1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ በኤች አይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ

ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2011

በዓለም ላይ በኤች-አይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤድስ መከላከያ ድጋፍ በምህፃሩ «UNAIDS» ገለጸ። የኢች-አይቪ ስርጭት በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ስርጭቱ «ወረርሽኝ» ሊባል በሚችል ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል።

Südafrika Weltaidstag Wandbild in Soweto
ምስል picture-alliance/dpa

«በተለይ በአዲስ አበባ ስርጭቱ ወረርሽኝ ከሚባልበት ደረጃ ላይ ነው»

This browser does not support the audio element.

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሰረት በጎርጎሮሳዊዉ 2018 ዓ/ም ከኤች- አይ ቪ ጋር በተያያዘ የሞቱ  ሰዎች ቁጥር  በ 30 ሺህ ዝቅ ቢልም የበሽታዉ ስርጭት ግን  አሁንም እየጨመረ መምጣቱን ነዉ ያመለከተዉ። ለሞት መጠኑ  መቀነስ  የፀረ-ኤች አይቪ ህክምና ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት  በምክንያትነት ተጠቅሷል። በአንፃሩ ግን  ኤች-አይቪ  ኤድስን  ለመከላከልና በበሽታዉ እንደ አዲስ  የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት ደካማ መሆኑን ነዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የገለፀዉ። ችግሩ በአፍሪቃ በተለይም ከሳሃራ በታች ባሉ ሀገራት ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል።በኤች-አይቪ እንደ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከወንዶቹ ጋር ሲነጻፀርም የሴቶች በተለይም የወጣት ሴቶች የመያዝ እድል 60 በመቶ የጨመረ መሆኑን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል። በጉዳዩ ላይ «DW» ያነጋገራቸዉ የአዲስ አበባ ከተማ የኤች-አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ሲስተር  ፈለቀች  አንዳርጌ   የተጠቀሱት ችግሮች በኢትዮጵያም የተለያዩ የክልል ከተሞችና  በአዲስ አበባ ኤች-አይቪ ኤድስ  በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና አሁንም ድረስ ስጋት ሆኖ መቀጠሉን  ነዉ  ያመለከቱት። 
በሀገሮች የኤች አይቪ ስርጭት ከ አንድ ፐርሰንት በላይ ከሆነ ወረርሽኝ ሊባል እንደሚችል ሃላፊዋ ገልፀዉ።«በሀገር ዓቀፍ ደረጃ 0 ነጥብ 9 ፐርሰንት ነዉ።ይህ ቁጥር የክልሎቹ ገፅታ ስንመለከት የተለያዩ ገፅታዎች አሉት።በጋምቤላ 4 ነጥብ 8 ነዉ።በአዲስ አበባ በሁለተኛ ደረጃ ስርጭቱ 3 ነጥብ የስርጭት መጠን አለዉ።ሌሎች አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ደግሞ ከ 1 ፐርሰንት በላይ የስርጭት መጠን አላቸዉ።» ካሉ በኋላ ስለዚህ አሁንም ድረስ ኤች አይቪ ከፍተኛ የሀገር ስጋት ነዉ ማለት ነዉ ብለዋል።
እንደ ተባበሩት መንግስታት መረጃ በ2017 ከኤች አይቪ/ኤድስ ጋር በተያያዘ 8 መቶ ሺ ሰዎች  በ2018 ዓ/ም ደግሞ 770 ሺ ሰዎች ሞተዋል። ይህም የሚፈለገዉን ያህል ባይቀንስም በ2010 ከነበረዉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሞት መጠን ጋር ሲነፃፀር ከፀረ ኤች-አይቪ መድሐኒት ጋር ተያይዞ  በአንድ ሦስተኛ  መቀነሱ ነዉ  የተመለከተዉ። ያም ሆኖ ይህ የሞት መጠን መቀነስ ኤች-አይቪን ለመከላከል በሚደረገዉ ጥረት ላይ መዘናጋትን  መፍጠሩን  ሲስተር ፈለቀች ያስረዳሉ። በመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት የነበረዉ ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራና በሽታዉን ለመከላከል ይደረግ የነበረዉ የለጋሾች ድጋፍ እየቀነሰ መምጣት ለስርጭቱ መጨመር ሌላዉ ምክንያት ሲሆን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ለበሽታዉ የሚያጋልጡ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች መኖራቸዉን ገልፀዋል። 
በአዲስ አበባ ደግሞ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገዉ ፍልሰት መጨመር፣ የአልኮል መጠጥ፣የራቁት ጭፈራ ቤቶች፣ከድህነት ጋር ተያይዞ የሴተኛ አዳሪነት መጨመር፣ህገወጥ የማሳጅ ቤቶችና የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ለስርጭቱ አስተዋፅኦ ማድረጋቸዉን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ለመከላከሉ ስራ ከለጋሾች ይገኝ የነበረዉ ድጋፍ በመቀነሱ በዋናነት ስራዉ በመንግስት  ትከሻ ላይ የወደቀ በመሆኑ በዋናነት የፖለቲካ አመራሩ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። ያም ሆኖ ግን ችግሩ የተቀናጀ ስራ ይጠይቃል ነዉ ያሉት ሲስተር ፈለቀች።
በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት 38 ሚሊዮን  የሚደርሱ  ሰዎች ከኤች-አይቪ ጋር የሚኖሩ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ ከ23 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የፀረ-ኤች አይቪ ህክምና ይወስዳሉ። ኤች-አይቪ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተከሰተ ከጎርጎሮሳዉያኑ 1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በዓለም ላይ እስካሁን 35 ሚሊዮን  ሰዎች በበሽታዉ ሕይወታቸዉ አልፏል።
ሙሉ ቅንብሩን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

ምስል picture-alliance/dpa/F. Schuh

ፀሐይ ጫኔ 
አዜብ ታደሰ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW