በኢትዮጱያ የሀገር አቋራጭ አዉቶብስ አሽከርካሪዎች ፈተና
ዓርብ፣ ሰኔ 27 2017
አሽከርካሪ እሸቱ በላይ ባለፉት 6 ዓመታት የሐገር አቋራጭ አውቶቡስ ሾፌር ሆኖ በተለያዩ ጦርነቶች ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ተሳትፏል፡፡ እሱና ጓደኞቹ በተሳተፉባቸው ግዳጆችም በርካታ ጓደኞቹን በሞት እንዳጣ ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ የእነኝህን በሞት የተለዩ አሽከርካሪዎች ቤተሰቦቻቸው ዛሬ ላይ ኑሮ ቢከብዳቸውም ይህንን ችግር የሚካፈል አካል ቀርቶ ሞታቸውን በአግባቡ የሚነግራቸው የለም ይላሉ፡፡
‹‹ከህልውና ዘመቻ ጀምሮ ያለው የሰላም ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዘመቻ በሄድንበት ጊዜ የሞቱ ብዙ ጓደኞች አሉኝ፡፡ የተረዳም የለም፤ እናርዳ ብንል እንኳን ለማንም አልተነገረም፡፡ ቤተሰቦቻቸው ግን አውቀዋል፡፡ ምንም የሚያደርጉት ነገር ግን የለም፡፡››
የሾፌሮቹን መብት ለማስጠበቅ የተቋቋመዉ ማህበር ስራ አለመስራት
ሌላው ለዶቼቬሌ አስተያየቱን ያጋራው አሽከርካሪም የሀገር አቋራጭ ሾፌሮችን ደህንነት ለመከታተል እና ለመተጋገዝ የተቋቋመው የሾፌሮች ማህበር ስራውን በአግባቡ እየሰራ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የአሽከርካሪዎችን ዋስትና ማህበሩም ሆነ መንግስት ማስጠበቅ አልቻለም ሲል ነው የሚናገረው፡፡
‹‹ምንም አይነት ዋስትና የለም አደጋው ከደረሰ ደረሰ ነው፡፡ የሾፌሮች ማህበር አለ ምንም አይነት ስራ እየሰራ አይደለም፡፡ ሾፌር ከሞተም ቤተሰቡን በትኖ ነው የሚሞተው በማህበር ደረጃም ሆነ በመንግስት ደረጃ ምንም ዋስትና የለም፡፡››
ተደጋጋሚ የሾፌሮች እገታ
አሁን ላይ በአማራ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ አካባቢ ያለው እገታና ዝርፊያ ሰርተን ለመለወጥም ሆነ ለህይወታችን ዋስትና አለመኖር ስራችንን ትተን እንድንቀመጥ እያደረገን ነው ሲሉም አሽከርካሪዎቹም ይገልፃሉ፡፡ ‹‹እገታው በገብረ ጉራቻ መንግስትም ያውቀዋል፡፡ በአዋሽ በኩልም እንደዚሁ ሁሉም ቦታ እገታ ስለሆነ እኔ አሁን ሾፌር ነኝ ትቼ ቁጭ ብያለሁ ፤ ምንም ዋስትና የለም፤ ከሞመት ይሻላል ብየ መቀመጡን መርጫለሁ፡፡››
በግዳጅ ላይ እያሉ የሞቱ አሽከርካሪዎች ቤተሰቦች መቸገር
በኢትዮጵያ የሀገር አቋራጭ ሾፌሮች ማህበር ዋና ፀሀፊ አቶ መሳይ ኃ/ማርያም እንደሚገልፁት በሰሜኑ ጦርነት ሲያገለግሉ የነበሩ የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎች በጦርነት ውስጥ ህይወታቸው በማለፉ ዛሬ ላይ ቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር ተዳርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ በጦርነቱ የሞቱ አሽክርካሪዎችን ቤተሰቦች ለመደጎም የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስተር በባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ቢያዘጋጅም እስከ ዛሬ ግን ተፈፃሚ አልሆነም፡፡
‹‹ከህልውና ዘመቻ ጀምሮ ችግሮች አሉ፤ በህልውና ዘመቻ እስከ ግንባር ድረስ ነው አሽከርካሪዎች የሚገቡት የተሰውም አሉ የእነሱን ቤተሰቦች አሁን የከፋ ችግር ላይ የሚገኙት ልጆች ትምህርት ቤት አቁመዋል፣ የቤት ኪራይ የሚከፍል የለም፣ ብዙ ነገር የለመዱ ናቸው፡፡ ያን ሁሉ አጥተዋል፡፡ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስተርም ቴሌቶን አዘጋጅቷል ግን እስካሁን አልተጠናቀቀም፡፡››
በግዳጅ ላይ እያሉ የሞቱ አሽከርካሪዎችን ሞት ለቤተሰቦቻቸዉ በተገቢዉ መንገድ አለማርዳት
የኢትዮጵያ የሀገር አቋራጭ ሾፌሮች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተካ ደበሌ አሽከርካሪዎች በግዳጅ በተሰማሩባቸው ጦርነቶች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ እንኳን ለቤተሰቦቻቸው ለማርዳት የተቸገርንበት ሁኔታ ነው ያለው ይላሉ፡፡ ‹‹በህልውና ዘመቻው አሁንም በሚደረገው የመንግስት እንቅስቃሴ የእኛ አገር አቋራጭ አገልጋይ ነው፡፡ ግዳጅ እንሰማራለን የቀሩ ወንድሞቻችንም አሉ መስዋዕት የሆኑ በረዳት፣በገንዘብ ተቀባይ በሾፌር ይህን ያህል ተብሎ የሚነገር አይደለም፡፡ ለዚህ ሁሉ ቤተሰቦች እንኳን ለማርዳት ጥያቄዎችን ብንጠይቅ እናንተን አይመለከታችሁም እኛው በወረዳና ቀበሌ ደረጃ እናረዳለን እናንተ ምን አገባችሁ ተብለናል፡፡››
እንደ አቶ ተካ ደበሌ ገለፃም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአሽከርካሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው እገታም የማህበሩን አቅም ፈትኗል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
‹‹አብዝሃኛው እገታ የሚፈፀመው በእኛ በህዝብ ማመላለሻ መኪኖች ላይ ነው፡፡ በጎጃም በር በርካታ ጊዜ ታግተዋል፡፡ በጥይት ተመተው ያመለጡም አሉ፤ የሚሞቱም አሉ፤ ምንም አቅም የለንም፤ ማህበሩ እራሱ እየተንገዳገደ ቢሮውን መምራት አልቻለም፡፡››
በትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር አማካኝነት የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም በተለያዩ የግዳጅ አጋጣሚዎች ህይወታቸውን ያጡ አሽከርካሪዎችን ቤተሰቦችን ለመደገፍ የታሰበ በመሆኑ ቃል የተገቡ ልገሳዎች ተሰብስበው ሲጠናቀቁ ለቤተሰቦቻቸው ለማድረስ እንደሚሰራ አቶ መሳይ ኃ/ማርያም የማህበሩ ፀሀፊ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአሽከርካሪዎች ደህንነት ከእኛ በላይ በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው፡፡
‹‹የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ቴሌቶን ገቢ በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር አካውን የገባ በመሆኑ የእኛ ድርሻ ሲደርሰን የተመዘገቡ አሉ በአካል ለእነሱ ለማድረስ እንሰራለን፡፡ አገር አቋራጭ አውቶቡስ ሾፌር የግል ተቀጣሪ ነው ያው ክስተት ስለሆነ አሁን የመጣብን በሽታ ይታገታል ይሄዳል በእኛ በኩል ከመንግስት በላይ ምንም የምናደርገው ነገር የለም መንግስትም ይህንን ነገር ስሚያውቅ እኛም የሚደርሱትን ነገር ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ መንግስትም ጉዳዩን ማቅለል እና ማርገብ ነው የሚገባው፤ እኛ ምንም አቅም ስለሌለን እያዘንን ብቻ ነው ዝም የምንለው፡፡››
ኢሳያስ ገላው
ኂሩት መለ
ነጋሽ መሐመድ