1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
መቅሰፍትአፍሪቃ

በአፋር ክልል የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ጉዳት

ኢሳያስ ገላው
ሰኞ፣ ጥቅምት 3 2018

በራህሌ ወረዳ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት በቡሬ እና ዓስጉቢ ቀበሌዎች በርካታ ቤቶች ፈርሰዋል። በአደጋው ዕድሜው 12 ዓመት የሆነ ልጅ ሕይወት ያለፈ ሲሆን ሌሎች ስድስት ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል። በመሬት መንቀጥቀጡ ከ43 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ፈርሶባቸዋል።

የአፋር መሬት መንቀጥቀጥ
በአፋር ክልል የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በርካታ ቤቶችን አፈራርሷልምስል፦ Esayas Gelaw/DW

በአፋር ክልል የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ጉዳት

This browser does not support the audio element.

 

ባለፉት ስድስት ወራት በኤርታሌ አካባቢ የተከሰተዉ የተለየ የመሬት መንቀጥቀጥ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ እየታ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአፋር ክልል ባራሕሌ ወረዳ ከትናንት በስተያ ምሽት በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ። በአደጋውም አንድ የ12 ዓመት ታዳጊ ሕይወት ሲያልፍ፤ ስድስት ሰዎች ላይም ጉዳት ተመዝግቧል። ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮበነበረው ርዕደ መሬት ምክንያት ከ43,000 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በቡሬ፣ ዓስጉቢ ቀበሌዎች ተፈናቅለዋል። የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ኑሩ መሀመድ በአደጋው በርካታ ቤቶች መፍረሳቸውን ገልፀው አሁንም የርዕደመሬቱ ስሜት በመኖሩ ስጋት ላይ መውደቃቸውን ይናገራሉ።

‹«ያሉት ቤቶች ሁሉም ፈርሰዋል።  አሁን ሰውም በጣም ስለተጎዳ የሚበላም የሚጠጣም የለም። ገና አሁን ዶዘር እየጠየቅን ነው። እየተቆፈረ ካልወጣ በቀር ዕቃ ለማውጣት አስቸጋሪ ነው። አሁን የመንቀጥቀጡ ስሜት ስላለም እንደማታው ባይሆንም ስጋት አለን። ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ ቤቶችም እየፈረሱ ነው።»

በአፋር ክልል በተደጋጋሚ የሚከሰት ርዕደ መሬት በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነዉ

ጉዳቱ የደረሰበት የባራሕሌ ወረዳ አስተዳዳሪም አቶ አሊ ሁሴን በርዕደ መሬት መለኪያ 5.6 በተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ43,000 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ገልፀው ይህ ርዕደ መሬት ያልተጠበቀ እና ዝግጅት ያልተደረገበት ነው ብለዋል።

«ጉዳቱ የደረሰው 2 ቀበሌ ነው በቡሬ፣ ዓስጉቢ ላይ 43,000 በላይ ማኅበረሰብ ተፈናቅሏል ቀላል እና ከባድጉዳት ሲርስምአንድ ሰው ሞቷል፡፡ ትልቅ ጉዳት ያስተናገደው ምሽት 200 ሰዓት ላይ የነበረው ርዕደ መሬት ነው። ሳይጠበቅ፣ ሳይገመት የመጣ ነው፤ የተለመደ አይደለም።» 

አሁን በአካባቢው ዝናባማ የአየር ጠባይ በመኖሩ እና እነኝህ 43,000 ተፈናቃዮች ከአደጋ ለመሸሽ በሜዳ ላይ ሰፍረው በመገኘታቸው የምግብ እና የመጠለያ ድጋፍ ማድረግ ይገባል የሚሉት አቶ አሊ ሁሴን የክልሉ መንግሥት እና ሌሎች የረድኤት ተቋማት እንዲያግዟቸው ይጠይቃሉ።  

በመሬት መንቀጥቀጡ ከፈራረሱት ቤቶች በከፊል ምስል፦ Esayas Gelaw/DW

ከ 43 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ተፈናቅለዋል

«ድጋፎችን ከክልል እየጠበቅን ነው ድጋፍ ያስፈልገናል። የመጠለያ፣ የምግብ፣ ዝናባማ ጊዜ ስለሆነ አሁን እየዘነበነው።  ንዝረትም አለ፤ ከ20 ደቂቃ በፊት ተሰምቷል። እኛ አሁን ኮማድ ፖስት አቋቁመን የተወሰነ ድጋፍ ጀምረናል። የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ይደግፉናል ብለን እንጠብቃለን።» 

አሁን በባራሕሌ ወረዳ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከአፋር ክልል ውጭ በመቀሌ እና ውቅሮ መሰማቱን የሚገልፁት የከርሰ ምድር ጥናት ባለሙያ እና የኢትዮጵያ አስጎብኝዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዕንቁ ሙሉጌታ አካባቢው በተፈጥሮው የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካል በመሆኑ በተደጋጋሚ ለርዕደ መሬት ተጋላጭ ነው ይላሉ። በተለይም በባለፈው ዓመት ከመስከረም ወር ጀምሮ በፈንታሌ ወረዳ የነበረው ርዕደ መሬት ይህ ቀጣይ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።

‹‹የዛሬ ዓመት ፈንታሌ ላይ የጀመረው የመሬት የመሰንጠቅ የርዕደ መሬት ወይም የመሬት መሰበር ሁኔታ ነው። ቀጣይነት ኖሮት ወደ ባራሕሌ አባባሁ፤ መቀለ ውቅሮ፤ አካባቢ የተሰማው የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ወይም ስምጥ ሸለቆ የተሰበረባቸው ቦታዎች ናቸው። መስመሩ አንድ ዓይነት ነው። ይሄ ሄዶ ሄዶ ቀይ ባሕር ይደርሳል።»  

በባራሕሌ ወረዳ የተከሰተው ርዕደ መሬት ቀጣይነት ሊኖረው ይችልላ የሚሉት አቶ ዕንቁ ሙሉጌታ ማኅበረሰቡን ከአካባቢው ማራቅ እና ሜዳ ላይ የማስፈር ተግባር ሊሠራ ይገባል ይላሉ። 

«የመጀመሪያ ጥንቃቄ እንዴት ማድርግ እንዳለበት ለማኅበረሰቡ ማሳየት ያስፈልጋል። ከቦታ ቦታ ተጨናንቆ መንቀሳቀስ የለበትም። በቅርብ ርቀት ማኅበረሰቡ ሳይረበሽ ሕንጻዎችን በመሸሽ ነጻ ሜዳ ላይ መስፈር አለባቸው። በተነፃፃሪነት ርዕደ መሬቱ ከደረሰበት ቦታ 50 ኪሎ ሜትር መውጣት ያስፈልጋል።»

ኢሳያስ ገላው

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW