በኢትዮጵያ በነዳጅ ማደያዎች የሚስተዋለው የአቅርቦት መቆራረጥ መንስኤው ምንድነው?
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2 2018
በመዲናዋ አዲስ አበባ የነዳጅ እጥረት ባስከተለው መጨናነቅ በተለይም ከባለፈው ቅዳሜ ጀመሮ ከሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እስከ ከባድ የጭነት መኪናዎች በየነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም ሰልፎች ላይ ተጨናንቀው ታይተዋል።
እጥረቱ የፈጠረው የአሽከርካሪዎች እንግልት
ከአዲስ አበባ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የተሽከርካሪ ባለንብረት እና አሽከርካሪ እንዳሉት ይህ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እና የማደያዎች መጨናነቅ ከተስተዋለ ወደ ሳምንት ተጠግቷል። «በቃ ከሳምንት ጀምሮ ሁለት ሦስት ቀን ቆመን እየቀዳን ነው» ያሉት አስተያየት ሰጪው መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዳቃተው ጥያቄ እንደሆነባቸውም ገልጸዋል። አስተያየት ሰጪው በየማደያው የሚስተዋለው የነዳጅ እጥረቱ ለተጨማሪ ዋጋ ፍለጋ ምርትን የመደበቅ እንጂ የአቅርቦት እጥረት የፈጠረው እንዳልሆነም እንደሚሰጉ ገልጸውልናል።
ሌላም አስተያየት ሰጪ አሽከርካሪ እንዳሉት፤ የነዳጅ አቅርቦቱ መቆራረጥና የተፈጠረው እንግልት የማጓጓዣ ነዳጅ እጥረትን በመፍጠር የጫኑትን ምርት እስከማበላሸት የሚያደርስ ኪሳራ እያስከተለ ነው፡፡ «በጣም አስቸጋሪ ነው። ሰልፉ ከመብዛቱ መኪና ቆሟል፤ በመሃል ደግሞ አልቋልም ስለሚባል እየተቸገርን ነው» በማለት የችግሩንም መንስኤ ግን እንዳልተረዱት አመልክተዋል። በነዳጅ አቅርቦት ችግሩ የተነሳ መኪና ነዳጅ ለመቅዳት ሁለት-ሦስት ቀናትን ከሥራ መስተጓጎሉ የተጫነውን ዕቃ እስከማበላሸት የሚያደርስ ኪሳራንም እያስከተለ ነው ብለዋል።
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው መረጋገጥ አቅርቦቱን መልሶ ያስተካክለው ይሆን?
ከወትሮም በነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊደረግ ነው በሚል መረጃዎች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲሰራጩ ዳፋው ለአሽከርካሪዎች እና ለተሽከርካሪ ባለንብረቶች እንደሚተርፍ ተገምቷል። ከሰሞኑም የተስተዋለው የነዳጅ አቅርቦት እጥረትና የማደያዎቹ መጨናነቅ መንስኤው ይሄው ሳይሆን አይቀርም በሚልም ይነሳል። ትናንት ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ ይፋ የሆነው አዲሱ የቤንዚን እና ናፍጣ ነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ መሸጫ ከሰባት እስከ ስምንት ብር ግድም ጭማሪ በማሳየት የሁሉም ዋጋ ሲጠበቅ እንደነበረው ወደ 129 ብር ከፍ ብሏል። ይህስ ጭማሪ በየማደያዎቹ የነዳጅ አቅርቦቱን አረጋግቶት ይሆን በሚል የተጠየቁት ተጠቃሚ፤ «አሁንም ጭማሪ ከተደረገ በኋላ ቢያንስ እስከዛሬ ድረስ አቅርቦቱ ላይ ለውጥ አልመጣም» ነው ያሉት።
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በነዳጅ ላይ የ30 በመቶ ጭማሪ ይጠበቃል በሚል በተለያየ መንገድ የሚሰራጨውን መረጃ መኖሩንም በመጠቆም ምናልባት ማደያዎች እሱን ጭማሪ ይጠብቁት ይሆን? በማለትም ጠይቀዋል። ችግሩ የነዳጅ አቅርቦት ችግር አይመስልም የሚሉት አስተያየት ሰጪው መንግሥት ተከታትሎ ማስተካከያ እንዲወሰድ ካላደረገ መፍትሄ እንደማይመጣም ምልከታቸውን አጋርተዋል። ችግሩም መዲናዋ አዲስ አበባን ጨምሮ መላ የአገሪቱን ክፍል ያዳረሰ እልባት የሚሻ ችግር ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስለ ነዳጅ አቅርቦት መቆራረጡ የመንግሥት ግምገማ
ዶይቼ ቬለ በትናንትናው ዕለት ይፋ የተደረገውን የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ከሰሞኑ የገጠመው የአቅርቦት መስተጓጎል መንስኤና እየተሠሩ ስለሚገኙ መፍትሄዎች አስተያየታቸውን እንዲሰጡት የ ኢትዮጵያ ነዳጅ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ደስታ መኳንንትን ቢጠይቅም መልስና ማብራሪያ አልሰጡንም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስለሚያጋጥመው የነዳጅ አቅርቦት መቆራረጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ሲሰጡ «መንግሥት በውድ ዋጋ ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባውን ነዳጅ፤ አቅራቢዎች የዋጋ ጭማሪን ሲጠባበቁ ምርትን እንደሚደብቁ ይታወቃል» በማለት መንግሥታቸው ይህን በሚያደርጉ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በአውቶሜሽን እንደሚከታተል መግለጻቸው አይዘነጋም።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ