በኢትዮጵያ ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ እና ዐበይት ጉዳዮች
እሑድ፣ መጋቢት 20 2018
ባለፉት 30 ገደማ ዓመታት ሴት የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ2 በመቶ ወደ 40 በመቶ ገደማ ከፍ ብሏል። በ1987 በተካሔደው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ 536 ወንዶች እና 10 ሴቶች ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠውን ምክር ቤት መቀመጫዎች ማግኘት ችለው እንደነበር የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል።
በሰኔ 2013 እና መስከረም 2014 በግጭት ድባብ ውስጥ ከተካሔደው ምርጫ በኋላ ከተመሠረተው ምክር ቤት አባላት ውስጥ 202 ሴቶች ናቸው። ከምክር ቤቱ መቀመጫዎች 40 በመቶው በሴቶች የተያዘ ቢሆንም አንዳቸውም የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አልያም የግል ተወዳዳሪ አይደሉም። ሁሉም የገዥው ብልጽግና ፓርቲ አባላት ናቸው።
6ኛው አጠቃላይ ምርጫ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ፈርሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፕሬዝደንትነት የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ ከተመሠረተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሔደ ነው። ይሁንና በተወካዮች ምክር ቤት 38 መቀመጫዎች ባሉት የትግራይ ክልል ምርጫው አልተካሔደም። በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል በበረታው ውጥረት ምክንያት ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ በትግራይ ክልል መቼ እና እንዴት እንደሚካሔድ አይታወቅም።
በመጪው ግንቦት ይካሔዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ሰባተኛ አጠቃላይ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ ቢጠናቀቅም እስካሁን ምን ያክሉ ሴቶች እንደሆኑ በይፋ አልተገለጸም። ቦርዱ እስከ መጋቢት 18 ቀን 2018 ከመዘገባቸው 28.4 ሚሊዮን ገደማ መራጮች ውስጥ ከ13 ሚሊዮን በላይ ወይም 46 በመቶው ሴቶች ናቸው። ምዝገባው እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ይቀጥላል።
ባለፉት ስድስት ምርጫዎች አሸንፈው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት የሆኑ ሴቶች ቁጥር መጨመሩ ፋይዳ ቢኖረውም በተጨባጭ ለውጥ እንዳልመጣ ተመራማሪዎች እና የጾታ ዕኩልነት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚካሔደው ሴቶች በኢትዮጵያ በተካሔዱ እና በመካሔድ ላይ በሚገኙ ግጭቶች ውስጥ አስገድዶ መደፈርን ጨምሮ ከሚፈጸምባቸው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሳይላቀቁ ነው። ጦርነት ሲነሳ፣ ግጭት ሲቀሰቀስ ሴቶች፣ ሕጻናት አቅመ ደካሞች እና አረጋውን ላይ ዳፋው ይበረታል።
ለመሆኑ ሴት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ሲጨምርም ይሁን እንስቶች በከፍተኛ የመንግሥት የሥልጣን እርከኖች ሲሾሙ በተጨባጭ ምን ፈየደ? በድምጽ ሰጪነትም ይሁን በዕጩነት በምርጫው ለመሳተፍ ለሴቶች የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ምን ያክል ፈታኝ ነው? ለሴቶች አንገብጋቢ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?
ዶቸ ቨለ በጉዳዩ ላይ አራት እንግዶች በመጋበዝ ይኸን ውይይት አካሒዷል። በውይይቱ ከተሳተፉ መካከል በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የተወዳደሩት እና ዘንድሮም በዕጩነት የተመዘገቡት እጸገነት ተስፋዬ ይገኙበታል። እጸገነት የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ሰብሳቢ ናቸው።
የኦሮሞ ፌድራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባል የሆኑት ሒሮዋቅ ግርማ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም መምህር እና የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ዶክተር ትርሲት ሳህለድንግል እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ጥናት ተመራማሪ ፍቅር ጌታቸው በውይይቱ ተሳትፈዋል።
ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ