1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ሥምምነት የተቆጣችው ሶማሊያ ፊቷን ወደ ግብጽ አዙራለች

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 24 2016

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ በተፈራረመችው “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” የተቆጣችው ሶማሊያ ፊቷን ወደ ግብጽና ቃጣር አዙራለች። ሶማሌላንድ ኢትዮጵያ እውቅና የምትሰጥ የመጀመሪያ ሀገር በመሆኗ አመስግና ሥምምነቱን “የሚያስተጓጉሉ ወይም የሚቃወሙ” ወገኖችን አስጠንቅቃለች። ተንታኞች የለየለት ጦርነትም ባይሆን የእጅ አዙር ግጭትን ይሰጋሉ።

በርበራ ወደብ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የተፈራረሙት ሥምምነት ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን የምትጠቀምበትን መንገድ ያካተተ ነው። ምስል Jonas Gerding/DW

በኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ሥምምነት የተቀየመችው ሶማሊያ ፊቷን ወደ ግብጽ አዙራለች

This browser does not support the audio element.

ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” ተፈራርማ እውቅና ልታገኝ መሆኗን የሰሙ የሐርጌሳ ነዋሪዎች ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ሲወጡ መሀሉ ላይ ኮከብ ጣል ያለበት አረንጓዴ፣ ነጭ እና ቀይ ሰንደቃቸውን ያውለበልቡ ነበር። ድማጻቸውን ከፍ አድርገው በድምጽ ማጉያ ከተለቀቀው ሙዚቃ ጋር አብረው ያዜማሉ።

ወደ ኮኒስ ስታዲየም የተመሙ የሞቃዲሾ ነዋሪዎች በአንጻሩ ሥምምነቱ አስቆጥቷቸዋል። ተማሪዎች የሚበዙበት የዛሬው የሞቃዲሾ ሰልፈኛ የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የሚያወግዙ መፈክሮች ማሰማቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ቁጣው ግን በሞቃዲሾ ነዋሪዎች ዘንድ ብቻ አልተገታም። በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደር አብዱልዋሒ ዋርፋ ወደ ሞቃዲሾ “ለምክክር” ተጠርተዋል። የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔ ትላንት ማክሰኞ ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ ባለፉት ወራት ኢትዮጵያ የባሕር በር ሊኖራት ይገባል እያሉ ሲወተውቱ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ጋር የተፈራረሙትን ሥምምነት አጥብቆ ኮንኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የተፈራረሙት “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ ወታደራዊ የጦር ሠፈር እንዲኖራት የፈቅድ መሆኑ ተገልጿል። ምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ ሶማሌላንድ የሶማሊያ ግዛት ነች ሲሉ ተደምጠዋል። “ትላንት ቁርጠኞች ነበርን። ዛሬም ቁርጠኞች ነን። አንዲት ስንዝር የሶማሊያን ግዛት ማንም አሳልፎ አይሰጥም። እንደዚያ የምናደርግበት ምክንያት የለም” ሲሉ ፕሬዝደንቱ የመንግሥታቸውን አቋም አሳውቀዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር የጠራው የድጋፍ ሰልፍ

የሶማሊያ መንግሥት በስብሰባው ባጸደቀው የውሳኔ ሐሳብ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙትን ሥምምነት “ፈቃድ ያልተሰጠው” በማለት አውግዟል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የመግባቢያ ሥምምነቱን በመፈራረም የወሰደው እርምጃ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ እንደሆነም ተችቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የኢስላማዊ ትብብር ድርጅት፣ የአረብ ሊግ፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ድርጅት ወይም ኢጋድ “ኢትዮጵያ ወደ ዓለም አቀፍ ሕግጋት እንድትመለስ ግፊት” እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

“የኢትዮጵያ እርምጃ ቀድሞም በቅጡ ያልረጋውን የቀጠናውን መረጋጋት እና ሠላም ለአደጋ የሚያጋልጥ ጥቃት ነው። በሶማሊያ ሉዓላዊነት፣ ነፃነት እና አንድነት ላይ የተፈጸመ ጥሰት እና ወረራ ነው” ሲሉ የተናገሩት የሶማሊያ መንግሥት ቃል አቀባይ ፋርሐን ሞሐመድ ጂማሌ መንግሥታቸው የአዲስ አበባው ሥምምነት “ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለው እና የማይሰራ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሞሐመድ “አንዲት ስንዝር የሶማሊያን ግዛት ማንም አሳልፎ አይሰጥም” ሲሉ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙትን ሥምምነት ተቃውመዋል።ምስል Abukar Mohamed Muhudin/AA/picture alliance

የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” ሙሉ ይዘት እስካሁን ይፋ አልሆነም። ሥምምነቱን የተፈራረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ከወንድም የሶማሌላንድ ሕዝብ ጋር በትብብር ለመልማት፣ ለማደግ የጋራ ሠላማችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል መነሻ ሠነድ ይሆናል” ሲሉ ገልጸውታል።

የመግባቢያ ሥምምነቱ “ሶማሌላንድ ውስጥ ኢትዮጵያ ወታደራዊ የጦር ሠፈር እና የንግድ የባሕር በር (commercial maritime) እንዲኖራት ይፈቅዳል” ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ ሬድዋን ሑሴን ውሉ የ50 ዓመት ኪራይ እንደሚሆን ገልጸዋል።

የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ “ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሊዙ የሚታሰብ ድርሻ” እንደሚኖራት አስታውቋል። ኢትዮጵያ ለባሕር በር የምትከፍለው ኪራይ እና ለሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጠው ድርሻ መጠን አቶ ሬድዋን እንዳሉት “በዝርዝር ውይይቶች ይወሰናል።” ድርድሩ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አቶ ሬድዋን ተናግረዋል።

ሶማሊያ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ሲሰረዝላት ዜጎቿ የደቀቀው ኤኮኖሚ ያንሰራራል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ይሁኑ አቶ ሬድዋን ሑሴን ያልጠቀሱት በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ትሰጠዋለች የተባለው እውቅና ጉዳይ ነው። ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ “20 ኪሎ ሜትር የሚሰፋ የባሕር በር እንፈቅድላቸዋለን። እነርሱ ደግሞ እንደ ሉዓላዊ ሀገር እውቅና ይሰጡናል። የመግባቢያ ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ለሶማሌላንድ እውቅና በመስጠት የመጀመሪያ ሀገር ይሆናሉ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተፈራረሙት ሥምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና እንደምትሰጥ ተናግረዋል። ምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ የተፈራረሙት ሥምምነት “በሒደት ሶማሌ ላንድ ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥልቀት አጢኖ አቋም የሚወስድበትን አግባብ” እንደሚያካትት አስታውቋል።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሶማሌላንድ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እውቅና ለማግኘት ስትዋትት ቆይታለች። በጎርጎሮሳዊው 2001 በተካሔደ ሕዝበ-ውሳኔ አብዛኛው ሕዝብ ሶማሌላንድ ሉዓላዊ ሀገር እንድትሆን ደግፏል።

ዚያድ ባሬ ከ32 ዓመታት በፊት ከሥልጣን ሲወገዱ ነጻነቷን ያወጀችው ግዛት የራሷ ሕገ-መንግሥት፣ የጸጥታ አስከባሪ ኃይል፣ መንግሥታዊ መዋቅር፣ የመገበያያ ገንዘብ እና አረንጓዴ፣ ነጭ እና ቀይ ቀለማት ያሉት ሰንደቅ ዓላማ ያላት ናት። ይሁን እንጂ እስካሁን የፈለገችውን እውቅና የሰጠ ሀገር የለም። 

በኦስሎ የሰላም ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አሕመድ መሐመድ “ሶማሌላንድ በጎረቤት ሀገሮች በተለይም በኢትዮጵያ እውቅና እንድታገኝ ሶማሊያ አትፈልግም። ከዚህ በተጨማሪ ሶማሊያ እና ምናልባትም ሌሎች ሀገሮች በቀይ ባሕር ዳርቻ ኢትዮጵያ ወደብ እንዲኖራት አይፈልጉም። ወደቡ የኤኮኖሚ ሳይሆን ወታደራዊ የጦር ሠፈር ነው። ለዚያ ነው ከሶማሊያ መንግሥት ጠንካራ ምላሽ የተሰጠው” ሲሉ ሶማሊያ የተቆጣችበትን ምክንያት ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የዐቢይ የወደብ መሻት ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ተቃውሞ ቢገጥመውም አላፈገፈጉም

የአውሮፓ ኅብረት በሶማሊያን ሕገ-መንግሥት፣ በአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መሠረት የሀገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ምክር ለግሷል።

ሶማሌላንድ ነጻነቷን ካወጀት ሦስት አስርት ዓመታት ቢቆጠሩም እስካሁን ዓለም አቀፍ እውቅና አላገኘችም። ምስል Valerio Rosati/PantherMedia/IMAGO

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ወርቅነሕ ገበየሁ ሁለቱ ሀገሮች ውዝግቡን በሰላማዊ እና አግባቢ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ ቢያቀርቡም ከሶማሊያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ብርቱ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። የዋና ጸሐፊው ጥሪ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚያዳላ እንደሆነ የነቀፈው የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በአፋጣኝ ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ መግለጫቸውን ሰርዘው ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።

የሶማሊያ መንግሥት ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች እና በይፋ ካወጣቸው መግለጫዎች በተጨማሪ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛል። “ከትላንት ጀምሮ ሶማሊያ በጉዳዩ ላይ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር በተለይ ከግብጽ ጋር ንግግር ማድረግ ጀምራለች። በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ያለው ፉክክር የሚታወቅ ነው።ከዚህ በተጨማሪ ሶማሊያ ከቃጣር ጋር ተነጋግራለች። የተባበሩት ኤሜሬቶች ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ወደብ እንዲኖራት በመደገፍ በጉዳዩ እጇ አለበት የሚል ጭምጭምታ አለ” ያሉት ዶክተር አሕመድ “ጉዳዩ በርካታ ተግዳሮቶች እና ዲፕሎማሲያዊ ችግሮች የሚፈጥር ይመስላል” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

ዶክተር አሕመድ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የለየለት ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት የላቸውም። በቀጠናው በተለይ ባለፉት ዓመታት መረጋጋት በራቀው የላስ ናዖድ አካባቢ አንዱ ሌላውን ለማዳከም የእጅ አዙር ግጭት ሊታይች እንደሚችል ግን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW