1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ የኢሰመጉ ጥያቄ

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 8 2018

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከፍተኛ መሻሻልን የሚጠይቅ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ገለጠ ። ሰብአዊ ድርጅቱ ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ሰላማዊ አማራጮች እንዲከተሉም አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አርማ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አርማምስል፦ Ethiopian Human Rights Council

ነባራዊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ በኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከፍተኛ መሻሻልን የሚጠይቅ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ገለጠ ። ሰብአዊ ድርጅቱ ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ሰላማዊ አማራጮች እንዲከተሉም አሳስቧል፡፡

በጎርጎሪዮሱ ታኅሣሥ 10 የተከበረውን 77ኛው የዓለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቀንን በማስመልከት በአገር ውስጥ ተዘዋውሮ የተፈናቃዮች ሁኔታን እና በቁጥጥር ስር የሚገኙ የተጠርጣሪዎችን አያያዝ መመልከቱን በመጠቆም፤ ይስተዋላሉ ያሏቸውን አሁናዊ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ሁኔታ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዓለማቀፋዊ የሰብአዊ መብት ቀን በሚታወስበት ባሁን ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ልዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ ብሏል፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች በሚፈጸሙ በነዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መንግስት እና ከመንግስት ውጪ ያሉ አካላት ይሳተፋሉ ያለው ኢሰመጉ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመት እና ሌሎችም ዘርፈብዙ ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች  እንደሚስተዋሉ ማረጋገጡን በሪፖርቱ አንስቷል፡፡

ነባራዊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ

በዚህ ላይ ተጨማሪ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ፤ «በፕሪቶሪያ ስምምነት የተቀመጡ ጉዳዮች እስካሁን ካለመተግበራቸው ጀምሮ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች ሰላም የመደፍረስ ሁኔታ በርካቶች ሰብአዊ መብታቸው እንዲጣስ ምክንያት ሆኗል» ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥበቃዎችን የተሟላ የሚያደርጉ ድርጊቶች በሚቀርቡት ምክረሃሳቦች ልክ በዋናነት ኃላፊነት ባለው መንግስት በተሟላ መልኩ አልተፈጸመም የሚል አስተያየታቸውን ያከሉት አቶ ተስፋዬ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቡድን እና በተናጥል ወደ ሰላም የሚመጡ ታጣቂዎች ጉዳይ ግን በአዎንታዊ መልኩ የሚታይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና አሁንም  ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ መሻሻልን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ተግባራት መሬት ላይ ይታያሉ የሚሉት የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ ኃላፊ ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ መሥራት አስፈላጊነቱ እንደሚጎላም አንስተዋል፡፡ «ግጭቶችን የመፍታት ሂደቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው» በማለትም በትግራይ ክልል የተጀመረው ችግሮችን በሰላም የመፍታት ጥረቱ ተፈናቃዮቸን ወደ ቀዬያቸው በመመለስ እና የትጥቅ መፍታት ሂደቱን የተጨበጠ በማድረግ ሊባባስ የሚችለውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተሸሻለ መልኩ ማስኬድ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡

እንደ አገር እየተሠሩባቸው ናቸው የሚባሉትን የሽግግር ጊዜ ፍትህ እና የምክክር ኮሚሽን ሥራዎችንም ወደ ተጨበጠ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡ በእስር ላይ ያሉ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች እና ፖለቲከኞችን ለሰላም ሲባል በሕግ አግባብ እና አንዳንዴም በምሕረት መፍታት እንደሚያስፈልግ የገለጹት የሰብአዊ ድርጅቱ ኃላፊ ሕግን እንዳስፈላጊነቱ የማሻሻል ሁኔታም ልታሰብበት እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡

«በግጭትም ላይ ያሉ አካላት እንታገልለታለን ለሚሉት ወገን ሲሉ ሰላማዊ መንገዶችን አማራጭ ማድረግ አለባቸው»፦ ኢሰመጉምስል፦ Tiksa Negeri /REUTERS

ተጠያቂነትን ለማስፈን..

የሰብአዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ቀዳሚ ግዴታ የመንግስት ነው ያለው  ኢሰመጉ፤ መንግስት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ  በተፈለገው ልክ እንዲሻሻል ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና አገራዊ መግባባት ላይ መሥራት፣ የዜጎች ደህንነት ላይ መሥራት እና ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ አተኩሮ እንዲሠራም ምክረሃሳብ አቅርቧል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ በዚሁም አክለው፤ «በግጭትም ላይ ያሉ አካላት እንታገልለታለን ለሚሉት ወገን ሲሉ ሰላማዊ መንገዶችን አማራጭ ማድረግ አለባቸው» በማለት ሁሉም ወገን የሰብአዊ መብቶች የተከበሩበትና ሰላማዊ አገር እንዲኖረን መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

ኢሰመጉ ያወጣውን ሪፖርት በማስመልከት ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ እናታለም መለሰ እና የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም ለዛሬ ምላሻቸውን ማግኘት አልተቻለም፡፡

ኢሰመጉ በሪፖርቱ እንዳጠቃለለው ግን በግጭት ውስጥ ተሳትፎ የሚያደርጉ አካላትን ጨምሮ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የሲቪል ተቋማት ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሰብአዊ መብቶች መከበር በጋራ አዎንታዊ ሚናቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ሲል ጠይቋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW