1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የሰሞኑ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ተከሰተ?

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ መስከረም 29 2017

ሰሙኑን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የመሬት መንቀጥቀጥ መታየቱን ነዋሪዎች እና ባለሙያዎች ገልጸዋል።ለመሆኑ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ይከሰታል?በኢትዮጵያ የትኞቹ አካባቢዎች ተጋላጭ ናቸው?አደጋው ሲያጋጥም ምን ጥንቃቄ መደረግ አለበት?የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎችስ?

3D-Illustration eines schweren Erdbebens
ምስል Cigdem Simsek/Picture alliance

በኢትዮጵያ የሰሞኑ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ተከሰተ?

This browser does not support the audio element.

ሰሞኑን በአፋር ክልል ፈንታሌ ተራራ የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ በአዳማ ፣በመተሃራ በአዋሽ አርባ እንዲሁም በመዲናዋ አዲስ አበባ  የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ክስተት ታይቷል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም  ይህንኑን መረጃ አረጋግጧል። 
የአሜሪካ  የመሬት መንቀጥቀጥ ይፋዊ ድረ-ገፅም መታሃራ አካባቢ መካከለኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን አስታውቆ፤  ክስተቱ የ10 ኪሎ ሜትር  ጥልቀት እንደነበረው ገልጿል።የተከሰተው መንቀጥቀጥ ንዝረቱ ከ380 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ መሰማቱንም ድረ ገጹ አሳውቋል፡፡በአዲስ አበባ ይንቨርሲቲ የጅኦ ፊዚክስ ፣የህዋ ሳይንስ እና የአስትሮኖሚ  መመህር እና ተመራማሪ  የሆኑት ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ክስተቱ ለዚህ አካባቢ አዲስ አይደለም ይላሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም  መረጃ እንደሚያሳየው በፈንታሌ የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 4.9 የሚለካ ነበር።ፕሮፌሰር አታላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የተከሰተው የመሬት ንዝረት  መነሻም በአፋር ክልል ፈንታሌ ተራራ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ነው።

ፕሮፌሰር አታላይ አየለ በአዲስ አበባ ይንቨርሲቲ የጅኦ ፊዚክስ ፣የህዋ ሳይንስ እና የአስትሮኖሚ  መመህር እና ተመራማሪ ምስል Privat

ርዕደ መሬት እንዴት ይከሰታል?


የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ርዕደ መሬት በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣በመሬት ንጣፍ ላይ  የአለቶች መውደቅ እና  ከርሰ ምድር ውስጥ በሚፈጠር ፍንዳታ በአነስተኛ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል።በዋናነት  ግን ርዕደ መሬት ከምድር  በታች በሚገኙ አለታማ  ቁሶች ግጭት  የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። ይህ ግጭት የሚፈጠረው የምድር ንጣፎች ወይም «ቴክቶኒክ ፕሌትስ» በሚሰኙት ጠርዝ ላይ ነው። እነዚህ የምድር  ንጣፎች የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ  በመሆናቸው  አንዳንዴም ዕርስ በዕርስ  የሚጋጩበት ጊዜ አለ።ይህ ድንተኛ ግጭት የሚፈጥረው ንዝረት እና ሞገድም ምድርን በመሰንጠቅ  ርዕደ መሬት እንደፈጠር ያደርጋል።ለመሆኑ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የተከሰተው ርዕደ መረት መነሻ የትናው ነው? ፕሮፌሰር አታላይ እንገለፁት ሰሞኑን በኢትዮጵያ የተከሰተው ርዕደ መሬት በእሳተ ገሞራ በቀለጠ አለት ምክንያት ነው።«መነሻው ከሚመዘገበው ዳታ ለማየት እንደሞከርነው የቅልጥ አለት ከስር ወይም ፍል ውሃ የሚሆነው ማለት ነው።የቅልጥ አለት ከስር እየሰረሰረ ወደላይ ይወጣል ለመፈንዳት ።የታመቀ ሀይል ማለት ነው።እና ያ አለቱን እየደረመሰ ለመውጣት ሲታፈን፤ ከፍተኛ የታመቀ ሀይል ነው እና አለቱን ሲሰብር ነው መሬት መንቀጥቀጥ የሚፈጠረው።»በማለት ገልፀዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ 81 በመቶው የሚሆነው አብዛኛው አውዳሚ ርዕደ መሬት የሚከሰተው በፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ  አካባቢ ነው።ይህ የሆነበት ምክንያትም የመሬት ንጣፍ /ፕሌቶች/ በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት በዚሁ አካባቢ በመሆኑ ነው።ከሁለት ዓመት በፊት ጥር 29 ቀን 2015 ዓ/ም አውዳሚ  ርዕደ መሬት የተከሰተባቸው ቱርክ እና ሶርያም በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ሀገሮች ናቸው።

በጥር 2015 በቱርክ የተከሰተው የመረት መንቀጥቀጥ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነበርምስል Bulent Kilic/AFP

ፕሮፌሰር አታላይ እንደገለፁት በእነዚህ ሀገራት የተፈጠረው ክስተት  የአረቢያን የመሬት ንጣፍ  /ፕሌት/ ወደ ሰሜን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከምስራቅ አናቶሊያ የመሬት ንጣፍ /ፕሌት/ ጋር በመጋጨቱ የተፈጠረ  ነው። በወቅቱ ጉዳቱን ከፍ ያደረገውም ይኸው መነሻው መሆኑን ገልፀዋል። በኢትዮጵያ ግን መነሻው ከዚህ የተለዬ በመሆኑ የጉዳቱ መጠንም ይለያል።
የመሬት ንጣፍ /ፕሌቶች/ በአብዛኛው የሚንቀሳቀሱት በፓስፊክ ውቅያኖስ  ዳርቻ አካባቢ በመሆኑ በዓለም ላይ አብዛኛው አውዳሚ ርዕደ መሬት የሚከሰተው በዚሁ አካባቢ ነው።ኢትዮጵያም በአፍሪካ እና በአረብ ፕሌቶች አቅጣጫ የምትገኝ ሀገር በመሆኗ፤ በተለይ በሰምጥ ሸለቆ አካባቢ ለርዕደ መሬት ተጋላጭ ነች።ከዚህ አኳያ በተለይ  በሰምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያ ከተሞች በተለዬ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው።

የሚያደርሰውን ጉዳት ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ መቀነስ ይቻላል


ርዕደ መሬት አነስተኛ፣  መካከለኛ እና ከፍተኛ በመባል በሶስት ሊከፈል ይችላል።እንደ ፕሮፌሰር አታላይ ሰሞኑን የተከሰተው ርዕደ መሬት መካከለኛ የሚባል ነው።ርዕደ መሬት ከተፈጥሯዊ በተጨማሪ በሰው ሰራሽ መንገድ በግንባታ፣ በማዕድን ቁፋሮእና በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ ሊከሰት ይችላል። እነዚህን ሰውሰራሽ መንስኤዎች መከላከል ቢቻልም በተፈጥሮ የሚከሰትን ርዕደ መሬት ግን መተንበይም ሆነ መከላከል አስቸጋሪ ነው።ነገር ግን ፕሮፌሰር አታላይ  እንደሚሉት የሚያደርሰውን ጉዳት ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ መቀነስ ይቻላል።ከነዚህም መካከል ጠንካራ የህንፃ ግንባታ  አንዱ መሆኑን ያስረዳሉ።
ስለሆነም ከጥንቃቄ ባሻገር ስለ አካባቢ ጥበቃ እና የተፈጥሮ አደጋ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በተለያዩ መንገዶች ማሳደግ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW