1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፋር የጨው አምራቾች ቅሬታ ፣ የክልሉ መንግሥት ምላሽ

ሐሙስ፣ መስከረም 17 2016

ሕበሩ በ2013 ጀምሮ ያመረተዉን ጨዉ እንዳይሸጥ በመከልከሉ 150 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የጨዉ ምርት እየባከነበት መሆኑን አስታዉቋል።የክልሉ የማዕድን ቢሮ ኃላፊ ግን ማሕበሩ ለቢሯቸዉ ያቀረበዉ አቤቱታ የለም ብለዋል

የጨዉ ምርት
በአፋር ክልል ከሚመረተዉ ጨዉ በከፊልምስል DW/M. Haileselassie Brhane

የዶቢ ጨዉ አምራቾች ማሕበርና የአፋር ክልል ዉዝግብ

This browser does not support the audio element.

 

በአፋር ክልል የዶቤ ጥሬ ጨው አምራቾች ማሕበር በክልሉ ባለሥልጣናት ያለ አግባብ ጫና ሥለተደረገበት «ከፍተኛ+ ላለዉ ኪሳራ መዳረጉን አስታወቀ።ማሕበሩ  በ2013 ጀምሮ ያመረተዉን ጨዉ እንዳይሸጥ በመከልከሉ 150 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የጨዉ ምርት እየባከነበት መሆኑን አስታዉቋል።የክልሉ የማዕድን ቢሮ ኃላፊ ግን ማሕበሩ ለቢሯቸዉ ያቀረበዉ አቤቱታ የለም ብለዋል።ማሕበሩ ከ 2013 ዓ . ም ጀምሮ ያመረተውን ጥሬ ጨው ለግብይት እንዳያቀርብ ክልከላ አደረጉብኝ ባላቸው የክልሉ ባለሥልጣናት ምክንያት እስከ 150 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ምርት ለብክነት እንደተዳረገበት እና መፍትሔ እንዲሰጠው ለአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና የጎሣ መሪዎች ጭምር ቢያስረዳም መንግሥት ምላሽ ሊሰጠው እንዳልፈቀደ አስታውቋል። 

ለቀረበው አቤቱታ ምላሽ የሰጡት የአፋር ክልል የማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ በህኔ በክልሉ የጨው ምርት ችግር እንደሌለ ገልፀው ማሕበሩ ለቢሮው ያቀረበው ቅሬታም ሆነ አቤቱታ የለም ሲሉ ገልፀዋል። እያንዳንዱ የጨው አምራች መንግሥት ባወጣው የግብይት ድልድል መሠረት እንዲሠራ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት እኒሁ የክልሉ ባለሥልጣን በግለሰብ ባለሃብቶች እና ድርጅቶች ቁጥጥር ሥር የነበሩ የጨው ምርት ሥራዎች ላይ "ሙሉ ሪፎርም ተደርጓል" በማለት የቅሬታው ምንጭ ይህ መሆኑንና የማምረቻ ቦታዎች ለአካባቢው ወጣቶች እና ሴቶች መሰጠቱ ጥፋት እንዳልሆነና አቤቱታው ተቀባይነት እንደሌለው ገልፀዋል።

ከአፋር ክልል የሚመረተዉ ጨዉ በጦርነቱ ወቅት ወደ ገበያ መቅረብ አልቻለም ነበርምስል DW/M. Haileselassie Brhane


የጥሬ ጨው አምራቹ ማሕበር ቅሬታ 

አፋር ክልል ልዩ ልዩ ማዕድናት ያሉት አካባቢ መሆኑ ይነገራል። ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያን የሚመግበው የገበታ ጨው በአፍዴራ፣ በዶቢ እና ሌሎችም የክልሉ ስፍራዎች በስፋት ይመረታል። የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሚያወጣው ድልድል መሠረት ምርታችንን ለገበያ እናቀርባለን ያሉት አምራቾች ይሁንና በራሳቸው ለሚፈልጉት አካል ምርታቸውን ለግብይት የማቅረብ መብት እንደሌላቸው እና ሕጋዊ ባይሆንም አሠራሩም እንዳልፈቀደለቻው ገልፀዋል። 

ተበደልኩ የሚለው የዶቤ ጥሬ ጨው አምራቾች ማሕበር ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሁሴን አሊ ምርታችን ክፍያ ትፈጽሞለት አይነሳም፣ ክፍያ እየተከፈለን አይደለም፣ ከ 2013 ዓ . ም ጀምሮ ደግሞ ምርታችንን ለገበያ እንዳናቀርብ በአፋር ክልል መንግሥት ተከልክለናል ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
ከ 2013 ጀምሮ "ገበያ ላይ መዋል የነበረበት 3 ሚሊየን 600 ሺህ ኩንታል ጨው ለገበያ እንዳናውል በመከልከላችን አጥተናል" ያሉት እኒህ ሰው ድርጊቱ "ኢ-ሰብዓዊ" እንደሆነም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
ይህ የጥሬ ጨው አምራች ማሕበር አባላቶቹ ወደ ዶቢ ሲሃዱ እንደሚታሰሩ ፣ አሁን ያለው ሁኔታ ለደህንነታቸው ጭምር አስጊ መሆኑንም በምሬት ገልፀዋል። 

ጨዉ፣ ከተወዳጅ ቅመሞች አንዱምስል AFP/Getty Images

የአፋር ክልል ባለስልጣናት ምላሽ


የአፋር ክልል የማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ በህኔ ለዚህ ቅሬታ ምላሽ ሰጥተዋል። "እያንዳንዱ አምራች በወር ላይ ምን ያህል ኩንታል እንደሚያቀርብ ይታወቃል። ስለዚህ ከዚህ በፊት ይሸጡበት የነበሩት መንገዶች የተለያዩ መንገዶች አሉ። በኮንትሮባንድም፣ በተለያዩ ጥቁር ገበያ ፣ የመንግሥትም ግብር የማይገኝበት። ሙሉ ሪፎርም ተፎደርጓል ጨው ላይ የነበሩት በብቸኝነት የተያዙ፣ በድርጅቶች የተያዘ። ማቅረብ አልቻልኩም ቅሬታ አለኝ ብሎ ወደ እኛ የቀረበ አንድም አካል የለም"። ብለዋል
የአፋር ክልል የኮሙኒኬሽን አገልግሉት ኃላፊ አቶ መሐመድ ዓሊ በግለሰቦች በብቸኝነት ተይዞ የነበረ የጨው ሀብት ላይ ማስተካከያ በማድረግ ለወጣቶች እንዲሰጥ በመደረጉ መሰል ቅሬታዎች ተበራክተዋል ይላሉ።
"የዚያው አካባቢ ነዋሪዎች ምንም ጥቅም አያገኙም። እዚያው ዳር ተመልካች ነበሩ። የእነሱን ጨው በሞኖፖል ይዞ የሚጠቀመው ሌላ አካል ነበር። ይህንን ጨው አለአግባብ ይጠቀሙ በነበሩ ሰዎች ይበዘበዝ ነበር። የክልሉ መንግስት ሪፎርም ካደረገ በኋላ ይህንን ትክክል አለመሆኑንአፋር ከራሱ ሀብት እንዲጠቀም ፣ ዶቢ ላይ ወጣቱ እያነሳ ያለውን ቅሬታ መልስ እንዲያገኝ ተደርጓል" ሲሉ መልስ ሰጥተዋል 

ቅሬታ አቅራቢው ማሕበር 400 አባላት ያሉት ምሆኑን ገልጾ አቤቱታውን ለማዕድን ሚኒስቴር፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ማቅረቡን ብሎም መፍትሔ አገኛለሁ ብሎ እንደሚጠብቅ ለዶቼ ቬለ አስታውቋል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW