በኢትዮጵያ የብሔርና የማንነት ጥያቄ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 25 2016በኢትዮጵያ የብሔር ግጭት እንዲስፋፋና የማንነት ጥያቄ አወዘጋቢ እንዲሆን የሚያደርጉት፣ ለስልጣንና ለኃብት የሚሻኮቱ ኀይሎች መሆናቸውን ታዋቂ የታሪክ ምሁራን ገለጹ። ምሁራኑ፣ኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ ጉባዔ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ባቀረቡት ገለጻ፣ ኢትዮጵያውያን ከሚያለያያቸው ይልቅ፣ ለብዙ ሺህ ዓመታት ያጋመዷቸው በርካታ የአብሮነት እሴቶች እንዳላቸው አስረድተዋል። "ኢትዮጵያዊነት የአብሮነት እና የጥንካሬ ምስጢር" በሚል ርዕስ በዘጋጀው በዚህ ውይይት ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ካቀረቡት ምሁራን መኻከል አንዱ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ናቸው።
የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴቶች
ፕሮፌሰር ባህሩ፣መልክዓ ምድርና ቋንቋ፣ ንግድ፣ ጋብቻ፣ ምግብ፣ ስፖርት፣ የፖለቲካ ስልጣንና ለኢትዮጵያ ነጻነት በጋራ መቆምን የመሳሰሉት፣ ኢትዮጵያዊያንን ለዘመናት ያስተሳሰሩ የጋራ እሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል። የፖለቲካ ስልጣን ለዘመናት የኢትዮጵያዊነት አብሮነት መገለጫ እሴት እንዴት እንደሆነ ሲያስረዱ የሚከተለውን ብለዋል። "አሁን በተለምዶ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዐማራ እና በትግሬ ዶሚኔትድ ይሆናል ግን ይሄ አንድ ጠቃሚ ሁኔታን የዘነጋ ነው።ምክንያቱም ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተጫወቱትን ሚና ያደበዝዘዋል። ምክንያቱም ከ17ኛው መቶ ዓመት ጀምሮ፣ብዙ የኦሮሞ ልዒቃን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ለመጫወት ችለዋል። ደጃዝማች ቱሉ የሚባል በዓፄ እያሱ ቀዳማዊ ዘመን ደጃዝማች ወሬኛ የሚባለው፣በካፋና በምንትዋብ ዘመን የነበራቸው ከፍተኛ የፖለቲካና የየጁ ዳይናስቲ ተብሎ የሚጠራው፣ አንድ ሃምሳና ስድሣ ዓመት የቆየ፣ እስከ አፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ድረስ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ ይገዙ የነበሩ ምንጫቸው ኦሮሞ ነው።"
ማንነትን እንደ ሥልጣንና ሃብት ማካበቻ
እውነታው ይህ ሆኖ እያለ፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የብሔር ግጭት እንዲስፋፋና የማንነት ጥያቄ አወዘጋቢ እንዲሆን የሚደረገው፣ የሥልጣን እና የጥቅም ጉዳይ ስለሆነ መሆኑን የታሪክ ምሁሩ አብራርተዋል። "የጎሣ ግጭት በተንሰራፋበት እና የማንነት ጥያቄ እንደዚህ አወዘጋቢ በሆነበት ጊዜ፣ መጤና ነባር በሚል መፈራረጅ፣ ኢትዮጵያውያን በተገነጣጠሉበት ጊዜ ይህን በድፍረት ማቅረብ ትንሽ እንግዳ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ፣ የሃገራችንን ታሪክ ስናጤን፣ ይህን የሚክዱት እንኳን ቢሆኑ በልባቸው በእርግጥ ይህ ነገር እውነት እንደሆነ፣ኢትዮጵያዊያንን የሚያስተሳስሩ ብዙ እሴቶች እንዳሉ ያውቁታል፤ ግን የጥቅምና የስልጣን ጉዳይ ብቻ ስለሆነ ነው ይህን እየካዱ እስካሁን ድረስ የዘለቁትም ወደፊትም ለመስለቅ የሚሞክሩት።" እዚህ አትላንታ ከተማ የሚገኘው የሞርሐውስ ኮሌጅ የታሪክ ተባባሪ ፕሮፌሰር ኀይሌ ላሬቦ በበኩላቸው፣ "የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ እና ብሔራዊ ውሕደት"በሚል ርዕስ የጥናት ጽሑፋቸውን አቅርበዋል።
ዘመነ ትንሳኤ
እንደ እርሳቸው ማብራሪያም፣ የኢትዮጵያውያን ብሔራዊ አንድነትና ውሕደት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ያሉትን የአፄ ኃይለሥላሴ የዘመነ መንግስት፣ ዘመነ ትንሳኤ በማለት አውስተውታል።
ፕሮፌሰር ኀይሌ፣ የአሁኑን የጨለማና የድብልቅልቅ ወይም የጽንፈኞች ዘመን ብለው ፈረጀውታል። "ይህ እንግዲህ የአስተያየት ጉዳይ ነው።እኔ የጽንፈኞች ዘመን ነው የምለው። እነዚህ በውጭ ሃገር ትምህርት የተኮላሹ ናቸው።እንግዲህ የውጭ አገር ትምህርት የውጭ ሀገር ሰዎች ለኢትዮጵያ ጠንቅ እንደሆኑ ከጥንት ጀምሮ፣ገና የኢትዮጵያን መሬት እንደረገጡ ተነግሮ ነበር።" እነዚህ ጽንፈኞች ዋነኛ ምርኩዛቸው የሚያደርጉት፣ የቅኝ ገዢዎችን በተለይም ደግሞ የኢጣሊያን ፀረ ኢትዮጵያ ቅስቀሳ መሆኑን የጠቀሱት የታሪክ ምሁሩ፣መዳረሻቸውም አዲስ ኢትዮጵያን መፍጠር ወይም ከታሪክ ገጽ መፋቅ ነው ብለዋል። የዚህ ዓላማ አራማጆች፣ልዒቃን እንጂ በሕዝቡ መኻከል የሚነሳ ችግር አለመሆኑንም አመልክተዋል።
"እነዚህ ጽንፈኞች ምን ዓይነት ናቸው ሁለት ዐይነት የግራና የቀኝ፣ መነሻቸው የጭቆናና የብሔር አድልዎ ትርክት፣ የግራው የመደብ ትግል ይከተልና የኢትዮጵያ ሕዝብ በአቆርቋዥና በተቆርቋዥ ይከፋፍላል። የቀኙ ደግሞ የብሔር ትግል ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ በጨቋኝና በተጨቋኝ ይከፋፍላል። በአንድ መደብ ወይም በአንድ ብሄር የተገነባች አለበለዚያ በብዙ ብሄሮች የተዋቀረች ሃገርን ማቋቋም ነው።የመጨረሻ ዓላማቸው የስልጣን ሽኩቻ የሃብት ማካበቻ እንጂ ታሪካዊ ማስረጃ የለም።"ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ