በኢትዮጵያውያን ላይ ተጽእኖ ያስከተሉ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዕዛዛት
ሐሙስ፣ ጥር 22 2017
በኢትዮጵያውያን ላይ ተጽእኖ ያስከተሉ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ትዕዛዛት
በዩናይትድ ስቴትስ ሰነድ አልባ ናቸው የተባሉ በርካታ ስደተኞች፣በግዳጅ ወደመጡበት ሃገር እንዲመለሱ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያስተላለፉት ውሳኔዎች፣ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያስከትለውን ተጽዕኖ በተመለከተ የህግ ባለሙያ አነጋግረናል።
የሰሞኑ አሰሳና የጅምላ እስር
አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣በሃገሪቱ የስደተኞች እና ጉምሩክ ተቋም አማካይነት፣ ካለፈው እሁድ አንስቶ እዚህ አትላንታ ጆርጂያ፣ቺካጎ፣ኒዋርክ፣ሚያሚና ሌሎች አካባቢዎች አሰሳ በማካሄድ፣ሕገ ወጥ ያላቸውን ስደተኞች በቁጥጥር ሥር እያዋለ፣ በግዳጅ ወደመጡበት ሃገር እንዲመለሱ እያደረገ ነው። የአሜሪካ የስደተኞችና የጉምሩክ ተቋም በሆነው አይሲኢ ድረ ገጽ ላይ ባገኘነው መረጃ መሰረት፣ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣አንድ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ተይዘው ታስረዋል።
በወር አምስት ሺህ ሰዎች ለመመለስ መታቀዱ
ስለአሰሳውና እስሩ፣ዶይቸ ቨለ ያነጋግራቸው በቨርጂኒያ ግዛት የሕግ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ፣ስለጉዳዩ አሳሳቢነት እንደሚከተለው ገልፀዋል። "ከዚህ በፊት የማይነኩ ከትምህርት ቤት፣ከቤተክርስቲያን እና ከሆስፒታል ወረቀት የሌላቸውን ሰዎች አፍሶ፣ በወር አምስት ሺህ ሰው ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ነው እንግዲህ በወታደራዊ አውሮፕላን ዕቅዳቸው።ሕጋዊ ወረቀት የላቸውም የተባሉ ሰዎችን በጥርጣሬም ቢሆን አፈሳ እያካሄዱ በመስሪያ ቤቶች፣በቤተክርስቲያናት መንገድ ላይም፤ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ወደ ፊት የሚያስፈሩ ነገሮች ናቸው ማኀበረሰባችን ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ።"
በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተፈረሙና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በቀጥታ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ትዕዛዞችን በተመለከት የጠየቅናቸው የሕግ ባለሙያው ሲመልሱም፤ "የአሜሪካን ሃገር ወረቀት የሚያገኙበት አንደኛው መንገድ፣ የስደተኞች ከሌሎች ሃገሮች የመምጫና የጥገኝነት ጥያቄ ሂደት ነው።ያንን ነው እንግዲህ ትልቅ ግንብ የሰራበት።አጥር ሊሰራ ነው፣ሁለተኛ ነገር ደግሞ፣ በሜክሲኮ ወይም በሌላ በኩል የሚመጡ ሰዎች እዛው ባሉበት ቦታ ቁጭ ብለው ትራምፕ ሲፈልግ ማለት ነው።ማለትም ከዘጠና ቀናት በኃላ እንደገና ዐይቶ ሲፈቅድ የእዛን ጊዜ ማመልከት ይችላሉ።በአጭሩ እዛው ሜክሲኮ ወይም ሌላ አገር ቆይታችሁ ፕሮሰስ አድርጉ የሚለው ነገር የእኛን ማኀበረሰብ በብዛት ይነካዋል።ምክንያቱም በብዛት በሜክሲኮ በኩል በድንበር ተሻግረው የሚመጡ ስላሉ ማለቴ ነው።"
አዳዲስ የኢሚግሬሽን አሰራሮች
ሙሉ ለሙሉ እንዲቆሙ የተደረጉና ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የተመለከቱ አዳዲስ አሰራሮች ገቢራዊ መሆናቸውንም ደክተር ፍጹም ያስረዳሉ። "በሌሎች ሃገሮች፣በዑጋነሰዳ፣በኬንያ፣በሱዳንና በሌሎችም ሃገሮች፣በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በኩል አመልክተው፣ማመልከቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ፣በቤተሰብም ስፖንሰር ይሁኑ በቤተክርስቲያን የሚገቡ ሰዎች ስደተኞች ማቋቋም ይባላል፣ እሱን ሙሉ በሙሉ አስቁሞታል።ሌላ ነገር አድርጌ እንደገና ተመልክቼ እስክጨርስ ድረስ ተብሎ ለዘጠና ቀናት እንዲቋረጥ ሆኗል፤በዚሁ ይቀጥላል የሚል ፍርሃት ነው ያለው።"
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ማወቅ ያለባቸው ምንድነው?
ከሰሞኑ አሰሳ ጋር በተያያዘ፣አንድን ሰዎች እየደወሉ ሲገልጹ ነበር እና ምን ማድረግ እንደለባቸው የማያውቁ ብዙ ወገኖቻችን አሉ።ሊጠየቁ ይላሉ ወይ ሱቅ ሲሄዱ ወይ የሆነ ቦታ ላይ? ባለሙያው ሲመልሱም" አንደኛ ማንኛውም ሕጋዊ ወረቀት ያለው ሰው፣በጥገኝነትም ይሁን የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ሰው እነዛን ነገሮች በኪሱ ይዞ ስራም ቦታ ሲሄድ፣ቤተክርስቲያንም ሲሄድ፣ትምህርተ ቤትም ሲሄድ መያዝ አለበት።ምክንያቱም እነዚህ ሕግ አስከባሪዎች ወረቀት አለኝ ቤት እንኺድ ቢባል አይጠብቁም።ስለዚህ ሁሉም ሰው፣ያለውን መንግስት የሰጠውን የመታወቂያ ወረቀት ይዞ መንቀሳቀስ አለበት።የመኖሪያ መታወቂያ ካርድ፣የሥራ ፈቃድ የጊዚያዊ የስደተኛነት ሁኔታን የሚያሳይ ቲፒኤስ ወረቀቱን ይዞ መንቀሳቀስ አለበት።ብዙ ሰው የመኖሪያ ካርዱንና የሥራ ፈቃዱን ቤት ትቶ ነው የሚሄደው።እነዚህን ያልያዘ ሰው፣ማንም ሰው በሚጠይቀው ጊዜ ከእዛ ከሚጠይቀው ሰው ጋር መተባበር የለበትም።ስሙንም መናገር የለበትም ምንም ነገር መናገር አልፈልግም ማለት ይችላል፣አሜሪካን ሃገር፣እነዚህ ሰዎች በሙሉ ማንኛውም ኢሚግሬሽንም ቢሆን በሃገሪቱ ሕግ መገዛት ስላለባቸው፣ማንም ሰው ለመንግስት ኃይሎች የግድ ቃሉን መስጠት የለበትም።" እንደ ሕግ ባለሙያው ገለጻ፣ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደገና ወደ ኃይት ሐውስ ተመልሰው ያስተላለፏቸው ፕሬዚንታዊ ትዕዛዛት፣ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ብዙ ረገድ ተጽእኖ የሚያደርሱ ሆነው በቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚዘልቁ ይሆናል።
ታሪኩ ኃይሉ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ