1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህና ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት ይካሄዳል ተባለ

ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015

በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህና ቀጣይ የሽግግር ፍኖተ ካርታ መከናወን ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ማኀበራት ጉባዔ አስታወቀ።በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵውያን ህዝባዊ ማኀበራት ጉባኤ፣ (ኢሕማጉ) በውጭ የሚገኙ 11 የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ማኀበራትና ስብስቦችን ያቀፈ ነው።

Karte Äthiopien englisch

የውይይቱ ዓላማ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ ነው

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህና ቀጣይ የሽግግር ፍኖተ ካርታ መከናወን ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ማኀበራት ጉባዔ አስታወቀ።በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵውያን ህዝባዊ ማኀበራት ጉባኤ፣ (ኢሕማጉ) በውጭ የሚገኙ 11 የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ማኀበራትና ስብስቦችን ያቀፈ መሆኑን የድርጅቱ መስራችና አመራር አባል አቶ ሳሙኤል ሃብቴ በተለይ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል።

አቶ ሳሙኤል እንደሚሉት፣የኢትዮጵያ ህዝባዊ ማኀበራት ጉባኤ ካነገባቸው ዓላማዎችና ግቦች ማኸከል፣ለኢትዮጵያ ይበጃታል ያሉትን የሽግግር ሂደትና ዴሞክራሲያዊ ሕገመንግስት የሚረቀቅበትን መንገድ መርምሮ ምክረ ዐሳብ ማቅረብ ነው።

"ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሽግግር ዘመን የሽግግር ስርዓት ምን መምሰል አለበት? ምን ዓይነት ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነው መመስረት ያለበት?ሕዝብ የስልጣን ምንጭና ባለቤት የሚሆንበትንና የሚረጋገጥበት ስርዓት እንዴት ያለዉ ሊገነባ የሚችለው የሚለውን ነገር ፣ይህንን የሽግግሩን ስርዓት ስርዓት መያዝ የሚገባውን በእኛ አነጋገር፣ የባላደራ መንግስት ሕዝባዊ ሥርዓት ማምጣት የሚችል፣ከሕዝብ የተውጣጣ ፣ዕውን ለማድረግ እንድንችል ህብረተሰቡ ጋር መነጋገር መቻል አለበት።ለእዚህም ደግሞ ህዝባዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ህብረተሰባችን በማውረድ፣ህዝባዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት የሕዝቧን ሉዓላዊነት ጭምር ከነጥቅሞቿ ማስጠበቅ የሚቻልበትን ፖለቲካዊ ስርዓት መፍጠር ይኖርብናል ብለን ስራ ከጀመርን ከሁለት ዓመታት በላይ ሁኖናል።"

ጉባዔው፣በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ መከናወን ስላለባቸው ጉዳዮችም ውይይት የማካኼድ ውጥን አለው።ይህንን ተልዕኮ በተቀላጠፈ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግም፣ "የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ማኀበራት ጉባዔ" የተሰኘ የጋራ መድረክ ማቋቋማቸውን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል።

"በመሰረቱ ይህ ሕዝባዊ ውይይት፣ የፖለቲካ ፓርቲ አይደለም። ግን እንደ ሕዝባዊ ድርጅትነቱ፣ሕዝባዊ ንቅናቄ፣ዐሳብን በሕብረተሰቡ ውስጥ ወደ መሬት እንዲወርድ በማድረግ፣ይሄ ዴሞክራሲያዊ ዐሳብ የምንለው፣ የዴሞክራሲ ስርዓት መዘርጊያ ማረጋገጫ የመግባቢያ አስተሳሰብ፣በህብረተሰቡ ውስጥ ገብቶ፣ሕብረተሰቡ ደግሞ ኀይል ሆኖ ያንን ዐሳብ ወደ ተግባር እንዲተረጉመው፣እና የፖለቲካ ስርዓቱን እንዲቆጣጠር የፖለቲካ ስርዓቱን ሕዝብ በመረጣቸው፣ ዲሞክራቲክ በሆኑ ኃይሎች እንዲያዝ የማድረግ እንቅስቃሴ እና ቅቡልነት ያለዉ ሕገ መንግስት እንዲኖር፣ ፍትሓዊ የሆነ ሕዝባዊ ምርጫ እንዲደረግ፣በእነዚህ ነገሮች ላይ፣የምንሳተፍ ወይም ሕብረተሰቡ ነጻና ፍትዓዊ ምርጫ ዕድል አጋጥሞች የራሱን መብት እንዲያረጋግጥ ሁኔታዎች ለማመቻቸት ነው እኛ የቆምነው።"

አዲሱ ጉባዔ፣ በዓለም አቀፍና በኢትዮጸያ ህግጋት እንደአስፈላጊነቱ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በንጹሃን ላይ ፖለቲካዊ ወንጀሎች የፈፀሙ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ወደፍርድ እንዲቀርቡ እንደሚሰራም ተመልክቷል።

ከጉባዔው መሥራች ድርጅቶችና ስብስቦች መኻከል፣የኢትዮጵያኖች የውይይትና የመፍትሔ መድረክ፣ ራዕይ ለኢትዮጵያ፣የኢትዮጵያ የሴቶች መብት ማዕከል፣ አለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት፣ዲሲ ግብረ ኀይልና የአለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሲቪል ድርጅቶች ኔትወርክ ይገኙበታል።

የጉባኤው መስራችና የአመራር አባል አቶ ሳሙኤል እንደተናገሩት፣ሌሎች በጉባዔው ዓላማ ላይ የሚስማሙ ህዝባዊ ድርጅቶችን በማካተት ይበልጥ የመጠናከር ውጥን ተይዟል።

"ሌሎችንም በሰሜን አሜሪካም ሆነ በአውሮፓ፣በአውስትራሊያ፣በኢትዮጵያና በካናዳ ያሉትን ተመሳሳይ ሕዝባዊ ድርጅቶችን በመቅረብ፣በዓላማ ላይ እስከተግባባን ድረስ መስማማት ከቻልን ራዕያችን ተመሳሳይ ከሆነ እያሰፋነው እንደስሙ ጉባዔ ነው የሚለው በጉባዔ ደረጃ እያሳደግነው እንሄዳለን ብለን ተስፋ ጥለናል።"

የኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ማኀበራት ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕግ የበላይነት፣እኩልነት፣ ነፃነትና የፍትሕ መብቶቹን እንዲያስከብር፣ለመደገፍና ለማበረታታት የሚያስችለውን ድርጅታዊ ደንብ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ለማወቅ ተችሏል።

ታሪኩ ሀይሉ

አዜብ ታደሰ

ፀሀይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW