰማው የመሬት መንቀጥቀጥ የኤሌክትሪክ ምሰሶ በመጣሉ የእሳት አደጋም ተፈጥሯል፡፡የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ ትናንት ለሊት እና ዛሬ እኩለ ቀን አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ ተሰምቷልም፡፡

በአፋር ክልል የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አከባቢዎች ባለፉት 11 ቃናት ተደጋግሞ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በተለይም በአፋር ክልል የነዋሪዎችን ህይወት እያወከ ይገኛል፡፡

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ነዋሪ አሁን አሁን በእየእለቱ በአራት ሰዓት ግድም ልዩነት የመሬት ንዝረቱን ከፍተኛ ስሜት ማስተናገድ እየተለመደ ከመምጣት ይልቅ አደጋዎችን ማስከተል መጀመሩ በእጅጉ አስግታል፡፡ በተለይም ትናንት ለሊት 5፡11 አከባቢ ተከስቷል የተባለው ርዕደ መሬት አስደንጋጭና ከባድ ነበር፡፡ “በዚሁ አቅራቢያችን መልካ ወረር በምትባል ከተማ በትናንት ለሊቱ የመሬት መንቀጥቀጥ የመብራ ፖል ወድቆ የእሳ አደጋ አስከትሏል፡፡ ቤቶች እየተሰነጣጠቁ በተለይም ተማሪዎች በአዋሽ ፈንታሌ ከውጪ ተቀምጠው ለመማር ተገደዋልና ባጠቃላይ ህዝቡ ላይ በዚህ ተከታታይ የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ የስነልቦና ቀውስ ነው እየደረሰ ያለው” ብለዋል፡፡

የትናንት ለሊቱ የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባ ድረስ ከፍተኛ ንዝረት አስከትሎ በርካቶችን አስደንግጧል፡፡ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት አከባቢም በአዋሽ ፈንታሌ የተከሰተው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰምቷል፡፡ ይህ በዛሬው እለት የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.6 አካባቢ እንደሆነም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ኤሊያስ ሌዊ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ኢቢሲ አረጋግጠዋል። በአካባቢው ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንቅስቃሴ አሁንም እንዳልቆመ ያስረዱት ባለሙያው፤ በአዋሽ ፈንታሌ እና ሳቡሬ ከተማ መካከል ላይ ያለው የቅልጥ ዓለት እንቅስቀሴ እስከቀጠለ ድረስ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቱ የመቀጠል እድል እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

የአዋሽ አርባ ከተማ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ይህ ዛሬም የተደገመው ከባድ ንዝረት እንደማታው ባይሆንም የከፋ ነው ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል፡፡ “በአዋሽ አርባ እስካሁን ያስከተለው ጉዳት ባይኖርም የባታው በተለይም ድጋጤ ፈጥሯል፤ ደግሞም በየቀኑ ነው ንዝረቱን የምንሰማው” ሲሉም አስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ባለሙያዎች የመሬት መንቀጥቀጡ ሊቀጥል እንደሚችል አስታዉቀዋልምስል Seyoum Getu/DW

አብደላ የተባሉ የአዋሽ ሰባት አስተያየት ሰጪም ሃሳባቸውን አከሉ፤ “በተለይም የማታው በጣም ከባድ ነበር፡፡ በዚህ በጣም ነው የወዛወዘን፡፡ እቃ ሁሉ ተደረማምሷል፡፡ እንደማህበረሰብ ከፍተኛ ስነልቦናዊ ጫና እያደረሰ ማታ መተኛትም አልቻልንም” ብለዋል፡፡

አስተያየት ሰጪ ነዋሪዎቹ በተለይም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥና አስቀድሞ ከማስገንዝብ አኳያ በባለሙያዎች ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራም እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡ “በተለይም በአዲስ አበባ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች አስቀድሞ ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ካላስጨበጡ እጅግ በጣም ስነልቦናዊ ቀውስ እየመጣ ጉዳትም እየተከተለ ነው” ሲሉም ሃሳቦቻቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ስለተከታተለው ርዕደ መሬት ዛሬ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ባለሙያዎች ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማከል ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ከዚህ በፊት ባለፈው ሳምንት ውስጥ አስተያየታቸውን የሰጡን በአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የስነምድር ባለሙያው ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጋ ሰሞነኛው የመሬት መንቀትቀጥን ተከትሎ ከስምጥ ሸሎቆው የሚፈልቅ ውሃ የቀይባህርና ኤዴን ባህረሰላጤን ኢትዮጵያን ከሚያቋርጠው ስምጥ ሸለቆ ጋር በሂደት የመገናኘቱ ምልክት ሲሆን የርዕደ መሬቱም ቀጣይነት ሊኖረው የሚችል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ “በዝግመተ ለውጥ አሁን መሬት እየተሰነጠቀ፤ መንቀጥቀጡም እየቀጠለ ውሃ በትንሽ በትንሹ እየሰፋ ቀይባህርን ከአፋር ጋር በማገናኘት በመታሃራ ዝዋና ሃዋሳ አርባምንች ጋር የሚገናኝ ሃይቅ የመፈጠሩ ምልክት ነው” ሲሉም እያደር ሊፈጠር የሚችለውን የተመራማሪዎች ግምት አስቀምጠዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW