በአፋር ክልል ወደ ትግራይ የሚሄዱ የጭነት መኪናዎች ኬላዎች ላይ ተዘግተዋል።
ዓርብ፣ ግንቦት 22 2017
ሸቀጣሸቀጥ ጭነው ወደ ትግራይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች፥ ወደ ትግራይ እንዳይገቡ በአፋር እና አማራ ክልል በሚገኙ የፍተሻ ጣብያዎች መከልከላቸው ተገለፀ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በዚህ ክልከላ ጉዳይ ከፌደራል መንግስቱ ማብራሪያ ጠይቋል።
ያነጋገርናቸው መነሻቸው ከአዲስአበባ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች አድርገው ሸቀጦች እና ሌሎች ንብረቶች ጭነው ወደ ትግራይ ጉዞ ላይ የነበሩ ሹፌሮች እንደገለፁልን፥ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ጉዟቸው መስተጓጐሎች መታየት መጀመራቸው ያነሳሉ። መነሻው ከአዲስአበባ አድርጎ በአፋር ክልል በኩል ወደ ትግራይ ጉዞ ላይ የነበረ ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገው 'የኤፍ ኤስ አር' ሹፌር እንደሚለው መንገድ ላይ ያሉ በርካታ ኬላዎች ጭነት ይዞ ወደ ትግራይ መጓዝ እየከለከሉ ነው ብለዋል።
ሌላው ዶቸቬሌ ያነጋገራየው ብርሃኑ አለምሰገድ የተባለ ሸቀጦች የሚያመላልስ የከባድ መኪና ሹፌር፥ በአፋር እና በአማራ ክልል በኩል ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች ሸቀጦች ይዘው ለሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ማለፍ መከልከሉ ገልፀውልናል። በዚህም በወልደያ አካባቢ እንዲሁም በአፋር ክልል ሰርዶ በርካታ ተሽከርካሪዎች ጭነት ይዘው ቆመው እንዳለ ጨምረው ገልፀውልናል።
በዚህ ጉዳይ ዙርያ ትላንትለፌደራል መንግስቱ የሚመለከታቸው አካላትደብዳቤ የፃፈው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ንግድና ኤክስፖርት ኤጀንሲ ወደ ትግራይ ክልል የተለያዩ ሸቀጦች ይዘው በአፋር ክልል መስመር የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ካለፈው ግንቦት 18 ቀን ጀምሮ ሰርዶ በሚገኝ የፍተሻ ጣብያ ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ እንደተከለከሉ 'ከተለያዩ ምንጮች ሰምተናል፥ በምን ምክንያት እንደተከለከሉ ማብራርያ እንዲሰጠን' ሲል ይጠይቃል። ከፌደራል መንግስቱ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ምላሽ እንደሚጠብቅም አክሏል።
በዚህ ክልከላ ምክንያት መንገድ ላይ ቆመው ያሉ ሹፌሮች ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው ይጠይቃሉ። ከዚህ በፊትም ወደ ትግራይ ይገባ የነበረ ነዳጅ ተቋርጦ መቆየቱ መዘገባችን ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከፌደራል ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚሊዮን ኀይለስላሴ
ታምራት ዲንሳ
ፀሀይ ጫኔ