1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የብሔር ተኮር ጥላቻን ለማስወገድ የተካሄደ ስብሰባ

ታሪኩ ኃይሉ
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2016

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘው ዐቢይ ችግር፣የጥላቻ ፖለቲካ መስፋፋት እንደሆነ ተገለጸ። መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ፣ በፕሪንስተን ከተማ ባደረገውና በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ በሚመራው የሲሜቲክ ጥናት ተቋም አማካይነት ጥላቻን የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።

የጥላቻ ንግግር መግለጫ
የጥላቻ ንግግር መግለጫ ምስል Elada Vasilyeva/Zoonar/picture alliance

በኢትዮጵያ የብሔር ተኮር ጥላቻን ለማስወገድ የተካሄደ ስብሰባ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ የብሔር ተኮር ጥላቻን ለማስወገድ የተካሄደ ስብሰባ 

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ህልውና እየተፈታተነ የሚገኘው ዐቢይ ችግር፣የጥላቻ ፖለቲካ መስፋፋት እንደሆነ ተገለጸ። መቀመጫውን  በዩናይትድ ስቴትስ፣በፕሪንስተን ከተማ ባደረገውና በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ በሚመራው የሲሜቲክ ጥናት ተቋም አማካይነት ጥላቻን የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል። ዋነኛ አጀንዳውን ከፖለቲካ ውጭ ያደረገው ይኸው ስብሰባ፣ በኢትዮጵያ የብሔር ጥላቻ መስፋፋት ዝንባሌ፣አገሪቱን አሁን ላይ ወደ አስከፊ ደረጃ እያደረሳት ስለመሆኑ ተወያይቷል።

አሳሳቢው የጥላቻ ፖለቲካ መስፋፋት 

ይኸው የጥላቻ ፖለቲካ መስፋፋት፣ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ይህን ውይይት ለማዘጋጀት እንዳነሳሳቸው፣ስብሰባውን ያዘጋጁትና የመሩት፣በፕሪንስተን የሴማዊ ጥናት ተቋም ዳይሬክተርና በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃና አፍሮ አሜሪካ ጥናት ክፍል መስራች ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል። 

"እኔ ዛሬ የማየው ትልቁ የኢትዮጵያ ችግር ጥላቻ፣ ዐማራው ኦሮሞውን አይወድም፣ኦሮሞው ዐማራን ይሰድባል፣ትግሬ እንደዚሁ...በዚህ ምክንያት ፖለቲካው ምንም ኢንተረስ አያደርገኝም። እኔ ሁልጊዜ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዴት አድርጎ በፍቅር፣በመከባበር አብሮ በመስራት፤ ድህነትን፣መሃይምነትን፣ በሽታን ከአገራችን የሚያጠፋ፣እሱን ነው እኔ የምፈልገው።ፖለቲካው ላይ ብዙም ፍላጎት የለኝም።እና በዚሁ ምክንያት ይህንን ነገር አየሁኝና ደግሞ የማየው በኢንተርኔት ዐየዋለሁ፣በጽሑፍ ዐየዋለሁ።ይኼ እኮ ምን ይጠቅማል ብዬ አስብኩኝና አንድ ሦስት ወንድሞቻችን ዐማራዎች፣ሦስት ትግሬዎች ሌሎችም አንድ ሦስት ነበሩ፣ ተሰብሰብንና ግሩም ግሩም ስብሰባ አደረግን።"

የውይይቱ ተሳታፊዎች 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት፣  በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የሰብአዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጎላ ተሳትፎ ያላቸውና እና በሰላም ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ታዋቂ ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል። ተሰብሳቢዎቹ እንደ  ፖለቲካና የብሔር ተወካይ ሳይሆን  በግል አቋማቸው እንዲሳተፉ መደረጉም ተገልጿል። "ሁላቸውም በአንዳንድ በኩል የሚቀያየሙ ሰዎች ናቸው የመጡት፤ እና እነሱ አንድ በአንድ ተቀምጠው ከመጀመሪያው ጀምረው ጥላቻ በሽታ እንደሆነ መፈቃቀር፣ መከባበር ደግሞ አስፈላጊ እንደሆነ ተረዱ።አሁን እነሱ የጀመሩትን ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምሳሌውን ተከትሎ ወደፊት እንዲሄድ ነው የምፈልገው።" 

የጥላቻ ፖለቲካ መስፋፋት የሰላምን ጭላንጭል ተስፋ እንዳያዳፍን ያሰጋልምስል Seyoum Getu/DW

ሰላማዊ የውይይትና የድርድር ባህል

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ከተለመደው የኃይልና የጦርነት አዙሪት ወጥቶ፣ዘመኑን እና ትውልዱን ወደሚዋጅ፣ ሰላማዊ የውይይትና የድርድር ባህል ለመሸጋገር ካልቻለ መዳረሻው እጅግ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል በስብሰባው ላይ ተወስቷል። ከዚህ ችግር በዘላቂነት መውጣት የሚቻለውም፣በዘርና በቋንቋ መጠላላትና ጸብን በመተው፣በጋራ የዕድገት ጉዳዮች ላይ ማተኮር ሲቻል መሆኑን፣የሴማዊ ጥናት ጥናት ዳይሬክተሩ ፕሮፌሰር ኤፍሬም አስገንዝበዋል። "እኛም ሕዝባችን ቃል ኪዳን ገብተን ተባብረን ትልልቅ ጠላቶቻችን ልነጥፋቸው፣ እነዚህ ትልልቅ ጠላቶቻችን ረሃብ፣በሽታ፣መኃይምነት፣እዛ ላይ ብናተኩር፣በዘር መጣላት፣ በቋንቋ መጣላት ትተን ወደፊት ብንገፋ፣ኢትዮጵያ  ወደፊት ትልቅ አገር ነው የምትሆነው።" 

የፖለቲካ ቅራኔዎችን በሰላምና በውይይት ብቻ ለመፍታት የሚያስችል ዐዲስና መዋቅራዊ ዴሞክራሲያዊ ባህል፣ በኢትዮጵያ መገንባት እንደሚያስፈልግም ተመልክቷል። ይህን በጎና አበረታች ያሉትን ጅማሮ የበለጠ አስፍቶና አጠናክሮ  ለመቀጠልና ሰፊ ሕዝባዊ ተደራሽነት እንዲኖረው ለማድረግ፣ ስምምነት ላይ መደረሱንም ከፕሮፌሰር ኤፍሬም ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። 

ታሪኩ ኃይሉ 

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW