1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በአፋር ክልል ለሰብአዊ ርዳታ “ከዩኤስኤይድ ብዙ ድጋፍ ይገኝ” የነበረ ቢሆንም ተቀዛቅዟል

ኢሳያስ ገላው
ቅዳሜ፣ ግንቦት 2 2017

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) የሚያደርገው ድጋፍ ከቆመ በኋላ በአፋር ክልል የሰብአዊ ርዳታ ጉዳይ ሥጋት ፈጥሯል። ለሰብአዊ ርዳታ ፈላጊዎች “ከዩኤኤይድ ብዙ ድጋፍ ይገኝ” የነበረ ቢሆንም መቀዛቀዙን የክልሉ ባለሥልጣን ለዶቸ ቨለ ተናግረዋል። ተቋሙ ለግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የሚሰጠው ድጎማ መቆም የሠራተኞች ስንብት አስከትሏል።

በአፋር ክልል ርዳታ የተቀበሉ ሰዎች
ባለፉት ስድስት አመታት በአፋር ክልል ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ በሰሜኑ ጦርነት በቅርቡም የተከሰተዉ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ተደጋጋሚ የሆነ ድርቅ በርካቶችን ሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊ እንዲሆኑ አስገድዷል። ምስል፦ Claire Nevill/WFP via AP/picture alliance

በአፋር ክልል ለሰብአዊ ርዳታ “ከዩኤኤይድ ብዙ ድጋፍ ይገኝ” የነበረ ቢሆንም ተቀዛቅዟል

This browser does not support the audio element.

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ መቋረጥ እንደ አፋር ክልል ላሉ ከፍተኛ አርብቶ አደር ማህበረሰብ የሚኖርባቸው እና በተደጋጋሚ በድርቅ ለሚጎዱ አካባቢዎች ችግሩ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል። በክልሉ ይቀርብ የነበረ ድጋፍ መቋረጥም ለአርብቶ አደርም ሆነ ከፊል አርብቶ አደሮች የጎላ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ በመንግሥት የሰብአዊ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ የሰብአዊ ድጋፍ ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

“እንደ ክልል ብዙ ተፅኖ አለዉ” የሚሉት ባለሙያ “የዝናብ እጥረት ሲኖር ከፍተኛ ድርቅ አለ። ምክንያቱም ከብቶች ካልተመገቡ ወተት ማህበረሰቡ አያገኝም” ሲሉ አስረድተዋል። “እርዳታዉ የቆመዉ ሙሉ በሙሉ ነው” የሚሉት የሰብአዊ ድጋፍ ባለሙያ “ሪሊፍ የሚባለዉ ፕሮግራም በኛ አካባቢ የለም” ሲሉ አክለዋል።

የሰራተኞች መሰናበት

በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከፍተኛዉን ድጋፍ የሚያገኙት ከዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) በመሆኑ ሰራተኞቻቸዉን ማሰናበት መቀጠላቸዉን ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ከሥራቸው ከተሰናበቱ የግብረ ሰናይድ ድርጅቶች ባልደረቦች መካከል አንዱ “የተዘጋም የፈረሰም ድርጅት አለ” ይላሉ። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ግለሰብ የቀጠራቸው የግብረሰናይ ድርጅት ለሥራው የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ ከዩኤስኤይድ ያገኝ እንደነበር ገልጸዋል።

ለትግራይ ተፈናቃዮችና ችግረኞች የሚሰጠዉ ርዳታ ማነስ ያስከተለዉ ሥጋት

ነገር ግን የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ሲያቆም “ከክፍያ ነፃ እረፍት [ውሰዱ] ተባልን። ከዚያ በኋላ የአገልግሎት ውሰዱ አሉን” በማለት የገጠማቸውን አብራርተዋል። ከሥራቸው የተሰናበቱት የቀድሞው የግብረ ሰናይ ድርጅት ባልደረባ “እኛ ብቻ ሳንሆን አብዛኛዉ ድርጅት በአፋር ክልል ቁሟል” ይላሉ። 

በአፋር ክልል ይቀርብ የነበረ ድጋፍ መቋረጥም ለአርብቶ አደርም ሆነ ከፊል አርብቶ አደሮች የጎላ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ በመንግሥት የሰብአዊ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ የሰብአዊ ድጋፍ ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል፦ AP Photo/picture alliance

በአፋር ክልል ከፍተኛ የሆነ የሕጻናት መቀንጨር ችግር እንዳይፈጠር የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ይደግፋቸዉ የነበሩ ተቋማት አልሚ ምግቦችን ያቀርቡ ነበር። በዩኤስኤይድ የሚደጎመው የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በአፋር ክልል በተመጣጠነ ምግብ እጦት ለተጎዱ ሕጻናት እስካሁን ድረስ አልሚ ምግቦች እያቀረበ እንደሆነ የሚናገሩት የሰብአዊ ድጋፍ ባለሙያ “ከዚህ በኋላ ከቆመ ብዙ ልጆች ወደ መቀንጨር እንደሚሄዱ” ሥጋታቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል። 

የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ክልሉን መልቀቅ

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ስራ ማቋረጣቸዉን የሚገልፁት በአፋር ክልል ፋይናንስ ቢሮ የሀብት ማሰባሰብ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ አወል መሀመድ “ለረዥም ዓመታት የተወሰኑ የልማት ፕሮጀክቶች ነበሩ። እነዚያ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ኃላፊው በክልሉ ከተዘረጉ የአጭር ጊዜ የሰብአዊ ርዳታ ፕሮጀክቶች መካከል “የተወሰኑት ለሦስት ወራት ቆይተው” ሥራ የጀመሩ መኖራቸውን ተናግረዋል። ይሁንና እነዚህም ቢሆኑ “የቀራቸው የተወሰኑ ወራት” ናቸው።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እርዳታ መቋረጥና ተፅዕኖው

ባለፉት ስድስት አመታት በአፋር ክልል ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ በሰሜኑ ጦርነት በቅርቡም የተከሰተዉ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ተደጋጋሚ የሆነ ድርቅ በርካቶችን ሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊ እንዲሆኑ አስገድዷል። 

በአፋር ክልል በየአመቱ የሰብአዊ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው “አስቸኳይ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ” የሚሉት ኃላፊው “የሰብአዊ ርዳታ ምላሽ አስፈላጊ ነው። መሠረታዊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አወል መሀመድ “ከዩኤኤይድ ብዙ ድጋፉ ይገኝ ነበር። አሁን ተቀዛቅዟል” ሲሉ ተናግረዋል። 

የአፋር ክልል ሞቃታማ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አወል “አንዳንድ ጊዜ ድርቅ የሚከሰትበት ጊዜ አለ። እነዚያ በቋሚነት ድጋፍ ይፈልጋሉ” በማለት አስረድተዋል። ሰብአዊ ርዳታ ፈላጊዎች የሚኖሩባቸው “ወረዳዎች ይህንን ነገር ማጣታቸው ተጽዕኖ ይፈጥራል” የሚል ሥጋት አላቸው። 

ኢሳያስ ገላው 
እሸቴ በቀለ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW