በኢትዮጵያ የሚታየዉ የዋጋ ግሽበት መረጋጋት ታይቶበታል?
ዓርብ፣ መጋቢት 19 2017
በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበቱ መረጋጋት አሳይቷልን?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተከተለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ባለፉት ወራት የዋጋ ግሽበት መርገብ እንደታየበት የብሔራዊ ባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አስታወቀ። ዋጋን ማረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገትን ከመደገፍ ዓላማ ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለብሔራዊ ባንኩ የሚያቀርበው ኮሚቴው መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀምጦ ከገመገማቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች አንደኛው የዋጋ ግሽበትን ወቅታዊ ሁኔታ ነው። ካለፈው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ወዲህ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ በመምጣት የካቲት ወር 2017 መጨረሻ 15 በመቶ መድረሱንም ኮሚቴው መገንዘቡ ተገልጿል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ በዚህ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ነው የገለጹት።
ባለፉት ጥቂት ወራት የዋጋ ግሽበት በተከታታይ እየረገበ የመጣው ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመከተሉ፣ የግብርና ምርት በመሻሻሉና በአስተዳደራዊ ዋጋዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ማሻሻያ ቀስ በቀስ በመተግበሩ ምክንያት እንደሆነ መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ግምገማውን የተቀመጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አስተውቋል።
እንደ ኮሚቴው ግምገማ በየካቲት ወር 2017 መጨረሻ 14.6 በመቶ የደረሰው ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል ብሏል። ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበትም ቢሆን ወደ 15.6 በመቶ ቀንሶ ባለፉት ጥቂት ወራት ግን የማንሰራራት አዝማሚያ ማሳየቱ ነው የተመላከተው።
ባለፈው የካቲት ወር የ0.5 በመቶ ወርሃዊ ዕድገት ብቻ መታየቱን ያመለከተው ኮሚቴው ይህም የዋጋ ግሽበት በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አዲሰ ተጽእኖ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያመለክት ብሎታልም። ኢትዮጵያውያንን የሚፈታተነው የዋጋ ግሽበት
ስለዋጋ ግሽበት የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አሰርተያየት
መሻሻል አሳይቷል በተባለው የዋጋ ግሽበት ላይ ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ኢኮኖሚው ባለሙያ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ግን የዋጋ ግሽበቱ መረጋጋትን አሳይቷል ለማለት ቢያንስ የገንዘብ የመግዛት አቅም መረጋጋት ማሳየት ይኖርበታል የሚል አስተያየታቸውን ነው የሰጡት። “የዋጋ ንረትና የዋጋ ግሽበት በራሳቸው ልዩነት አላቸው። የዋጋ ንረቱ ወደ ዋጋ ግሽበቱ ተሸጋገረ የሚባለው ከ6 ወር እስከ ሁለት ዓመታት ተከታታይ የምርቶች የዋጋ ጭማሪ ሲስተዋል ነው። ሌላው ቢቀር ከተነጻጻሪው ጊዜ ጋር የገንዘቡ የመግዛት አቅም ደካማ ከሆነ ገሽቧል ማለት እንችላለን” ነው ያሉት።
እናም አሉ ባለሙያው፤ የዋጋ ግሽበቱ ከቁጥርም በላይ መታየት ያለበት ነው። “ግሽበት በቁጥርም በአይነትም ነው መታየት ያለበት። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚው ከቁጥርም በተጨማሪ በአይነት (ጥራት) ነው የሚታየው” ያሉት አቶ ሸዋፈራሁ፤ “የኑሮ ጥራቱ ምንያህል ደርሷል፣ በዚህ ውስጥ ደግሞ የዋጋ ጭማሪው ሁኔታ አስተዋጽኦው አሉታዊ ነው ወይስ አዎንታዊ የሚለው መገምገም አለበት። በመንግስት በኩል የሚነገረው ከሳይንስ ውጪ የሚሆንብኝ፤ የዋጋ ቅነሻው እንኳ የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ አሻሽሏል ወይ የሚለው ነው” ሲሉ ሞግተዋል። “የቁጥር ጫዋታው” በፖለቲካው የታየ እንዳይሆን የሚል ሰርጋታቸውን ገልጸዋል። የዋጋ ግሽበት በባለሙያዎች እና ነዋሪዎች አተያይ
የዋጋ ግሽበት ስብራቱ እንዴት ይጠገን?
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የዋጋ ንረት የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደስብራት ያየው አንዱ ጉዳይ እንደነበር አስታውሰው በዚህ ዓመት ግን ግሽበቱን ከ29 በመቶ ወደ 15 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። “በተሰራው ጣልቃ መግባት ከፍተኛው ውጤት መጥቷል። አንደኛው ቀደም ሲል የገንዘብ ጉድለት ከብሔራዊ ባንክ የሚሟላበትን መጠን በመገደብ፣ የመርት ጭማሪ እና የገቢ ትስስር በማሻሻል ግሽበቱን መቀነስ ተችሏል” ነው ያሉት። ግሽበትን ዜሮ ማድረግ እድገትን መግታት ነው ያሉት ዐቢይ ምርት ማሳደግና ወደ ገቢያ በማቅረብ ብሎም የገቢያ ስርዓቱን በማዘመን እምርታ ማምጣት እንደሚቻልም አስረድተዋል።
የፖለቲካል ኢኮኖሚው ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ግን ግሽበቱ አሁናዊው ኢኮኖሚያዊ ፈተና ለመሆኑ ትልቁ ምክንያት ይህ ነው ይላሉ።
“ችግሩ የትም ይሆን የት፤ አቅርቦትና ፍላጎት እንዲመጣጠን ግጭትን መፍታት፤ ከዚያም የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ማሻሻል ብሎም ምርታማነትን በማሳደግ ሰላምን አረጋግጦ መርትን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ብቻ መፍትሄ ነው” በማለት የችግሩንም መንጭ ሆነ መፍትሄውን አመላክተዋል።
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ