1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ድርቅና ረሃብ ፤ የአገዛዞች ዳተኛ ምላሽ

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2016

በየወቅቱ በሃገሪቱ የተፈራረቁ አገዛዞች በድርቅ የሚሞት ሕዝብ ከመታደግ ይልቅ``ለገጽታ ግንባታ`` በሚል አደጋውን መደበቅ፤ የእርዳታ እህል መዝረፍ፤የሃገሪቱን ውሱን ሃብት ቆጣቢ በሆነ መልኩ በመጠቀም አደጋዎቹን ከመመከት ይልቅ ለቅንጡ መናፈሻዎችና ቤተመንግስት ግንባታና እድሳት በቢልዮኖች የሚቆጠር የሃገሪቱ ሃብት ያባክናሉ በሚል ብዙዎች ይወቅሳሉ።

Pastoralisten Somalia
ምስል፦ DW/J.Jeffrey

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ድርቅና ረሃብ ፤ የአገዛዞች ዳተኛ ምላሽ

This browser does not support the audio element.


ተፈጥሮ ወተት እንደነጠፈች ጥገት ሰማዩ ጠብ የሚል ውሃ ተስኖት በሚከሰተው ድርቅ፤ ፖለቲከኞች በጠረጴዛ ዙርያ ተወያይተው፤ ሃሳባቸውን ለሕዝብ ሸጠው በምርጫ ካርድ ብቻ የስልጣን እርካብ የመቆናጠጥ ልምምዱ ጨርሶ ባለመኖሩ አንዱ ሌላኛውን ለማጥፋት በሚለኩሱት እሳት እና በሌሎች ምክንያቶች በኢትዮጵያ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ የአካልና የንብረት ውድመት ተዳርገዋል። አሁንም  መልኩን ይቀያይር እንደሆነ እንጂ ፈተናዉ «ባለህበት እርገጥ» እያለ ነዉ። በኢትዮጵያ ድርቅና ሰዉ ሰራሽ  ችግሮች በሚያደርሱት ጉዳቶችና በየጊዜው የተፈራረቁ አገዛዞች ዳተኛ ምላሽ ላይ መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን አብራችሁን ቆዩ።
    
የአጼ ሃይለስላሴ መንግስት በወሎና በትግራይ የተከሰተውንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ሕይወት የቀጠፈው ርሃብ ከአጠቃላይ የሥርአቱ ጥፋቶች ጋር ተዳምሮ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዓመጽ እንዲፋፋም አድርጎታል።ጥናቶች እንደሚጠቁሙት  ከ1965 እስከ 1966 በወሎ ብቻ ከ200,000 በላይ ሰዎች በርሃብ አልቀዋል። የወቅቱ የሃገሪቱ መሪ የነበሩት አጼ ሃይለስላሴ ድርቁ እንዳይታወቅ ከመሸፋፈን በተጨማሪ የንጉሳውያኑ ቤተሰቦች የተቀናጣ የሃብት አጠቃቀምና ብክነት ሕዝቡን ለዓመጽ ካነሳሱ እልፍ ችግሮች አንዱ ሆኖ ስልጣናቸውን እስከማሳጣት እንዳደረሳቸው በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ አቶ ሰሎሞን ተሰማ ያስታውሳሉ።
`` በወቅቱ የነበሩ የተማሪች ንቅናቄ ተሳታፊዎች ሁለት ነገሮች ላይ አተኩረዋል። አንደኛው የአጼ ሃይለስላሴ ሉሉ የተባለችው ውሻ ስትሞት የወርቅ መቃብር አሰርተዋል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አጼ ሃይለስላሴ ልደታቸውን ሲያከብሩ ኬክ ከለንደን ነው የመጣው፤ሕዝብ እየተራበ ሻምፓኙም ምኑም ከለንደን ነው የመጣው የሚሉ ናቸው።``

በትግራይ በጦርነቱ ከተፈናቀሉት በከፊልምስል፦ Million Haileselassie/DW

በአማካይ በየ10 ዓመቱ የሚከሰተው ድርቅ ሚልዮኖችን መቅጠፍ ማፈናቀል ቀጥሏል። በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ በተከሰተ ድርቅ 1.2 ሚልዮን ዜጎች ሲቀጥፍ ከ400,000 በላይ እንዲሰደዱ እንዳደረገ የታሪክ ድርሳናት መዝግበውታል። በወቅቱ የዓለም ማሕበረሰብ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት በርካታ ሃብቱን ቢያፈስም በስልጣን ላይ የነበረው የደርግ መንግስት ግን ለጉዳዩ ትኩረት በመንፈግ ለፓርቲ ምስረታ ድግስና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ሕንጻ በማሰራት ላይ ተጠምዶ እንደነበር፤ በወቅቱ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ይካሄዱ በነበሩ የእርስበእርስ ጦርነቶች የጦርመሳሪያ ግዢ በቢልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ይመነዝር እንደነበር ፖለቲከኞች ይወቀሳሉ።
በወቅቱ ደርግን ለመጣል ነፍጥ አንግቦ ሲዋጋ የነበረው ህወሐትም በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የመጣውን የእርዳታ እህል ወደ ጎረቤት ሃገራት እያሻገረ በመሸጥ ለጦርነት ያውለው እንደነበር ነባር የድርጅቱ አመራር አባላት የከተቡትን ድርሳን ዋቢ አድርገው የታሪክ ሙሁሩ አቶ ሰሎሞን ገልጸዋል።

በቦረና የተከሰተው ድርቅ በርካታ ከብቶች አልቀዋልምስል፦ Seyoum Getu/DW

በኢህአዴግ ብልጽግና የአገዛዝ ዘመንም ድርቅ ሊያስከትለው የሚችል ጉዳትን ለመቀነስ ቅድመ ትንበያ በመስራት አስፈላጊውን ቅድመዝግጅት ከማድርረግና ድርቁ ሲከሰት ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ለገጽታ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ዓለም አቀፍ ለጋሾች የሚያወጡትን የተጎጂዎች ቁጥር ከማሳነስ ጀምሮ ቅንጡና ወቅቱን ያልዋጁ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እየሰጡ ነው በመባል ይወቀሳሉ። 

በትግራይ ዉስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተደረገዉን ጦርነት ተከትሎ የደረሰው መፈናቀልና ርሃብ ሳያንስ አሁን በተፈጥሮ ምክንያት በተከሰተ የረሃብ አደጋ ብዙዎች እየሞቱ ነው። ድሮ ድሮ በትጥቅ ትግሉ ጊዜ የእርዳታ እህል በመሸጥ ስሙ የሚነሳው ህወሐት አሁንም በረሐብ የሚሞተዉን ሕዝብ ለማዳን አቅሙን አስተባብሮ ከመስራት ይልቅ ``ህወሐትን ለማዳን`` በሚል 3 ሳምንታት በሩን ቀርቅሮ ግምገማ ላይ መቀመጡን ብዙዎችን እንዳሳዘነ እየተነገረ ነው። 
ይህን ተግባር ያሳሰባቸውየትግራይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  ድርጊቱን አብዝተው ኮንነዋል። ዶክተር ደጀን መዝግቡ የትግራይ ነጻነት ድርጅት በትግርኛ ምህጻሩ ውናት ሊቀመንበር።
`` የረሃቡ ሁኔታ በጣም ከባድ፣ ጥልቀት ያለውና መቆጣጠር የማንችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። በጥናት የተደገፈ ቅድመ ማስጠንቀቂያም አልነበረም። የትግራይ ሕዝብ የሚያየው ሰው የለም። ህወሐትም በራሱ የስልጣን ሽኩቻ ላይ ነው ተጠምዶ ያለው። ለሕዝቡ ደንታ አልሰጠውም። 3 ሳምንት የሚሆን ድርጅታቸውን በማዳን ላይ ነው ተጠምደው ያሉት እንጂ ሕዝቡን በማዳን ላይ አደለም።``
የፌደራል መንግስትም በትግራይ፣ በአማራ፣ በዓፋር፣ በኦሮሚያ፣ በሶማልና ደቡብ ክልሎች  በድርቅና በጦርነት እንዲሁም ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ከ 4 . 3 ሚልዮን የሚልቁ ዜጎች ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያው ``የእህል ያለህ!`` እያሉ በተረበ አንጀታቸው፤ በሰለለ ድምጻቸው ቢጣሩም መንግስት ግን መናፈሻና ቤተመንግስት ከመገንባት አልመለስም ማለቱን ቀጥሎበታል በማለት ብዙዎች ሲወቅሱ ይደመጣል።

የዕርዳታ እህልምስል፦ AP Photo/picture alliance

በየወቅቱ በሃገሪቱ የተፈራረቁ አገዛዞች በተፈጥሮና ሰውሰራሽ ምክንያቶች በሚፈጠሩ አደጋዎች የሚሞት የሚፈናቀለውን ሕዝብ ``ለገጽታ ግንባታ`` በሚል አደጋውን መደበቅ፤ ለተረጂዎች ከዓለም አቀፍ ለጋሾች የተላከውን እህል መዝረፍ፤ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ የሃገሪቱን ውሱን ሃብት ቆጣቢ በሆነ መልኩ በመጠቀም አደጋዎቹን ከመመከት ይልቅ ቅንጡና መሰረታዊ ለማይባሉ መናፈሻዎች፣ ቤተመንግስትና ቢሮዎች ግንባታና እድሳት በቢልዮኖች የሚቆጠር የሃገሪቱ ሃብት ማዋል ዝውቱር ተግባራቸው ሆኗል በማለት ብዙዎች ይወቅሳሉ። የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ካሳ ``የተራበ ሕዝብ መሪውን ይበላል`` በማለት ያስጠነቅቃሉ።
``የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሰው የሚበላውን ካጣ እራሳቸውን ነው የሚበላቸው።`` 
በመላ ሃገሪቱ በድርቅ፣ በጦርነትና ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት በየቦታው በረሃብ የሚሰቃዩ ወገኖች ጬኸት የሚሰማው መች ይሁን?

 ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር 

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW