በኢትዮጵያ የንግድ ባንኮች የብድር ገደብ አለመነሳት ለምን?
ሐሙስ፣ መስከረም 22 2018
በኢትዮጵያ የንግድ ባንኮች የብድር ገደብ አለመነሳት ለምን?
የኢትዮጵያ ብሐየራዊ ባንክ በተያዘው መስከረም ወር ሙሉ በሙሉ ልነሳ ይችላል ተብሎ የተጠበቀውን የባንኮች የብድር ገደብን ሳያነሳው ቀርቷል፡፡
ብሔራዊ ባንኩ ባንኮች ያለገደብ እንዲያበድሩ ከማድረግም ይልቅ በተያዘው በጀት ዓመት ከዚህ በፊት ለብድር እንዲያውሉት የተቀመጠውን የብድር ምጣኔው ገድብ ከ18 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ በማድረግ የተወሰነ ገደቡን የማላላት እርምጃ ወስዷል፡፡
እንደ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያዎች ይህ የሆነው በኢትዮጵያ አሁንም እልባት እንዲበጅለት የታለመውን የዋጋ ግሽበት መቆጣጠር እንዲቻል ነው ይላሉ፡፡
በቅርቡ ዋና ገዢው ማሞ ምህረቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲያገለግሉ በነበሩት ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ የተካው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በፊት ባንኮች ላይ ተጥሎ የነበረውን የብድር ገደብ ምጣኔ ፖሊሲን በነበረው ሁኔታ ለማስቀጠል ወስኗል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በየሶስት ወሩ የግሽበት ሁኔታውን ጨምሮ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን በመገምገም በሚያስተላልፈው ውሳኔ መሰረት የባንኮች የብድር ምጣኔን በተመለለከተ የነበረውን አሰራር አሁንም ለማስቀጠል ምርጫው አድርጓልም፡፡ የገንዘብ አስተዳደሩን የተረጋጋ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግም የማዕከላዊ ባንኩ ጥብቅ አቋምን ለማስቀጠል ስወስንም ግሽበትን መቆጣጠር አንዱ ዓላማው መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ኮሚቴው የባንኮች ብድር ምጣኔን ከ18 በመቶ በ6በመቶ ብቻ እምርታ በማሳየት ወደ 24 በመቶ ከፍ ስያደርግ ገደቡን ሙሉ በሙሉ ማንሳት በዚህ ደረጃ ስጋት ስላለውም ነው ተብሏል፡፡
ማዕከላዊ ባንኩ ለምን ገደቡን ለማንሳት አልደፈረም ?
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መሀመድ ይህ የብሔራዊ ባንኩ ውሳኔ ከዚህ በፊት ከተቀመጠው አቅጣጫ የተለየ ነው ይላሉ፡፡ “በብሔራዊ ባንክ ግምገማ መሰረት፤ በባለፈው ግምገማ መሰረት በመስከረም ወር አጠቃላይም ከሁለት ዓመት በፊት የተጣለው የብድር ገደቡ ይነሳል የሚል ነበር” በማለት ያ በብዙዎች ተስፋ የተደረገው ግን ሳይሆን ብሔረዊ ባንክ ገደቡን ከ18 በመቶ ወደ 24 በመቶ በተወሰነ መልኩ ለማላላት ብቻ እንደወሰነ ነው የገለጹት፡፡
የተበዳሪዎች ፍላጎት መናር
ባለፈው ሁለት ዓመት የብድር ገደብ ተጥሎ መቆየቱ የተበዳሪዎችን የመበደር ፍላጎት አንሮት መቆየቱ አያጠያይቅም የሚሉት አብዱልመናን ይህ ሙሉ በሙሉ የሚለቀቅ ከሆነ ግሽበትን ያባብሳል የሚለው ትልቁ ስጋት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ “ባንኮቹ አከባቢ እርግጠኛ ነኝ ከፍተኛ የብድር ጥያቄ አለ” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደደር ባለሙያው ገደቡን በአንዴ ሙሉ በሙሉ ማንሳት ባንኮች የሚሰጡትን ብድር ባንዴ
በከፍተኛ መጠን ማሳደግ እንደምችል ገልጸዋል፡፡ ያ ደሞ አሁን ያለውን 13 በመቶ ግድም ያለውን ግሽበት የባሰ አስከፊ ሊያደርግ ስለምችል ብሔራዊ ባንክ ጥንቃቄ በተሞላበት ደረጃ በደረጃ የብድር ገደቡን የማንሳት ሁኔታ ነው እየተከተለ ያለው ብለዋል፡፡ ይህም የግሽበት መጠኑ አሁንም በተፈለገው መጠን እየወረደ አለመሆኑ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
የገደቡ መላላት እና ፋይዳው
የብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ባለፈው ነሃሴ ወር የተመዘገበው የግሽበት መጠን 13.6 በመቶ ላይ በመቆም ከዚያ በፊት ከነበው ወር መውረዱን ገምግሟል፡፡፡ የምጣኔ ሃብቱ እድገት በዚህን ወቅት ደግሞ በተለይ በግብርናው፣ ኢንደስትሪው፣ የወጪ ንግድ እና አገልግሎት ዘርፍ እምርታ ማሳየቱንም ገምግሟል፡፡
የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አብዱለመናን መሀመድ ኮሚቴው በብድር ምጣኔው ላይ ያላላው የ6 በመቶ ልዩነት ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለውም ስገልጹ፤ “6 በመቶ ጥሩ ነው፤ ባንኮች ከፍተኛ የሆነ የብድር ፍላጎት ላላቸው እንደ የወጪ ንግድ እና አምራች ዘርፎች የተወሰነ የብድር ፍላጎት ማሟላት ይችላሉ” ብለዋል፡፡
የብድር ገደቡ የተሻለ አማራጭ ነውን
ባንከኮች ላይ የሚጣለው የብድር ገደብ መጠኑ አማራጭ በመታጣቱ እንጂኢኮኖሚውን በማቀዝቀዝ ያለው ሚና አሉታዊ እንደሆነ የገለጹት አብዱልመናል፤ የዋጋ ግሽበት ቁጥጥር ተፈላጊ ደረጃ ላይ ስደርስ ሙሉ በሙሉ መለቀቁ አይቀረ ነውም ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው በሚቀጥለው ታህሳስ ወር ተሰብስቦ አጠቃላይ ምጣኔሃብታዊ ሁኔታውን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ይጠበቃል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ