በኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎች ኑሮና የዘርፉ ተግዳሮት
ማክሰኞ፣ ሰኔ 24 2017
አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻው የህክምናው ዘርፍ ተግዳሮት
በብዙ ወጪና ልፋት ያበቋቸውን የህክምና ባለሙያዎች በሚያስደንቅ ፍጥነት እያጡ ካሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት። «አስቸኳይ መፍትሄ የሚያሻው በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑና በሙያው የተካኑ የኢትዮጵያ የህክምና ዶክተሮች ፍልሰት» በሚል ርዕስ ዶክተር ታደሰ ዘርፉ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት አንድ አስደንጋጭ አውነት የጤና ዘርፏ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ እንደገጠመው ያመለክታል።ጽሑፉ በዋናነት በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑና በየህክምና ዘርፉ የተካኑ ዶክተሮችፍልሰት ከምንግዜውም በበለጠ ከፍተኛ እንደሆነ ያስገነዝባል። ለህክምና ባለሙያዎቹ ወደ ሌሎች ሃገራት መፍለስ ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት መካከልም ከሚሰጡት አገልግሎት አኳያ ዝቅተኛ ደመወዝ መከፈል አንዱ መሆኑንም ያነሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ ዶክተሮችም ሆኑ ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ከ200 ዶላር ያነሰ እንደሚከፈላቸው፣ በአንጻሩ እንደ ጎረቤት ኬንያ፣ ሱዳን ሌላው ቀርቶ ሶማሊላንድ ጭምር የዶክተሮች ወርኃዊ ደመወዝ 1,500 የአሜሪካን ዶላር ገደማ መሆኑንም ያብራራል።
ጽሑፉ በምሣሌነት ካነሳው የደመወዝ አከፋፈል በመነሳትም ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ለእነሱም ሆነ ለቤተሰባቸው የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ፍለጋ፣ የደኅንነት ይዞታው አስቸጋሪ ድባብ ወዳለባቸው እንደ ሶማሊያ ያሉ ሃገራት ሳይቀር ለመሄድ እንዲወስኑ እንዳደረጋቸውም ያስረዳል።
የህክምና ባለሙያዎች ፍልሰት፣ የተባባሰው ቀውስ
ዶቼቬለ ያነጋገራቸው በአሁኑ ጊዜ በአንድ የአፍሪቃ ሀገር በህክምና ሙያቸው እየሠሩና እያተማሩ የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ የማኅጸንና ጽንስ ህክምና ባለሙያ ይህንኑ ነው ያረጋገጡልን። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምና ተማሪ የነበሩት ዶክተር በ16 ዓመታት የአገልግሎት ቆይታቸው የቋጠሩት ጥሪት እንዳነበራቸው ያስተዋሉት ወደ አዲስ አበባ ለሥራ በተዛወሩበት አጋጣሚ እንደነበር አጫውተውናል። በዚህም ምክንያት በአማቾቻቸው ቤት ለወራት ከመኖር የተሻለ አማራጭ አልነበራቸውም።
እሳቸው እንደገለፁልን በጎንደር የአገልግሎት ቆይታቸው ሙሉ ትኩረታቸው ሥራቸውና ለኅብረተሰቡ የሚሰጡት የህክምና እርዳታ ብቻ ነበር። ነፍሰጡር እናቶችን እየተከታተሉ ማከሙና በሙያቸው መርዳቱ የእርካታቸው ጥግ ሆኖ ዓመታትን በፍጹም ሙያዊ ፍቅርና ትዕግሥት አስጓዛቸው።
ኋላም ቤተሰብ መሠረቱ ልጆችንም ወደዚች ምድር አመጡ። ኃላፊነት ከኤኮኖሚ አቅም ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጠ። ለዚህም ነው የተሻለ ገቢ ለማግኘት ከነበሩበት ወደ ዋና መዲና አዲስ አበባ የሄዱት። በግል ሀኪም ቤት የመቀጠር ዕድል በማግኘታቸው የተሻለ ክፍያ ማግኘት ጀመሩ። እልፍ ሲሉ እልፍ የሚለው ብሂል ትርጉሙ ተገለፀ፣ ከዚያም ይበልጥ ለተሻለ ኑሮ፣ ልጆችንም በአግባቡ ለማስተማር ዕድልን ማማተር ቀጠሉ፣ ዛሬ በሌላ የአፍሪቃ ሀገር ጥሩ እየተከፈላቸው በመሥራት ላይ ናቸው። ዘወትር ግን ወደ ሀገራቸው ያስባሉ። ሆኖም ግን ያኔ አብረዋቸው ይሠሩ ከነበሩ ባልደረቦቻቸው የሚደርሳቸው መልእክትም ይረብሻቸዋል።
ሌላው አስተያየታቸውን የሰጡን ሀገር ውስጥ በከፍተኛ ሀኪምነት የሚያገለግሉት ዶክተርም የሚገልጹት ተመሳሳይ ነው። የህክምና ባለሙያዎች በተፈለጉበት አጋጣሚ ሁሉ ወደ ሀኪም ቤት መሄድ ሙያዊ ግዴታ አለባቸው ያሉን እኝህ ዶክተር ያ ሁሉ ተጨማምሮ ለሚሰጡት አገልግሎት የሚከፈላቸው በቂ አለመሆኑ ወደሌላ ሀገር እንዲያማትሩ ዋናው ምክንያት መሆኑን ነው ያረጋገጡት።
በነገራችን ላይ አድማጮች ያነጋገርናቸው ሁለቱም ሀኪሞች ነባራዊ እውነታውን ለመግለጽ ወደኋላ ባይሉም ለእነሱም ሆነ ለቤተሰባቸው ደኅንነት ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈለጉም። በዚህ አጋጣሚ ከእናንተ ለሚደርሱን የተለያዩ ጤና ነክ ጥያቄዎች ማብራሪያ ለመስጠት ከሚተባበሩን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች መካከል ቤተሰብ ለማስተዳደር በቂ ክፍያ ባለማግኘት ወደሌሎች ሃገራት የሄዱ በርካቶች መሆናቸውን ለመግለጽ እንወዳለን። ባህሉም ሆነ ቋንቋውን በሚያውቁት በሀገራቸው ቆይተው ኅብረተሰባቸውን ቢያገለግሉ ግን ይመርጡ እንደነበር ነው የሚገልጹልን። አስተያየታቸውን የሰጡን የጽንስና ማኅጸን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያው ከእነሱ አንዱ ናቸው።
ከ120 ሚሊየን በላይ ሕዝብ አላት በምትባለው ኢትዮጵያ የሀኪሞች ቁጥር ከኅብረተሰቡ ብዛት እንኳን ሊመጣጠን እዚህ ግባ የሞባል አይደለም። እንደ ቅመም በኅብረተሰቡ መካከል በመጠኑ የሚገኙት የህክምና ባለሙያዎች ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ ሊያገለግሉት የሚመኙትን ሳይማር ያስተማራቸውን ኅብረተሰብ ያለ ምትክ እየተው ለአገልግሎታቸው ተመጣጣኝ ክፍያ ሊከፍሏቸው ዝግጁ ወደሆኑ ሌሎች ሃገራት መፍለሳቸው ተባብሶ መቀጠሉ ነው ያነጋገርናቸው ሀኪሞች የገለጹልን። ወደ ጎረቤት ሃገራት የሄዱትም በርካታ ናቸውም ይላሉ።
የህክምና ባለሙያዎች ፍልሰት የሚያስከትለው ተፅእኖ
የህክምና ባለሙያዎች ወደ ሌሎች ሃገራት መፍለስ እንኳን ዘንቦብሽ ዓይነት የሆነውን የሀገሪቱን የህክምና ዘርፍ የባሰ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ነው የዶክተር ታደሰ ዘርፉ ጽሑፍ የሚያሳስበው። እሳቸው እንደሚሉት የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ይዞታ ከጥራትም ሆነ ከተደራሽነት አኳያ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው። የህክምናው መሠረተ ልማት በፍጥነት እያደገ በመሄድ ላይ የሚገኘውን የሕዝብ ፍላጎት ለማስተናገድ በሚችል መልኩ ዝግጁ አይደለም። ምንም እንኳን ህክምናን ለማዳረስ የተለያዩ ጥረቶች ቢከናወኑም አብዛኛው ዘርፍ በቂ በጀት እንኳን የለውም። አስተያየታቸውን የሰጡን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ በቂ የህክምና ግብአት በሌለበት ለሚሠራው ባለሙያ ጫናው ከፍተኛ ነው ይላሉ።
ከሰሞኑ የታየው የሥራ ማቆም አድማ በማይደረግበት ዘርፍ ትኩረት ለማግኘት በሚል የህክምና ባለሙያዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ እንደ ድንገት ደራሽ ሳይሆን የከረመና ተደጋግሞ ሲጠየቅ የነበረ እንደሆነ የሚናገሩት ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎቹ ዘንድሮ ያለው የኑሮ ውድነት አባብሶት ወደ ተቃውሞ እንቅስቃሴ መቀየሩ የሂደቱ ውጤት ያስከተለው ነው ባይ ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ የህክምና ባለሙያዎቹ መፍትሄ ሳያገኙ የተጠራቀሙ ችግሮቻቸውን በይፋ ለሚመለከተው አካል አቅርበዋል። የደመወዝ ጉዳይ ቀዳሚው ቢሆንም የአዳርና የትርፍ ሰዓት አገልግሎታቸውን ያማከለ፤ በልዩ ልዩ ህመም የተያዙ ወገኖችን እንደማከማቸው ለበሽታ ተጋላጭነት በሚል የሚሰጣቸው ድጎማ ማነስ፤( እንደገለጹልኝ ለዚህ እስከዛሬ የሚከፈላቸው አንድ ሺህ ብር ነው፤) የተረኝነት ወይም እነሱ ዲዩቲ የሚሉትን ክፍያ በወቅቱ አለማግኘት፤ ስልጠና እና ተጨማሪ ትምህርቶችን የሚመለከት፤ በጤና ተቋማት አካባቢ ያለው ደኅንነት እንዲሁም ለባለሙያው የሚሰጠው ክብር ጉዳይና ተያያዥ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠይቀዋል። መንግሥት ለመጪው ዓመት በጀት ከውጪ የሚገኝ ያለውን ርዳታ ጨምሮ ለጤና ዘርፉ 48 ቢሊየን ብር መመደቡን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። ይህ ለተለያዩ ዘርፎች ከተመደበው እጅግ አናሳ መሆኑ ተጠቁሟል። ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ይገኝ ይሆን?
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ