“ልዩነቶችን በጠብመንጃ እና በኃይል የመፍታት አማራጭ ማክተም አለበት” ሣህለ ወርቅ ዘውዴ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 29 2016
የሀገሪቱ ህገ መንግስት የፀደቀበትን ህዳር 29 ቀን መሰረት አድርጎ በኢትዮጵያ መከበር የጀመረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ዘንድሮው ለ18 ኛ ጊዜ በሶማሌ ክልል አዘጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።
የበዓሉ የክብር እንግዳ የሆኑት የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ "በሀገራችን ልዩነቶችን በጠመንጃ እና በኃይል የመፍታት አማራጭ ማክተም አለበት" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቷ ባስተላለፉት መልዕክት "ብሄር ፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እንደምናከብር ሁሉ ለብሔራዊ ማንነታችን እና ለኢትዮጵያዊነታችን ከፍተኛውን ቦታ መስጠት ይጠብቅብናል።" ሲሉ ገልፀዋል።
የበዓሉ የክብር እንግዳ ሆነው በጅግጅጋ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመርሀ ግብሩ ንግግራቸው በሀገሪቱ ይታያል ያሉትን "ጫፍ የረገጠ ብሄርተኝነት" በማንሳት "እርስ በእርስ የሚያይዘንን እያላላን እንዳንሄድ እሰጋለሁ " ብለዋል።
ፕሬዝዳንቷ "ብሄር ፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እንደምናከብር ሁሉ ለብሔራዊ ማንነታችን እና ለኢትዮጵያዊነታችን ከፍተኛውን ቦታ መስጠት ይጠብቅብናል። ብሔራዊ ስሜትም ማዳበር አለብን እነዚህን በዓሎች ስናከብር" በማለት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የእርስ በእርስ ግጭቶች በዜጎች ላይ እያስከተሏቸው ያሉ ዘርፈ ጉዳቶችን ያነሱት ሳህለወርቅ በሀገሪቱ "ልዩነቶችን በጠመንጃ እና በኃይል የመፍታት አማራጭ ማክተም አለበት" ሲሉ አስገንዝበዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር በበኩላቸው "ታሪካዊ" ሲሉ በገለጿቸው ጠላቶች ተፈብርከው በእኩያን ወንድሞቻችን የሚቀነቀኑ ዋልታ ረገጥ የተናጠል አስተሳሰቦች አደጋ እየደቀኑ መሆኑን" በማንሳት ነገር ግን ይህ እንደማይሳካ ገልፀዋል።
የበዓሉ አዘጋጅ የሆነው የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ክልሉ ከአስር አመት በፊት ይህንን በዓል "አምባገነን" ባሏቸው መሪዎች ተጠርንፎ በሰላም እጦት ማካሄዱን በማስታወስ ዘንድሮ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች በተመዘገቡበት ወቅት መከበሩን አስረድተዋል።
"ብዝሀነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የዘንድሮ በዓል ላለፉት አምስት ቀናት በጂግጅጋ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ሲከበር ቆይቶ ዛሬ ተጠቃሏል። በበዓሉም በርካታ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ታድመዋል።
የፕሪቶርያ ስምምነት አፈፃፀም አንደኛ ዓመት እና የመቐለ ነዋሪዎች አስተያየት
የበዓሉ አከባበር በጅግጅጋ
ለወትሮው ህዳር 29 ቀን በሚካሄድ መርሀ ግብር ይከበር የነበረው የብሄር ብሄረሰብ በዓል ዘንድሮ በተለየ መልኩ ለአምስት ቀናት በተለያዩ ኩነቶች በጅግጅጋ ሲከበር ቆይቷል።
የሩጫ ውድድር ፣ የንግድ ትርዒት እና ባዛር ፣ የተለያዩ ብሄር ብሔረሰቦች የተሳተፉበት የባህል ኤግዝቢሽን እና የፓናል ውይይት መድረክ ላለፉት ቀናት በዓሉን አስመልክቶ በጅግጅጋ ሲከወኑ የቆዩ ዝግጅቶች ናቸው።
ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የባህል ቡድኖችም የየራሰቸውን አለባበስ እና አጨፋፈር በጅግጅጋ ጎዳናዎች ተዟዙረው ሲያቀርቡ ሰንብተዋል።
በዛሬው እለት በተካሄደው የማጠቃለያ መርሀ ግብር የኤፊድሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ተካሂዷል።
በቅርቡ የተቋቋመው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መጪውን 19ኛው ተመሳሳይ በዓል የማዘጋጀ ኃላፊነቱን በመረከብ የዘንድሮው በዓል ተጠቃሏል።