1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተፅዕኖ እንዲደርግ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

ነጋሽ መሐመድ
ረቡዕ፣ ጥር 21 2017

በአራቱ ወራት ዉስጥ «ሥለ ጅምላ አፈሳና እስራቱ ዓለም አቀፍ ዝምታ መስፈኑ» ይላሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪቃ የበላይ ኃላፊ ትገሬ ቻጉታሕ «ከማሳፈርም በላይ ነዉ።»ቻጉታሕ አክለዉ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም የሕግ-ሥርዓት እንዳሻዉ ሲያተራምሰዉ ዓለም አይቶ እንዳላየ ማለፉን ማቆም አለበት።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደርሰዉን የሠብአዊ መብት ጥሰት አይቶ እንዳለየ ማለፉን ማቆም አለበት
«የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች፣ የአፍሪቃና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ተቋማት፣ ከአማራ ክልል በጅምላ የታሰሩት ሰዎች እንዲለቀቁ በግልፅ መጠየቅ አለባቸዉ።ተፅዕኖም ሊያደርጉ ይገባል።» አምነስቲ ኢንተርናሽናል።ምስል፦ Eduardo Verdugo/AP Photo/picture alliance

በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተፅዕኖ እንዲደርግ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

This browser does not support the audio element.

 ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት ያደርሰዋል ያለዉን የመብት ጥሰትና የሲቪክ ማህበራትን ማገዱን እንዲያቆም ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግፊት ያደርግበት ዘንድ ጠየቀ።አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት በአማራ ክልል መጠነ-ሠፊ የእስራት ዘመቻ የከፈተበትን4ኛ ወር ምክንያት በማድረግ ትናንት  ባወጣዉ መግለጫ እንዳለዉ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚደርሰዉን የሠብአዊ መብት ጥሰት አይቶ እንዳለየ ማለፉን ማቆም አለበት።የኢትዮጵያ መንግስት ያለፍርድ ቤት ዉሳኔ ያሰራቸዉን ሰዎች ዓለም አቀፍ ዕዉቅና ባለዉ ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ወይም እንዲለቅ የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ጠይቋል።ነጋሽ መሐመድ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባን አነጋግሯል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደሚለዉ የኢትዮጵያ የፌደራልና የአማራ ክልል ፀጥታ አስከባሪዎች እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከመስከረም 28 ቀን 2024 ጀምሮ አማራ ክልል በከፈቱት ዘመቻ ወንድ ከሴት፣ ዳኛ-ከአቃቤ፣ ምሁር-ከተማሪ ሳይለዩ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን በጅምላና በመደዳ እያፈሱ በአራት ማቆያ ጣቢያዎች አስረዋል።ትናንት አራት ወራቸዉ።
በአራቱ ወራት ዉስጥ «ሥለ ጅምላ አፈሳና እስራቱ ዓለም አቀፍ ዝምታ መስፈኑ» ይላሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪቃ የበላይ ኃላፊ ትገሬ ቻጉታሕ «ከማሳፈርም በላይ ነዉ።»ቻጉታሕ አክለዉ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም የሕግ-ሥርዓት እንዳሻዉ ሲያተራምሰዉ ዓለም አይቶ እንዳላየ ማለፉን ማቆም አለበት።

ዓለም አቀፉ ማሕበረሠብ የኢትዮጵያን ጉዳይ ችላ ማለት የለበት

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ቀንድ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ሰዓድ ኑር እንደሚሉት ደግሞ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ሌላ ሥፍራ ያሉ ቀዉሶች ትኩረቱን ቢስቡትም ኢትዮጵያን ችላ ማለት የለበትም።
                             
«የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች፣ የአፍሪቃና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ተቋማት፣ በጅምላ የታሰሩት ሰዎች እንዲለቀቁ በግልፅ መጠየቅ አለባቸዉ።ተፅዕኖም ሊያደርጉ ይገባል።ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ቀዉሶችን ለማስወገድ ጣልቃ ሲገባ ነበር።እርግጥ ነዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቅም ግጭቶች አሉ።ጋዛና ዩክሬን ዉስጥ ያሉት ቀዉሶችም የኢትዮጵያዉን ሁኔታ ሸፍኖታል።ይሁንና የኢትዮጵያ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠዉ ይገባል።»
አምነስቲ ኢተርናሽናል እንደሚሉት አማራ ክልል በሚደረገዉ ግጭት ምክንያት ካለፈዉ መስከረም ጀምሮ ከታሰሩት ዉስጥ ባለፈዉ ጥቅምት 4 የፍትሕ ሰራተኞች፣ በያዝነዉ ጥር ደግሞ 3 ዳኞችን ጨምሮ በመቶ የሚቆጠሩ ሴቶች፣ አዛዉንቶችና ሕሙማን ተለቅቀዋል።ታዲያ እስረኞቹ ከተለቀቁ አምነስቲ ፍርድ ቤት ይቅረቡ ወይም ባስቸኳያ ይለቀቁ የሚለዉ የትኞቹን ነዉ? ጠየቅን።መለሱ ሰዓድ ኑር «የሚገርም ማስተዋል» እያሉ።

የመንግስት ጦር ኃሎችና የፋኖ ታጣቂዎች በአማራ ክልል የሚያደርጉት ጦርነት በርካታ ነዋሪዎችን ጎድቷል።በተለይ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች የሚወስዱትን ርምጃ ዉጪ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች በሰልፍ አዉግዘዉታል።ምስል፦ Marcello Valeri/ZUMA/picture alliance

 

አሁንም በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደታሰሩ ነዉ
                      
«በጣም አመሰገናለሁ። የሚገርም አስተዉሎት ነዉ።ጉዳዩ እንዴት ነዉ።በመግለጫችን እንዳልነዉ ጥር ላይ ዳኞችን ጨምሮ የተወሰኑ እስረኞች ተለቅቀዋል።አሁንም ግን በሺ የሚቆጠሩ ሕግ ፊት የመቅረብ መብታቸዉ ተገፍፎ እንደታሰሩ ነዉ።ሥለዚሕ የተወሰኑ መለቀቃቸዉን እናዉቃለን።ሁኔታዉ ግን አሁንም በጣም አሳሳቢ ነዉ።ሰዎች አሁንም በዘፈቀደ እንደታሰሩ ነዉ።»
የኢትዮጵያ መንግስት አራት የሲቪክ ማሕበራትን ማገዱንም አምነስቲ ኢንተርናሽናል አዉግዞታል።የኢትዮጵያ መንግስት ከአማራ ክልል በተጨማሪ ግጭት በሚደረግበት በኦሮሚያና በሌሎች አካባቢዎች »ይፈፅመዋል ያለዉን የመብጥ ጥሰት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እየተከታተለ መሆኑን ወይዘሮ ሰዓድ አስታዉቀዋል።
          
«በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈዱ ቀዉሶችን በቅርብ እየተከታተልን ነዉ።በመንግስት ላይ ዓለም አቀፍ ግፊት እንዲደረግ የምንጠይቀዉም ለዚሕ ነዉ።በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ግፊት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነዉ።ምክንያቱም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሲቪል ማሕበረሰቡንም እየደፈለቁት ነዉ።እንደምታዉቁት የአራት ታዋቂ የሠብአዊ መብቶች ድርጅቶች ፈቃድ ታግዷል።»
የኢትዮጵያ መንግስት የሚያስተዳድረዉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለፈዉ ሳምንት ባወጣዉ መግለጫም ኢትዮጵያ ዉስጥ ግጭት በሚደረግባቸዉ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸዉን ዘግቧል።

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ


 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW